ማብራሪያ

የአዕምሮ እድገት ውስንነት ምንድን ነው?

አካል ጉዳተኞች ስንል የተለያዩ መሰናክሎች ከሚያስከትሏቸው ተጽእኖዎች የተነሳ ከሌሎች ጋር በእኩልነት በማኅበረሰቡ ውስጥ ሙሉ እና ውጤታማ ተሳትፎ እንዳያደርጉ ሊገድቡ የሚችሉ የረዥም ጊዜ የአካል፣ የአዕምሮ፣ የአዕምሯዊ እድገት ውስንነት ወይም የስሜት ህዋሳት ጉዳቶች ያሉባቸውን ያጠቃልላል፡፡ (ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ስምምነት፣ 1998 ዓ.ም.)

የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ሰዎች ሁሉንም ሰብአዊ መብቶች እና መሰረታዊ ነፃነቶች ሙሉ በሙሉ የመጠቀም መብት አላቸው፡፡

ዳውን ሲንድሮም እና ኦቲዝም

ዳውን ሲንድሮም በተፈጥሮ የሚከሰት የሕዋስ ክፍፍል/ውቅር   ሲሆን ከሰው ልጅ ጋር ሁሌም ሲኖር የቆየ ሁኔታ ነው። ይህም ብዙውን ጊዜ የተለያየ ዓይነት ደረጃ ያላቸው የአዕምሮ እና የአካል ጉዳት እንዲሁም ጉዳቱን ተከትሎ የሚመጡ ተያያዥ የጤና ጉዳዮችን ያስከትላል። (ዳውን ሲንድሮም ኢንተርናሽናል

ዳውን ሲንድሮም ያለባቸው ሰዎች ላይ የሚታዩት ምልክቶች በአንዱ ላይ የሚታየው ከሌላኛው ከፍተኛ የሆነ ልዩነት አላቸው፡፡ ይኹን እንጂ ከተለመዱት የዳውን ሲንደሮም መገለጫዎች መካከል የአዕምሮ እድገት ውስንነት፣ ልዩ የራስ ቅል ቅርጽ፣ የንግግር እና የቋንቋ እክል፣ የጡንቻ አለመጠንከር፣ የመስማት፣ የዕይታ፣ የልብ እና እድገትን የሚቆጣጠር እጢ እክሎችን ጨምሮ የተለያዩ ዓይነት የጤና እና የስሜት ህዋሳት ጉዳቶችን ያካትታል፡፡ (ቡል እና ሌሎችም፣ 2011)

ዳውን ሲንድሮም ለማዳን አይቻልም፤ የሚከሰተው በአጋጣሚ ሲሆን መከላከል ካለመቻሉም በላይ ወላጆች ባደረጓቸው ወይም ባላደረጓቸው ነገሮች ምክንያት የሚከሰት አይደለም፡፡ ሆኖም ተጓዳኝ የጤና ችግሮቹን በተለይም በቅድመ ወሊድ ምርመራ ወቅት ወይም ከወሊድ በኋላ በዕይታ ከታወቀ በጥሩ ሁኔታ ለመቆጣጠር ይችላል። (ኪድስ ኸልዝ፣ 2022) ትምህርት እና ተገቢ የሆነ እንክብካቤም ዳውን ሲንድሮም ያለባቸውን ሕጻናት የተሻለ ሕይወት እንዲኖሩ ለማድረግ ያስችላል። (ኸልዝላይን፣ 2017) ይህም ዳውን ሲንድሮም ያለባቸው ሰዎች በማኅበረሰባቸው ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ እና እምቅ ችሎታ ለማጎልበት ያግዛል፡፡

ኦቲዝም ወይም በሳይንሳዊ መጠሪያው ኦቲዝም ስፔክትረም ዲስኦርደር በማኅበራዊ መስተጋብር እና በተግባቦት ሁኔታዎች ላይ በተወሰነ ደረጃ የሚታይ ከአዕምሮ እድገት ጋር የሚገናኙ የተለያዩ ዓይነት ሁኔታዎችን የሚያካትት የጉዳት ዓይነት ነው፡፡ (የተመድ የዓለም ጤና ድርጅት፣ 2022) ሳይንሳዊ ማስረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ከዘረመል እና ከአካባቢያዊ ሁኔታዎች ጋር የተገናኙ ምክንያቶች አዕምሮ  ማደግ በሚጀምርበት ወቅት ተጽዕኖ በማድረግ ለኦቲዝም መከሰት አስተዋጽዖ ያደርጋሉ፡፡የኦቲዝም መገለጫ ባህሪያት በለጋ ዕድሜ ሊታወቁ የሚችሉ ቢሆንም፤ አብዛኛውን ጊዜ ኦቲዝምን ሳይታከም ለረጅም ግዜ ይቆያል ። በዓለም ዙሪያ ከመቶ ሕፃናት ውስጥ አንዱ ኦቲዝም ሊኖርበት እንደሚችል ይገመታል፡፡ (ዘይዳን እና ሌሎችም፣ 2022

የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ሰዎች ላይ የሚደርሱት የሰብአዊ መብቶች ተጽዕኖዎች ምንድን ናቸው?

የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ ፍረጃ እና ማኅበራዊ መገለል ተጋላጭ ናቸው፡፡ በአብዛኛው መሰረታዊ አገልግሎቶችን ከማግኘት ክልከላ ይደረግባቸዋል። እንዲሁም በማኅበረሰባቸው ውስጥ የሚኖራቸውን ተሳትፎ የሚያሰናክሉ ዓይነተ ብዙ አድልዎች፤  የሕግ፣ የአመለካከት እና ከባቢያዊ መሰናክሎች ይገጥማቸዋል፡፡ በተጨማሪም በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ውስጥ ባሉ የሲቪል፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና የባሕል እንቅስቃሴዎች ለመሳተፍ የሚችሉባቸውን እድሎች የሚነፈጉ በመሆኑ ፤ሰብአዊ መብቶቻቸውን ሙሉ በሙሉ እንዳይጠቀሙ ሆነዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?

ኦቲዝም እና ዳውን ሲንድሮምን በተመለከተ በኢትዮጵያ የተደረጉ ጥናቶች በጣም ጥቂት ቢሆኑም፤ ሕፃናትን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ እንደሚኖሩ ይገመታል። የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ሰዎች ውጤታማ አይደሉም ወይም የተረገሙ ናቸው የሚለው የተሳሳተ ግንዛቤ አሁን ድረስ ያለ በመሆኑ፤ ብዙውን ጊዜ በቤት ውስጥ ተደብቀው ወይም ተለይተው ለብቻቸው  እንዲቀመጡ ይደረጋሉ።

ኢትዮጵያ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ሰዎች ተካታችነት እና ተሳትፎ ሙሉ በሙሉ ለማረጋገጥ ገና ብዙ መሥራት ይጠበቅባታል። በርካታ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ሕፃናት ከትምህርት እና ከሌሎች እነሱን ከሚጠቅሙ እድሎች ርቀዋል፡፡ በዚህም ራሳቸውን እንዳይችሉ እና ሙሉ አቅማቸው መጠቀም እንዳይችሉ ሆነዋል።

በሀገራችን ያሉ አንዳንድ የመንግሥት እና የግል ትምህርት ቤቶች የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ሕፃናትን ጨምሮ የተለያዩ ዓይነት አካል ጉዳተኛ ሕፃናትን አካትተው ለማስተማር ይሞክራሉ፡፡ ይኹንና እነዚህ ጥረቶች ገና ብዙ የሚቀራቸው እና ካለው ፍላጎት ጋር የማይመጣጠኑ ናቸው፡፡

የአዕምሮ እድገት ውስንነቶች ከሌሎች ጉዳቶች የተለዩ ናቸው። በዚህ ምክንያት የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ሕፃናት በቡድን ወይም ሌላ ዓይነት የአካል ወይም የስሜት ህዋሳት ጉዳት ካለባቸው ልጆች ጋር ቀላቅሎ ማስተማር አስቸጋሪ ነው። ስለዚህ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ሰዎች ልዩነት ያገናዘበ አካታች የትምህርት ፖሊሲ መኖሩ ወሳኝ ነው። ይህም በትምህርት ቤቶች ውስጥ ያለውን የፖሊሲውን አፈፃፀም መከታተል፣ መምህራንን እና ሌሎች የትምህርት ቤት ሠራተኞችን ማሰልጠን እና ተገቢ በጀት መመደብን ያካትታል፡፡በዚህ ዓመት የዓለም ዳውን ሲንድሮም እና የኦቲዝም የግንዛቤ ማስጨበጫ ቀናት ‘‘ማካተት ሲባል’’ እና ‘‘በሥራ ቦታ ተካታችነት’’ በሚሉ መሪ ሃሳቦች ተከብረዋል።