የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በትግራይ ክልል እና በፌደራል መንግሥት ኃይሎች መካከል እየተካረሩ የመጡት ውጥረቶች እና በአንዳንድ ቦታዎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች አሳስበውታል።

በአፋር፣ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች ያለውን ከፍተኛ የሰብአዊ እርዳታ ፍላጎት ለመቅረፍ ጉልህ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው እና ለግጭቱ ፖለቲካዊ መፍትሔ ለማምጣት መሰረት የሚጥል መሆኑን በማመልከት ኢሰመኮ እ.ኤ.አ. መጋቢት 30 ቀን 2022 በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ባለስልጣናት በኩል የተሰጡትን የተኩስ አቁም መግለጫዎችን በበጎ የሚመለከተው መሆኑን መግለጹ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ የትግራይ ባለስልጣናትም ሆኑ የፌደራል መንግሥት “የሰዎችን ሕይወት ለማዳን እና ጉዳት ለመቀነስ ከመደበኛ ሁኔታ የተለዩ እርምዎጃችን ጭምር መወሰድ” እንዳለባቸው እና “የፖለቲካ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት” አስፈላጊ ስለመሆኑ መግለጻቸውም የሚታወስ ነው፡፡ ኮሚሽኑ የተሻሻለ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲኖር፣ የተቋረጡ መሰረታዊ አገልግሎቶችን እንዲመለሱ፣ በአፋር፣ በአማራ እና በትግራይ የሚገኙ ተጎጂዎች እና በግጭቱ የተጠቁ አካባቢዎች መልሰው እንዲቋቋሙ እንዲሁም ዘላቂ የፖለቲካ መፍትሔ እና ፍትሕን የሚያሰፍን የተጠያቂነት እርምጃ እንዲወሰድ ተደጋጋሚ ጥሪ አድርጓል።

ግጭቱ ከተጀመረበት ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. አንስቶ ኢሰመኮ ጦርነቱ በሲቪል ወንዶች፣ ሴቶች እና ሕፃናት ላይ ያስከተለውን ጉዳት ክትትል አድርጎ፣ ሰንዷል። በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ኃይሎች ከባድ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕግ ጥሰቶች የፈጸሙ ሲሆን፣ አንዳንዶቹም የጦር ወንጀሎች እና በሰብአዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ሊሆኑ በሚችል መልኩ ከሕግ አግባብ እና ከፍርድ ውጪ የተፈጸሙ ግድያዎችን ጨምሮ የጭካኔ፤ ኢ-ሰብአዊና አዋራጅ አያያዝና ቅጣትን፣ የዘፈቀደ እስር፣ ጠለፋ እና አስገድዶ መሰወርን፣ በንብረት ላይ የተፈጸመ ዘረፋ፣ ገፈፋ እና ውድመትን፣ ወሲባዊ እና ጾታ-ተኮር ጥቃቶችን፣ በግዳጅ መፈናቀልን፣ የመንቀሳቀስ መብት ላይ ሕገ-ወጥ ገደቦች መጣልን ጨምሮ የኢኮኖሚ ማኅበራዊ እና የባሕላዊ መብቶች ላይ የደረሱ ጥሰቶችን እንደሚያጠቃልሉ በሪፖርቶቹ አመላክቷል፡፡ በተለይም ሴቶች፣ ሕፃናት፣ አዛውንቶች እና አካል ጉዳተኞች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የጦርነቱን ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆኑ ውጤቶች አሁንም እየኖሩ ያሉ፣ ለጥልቅ የሥነልቦናዊ ጉዳት የተዳረጉ፣ ኑሯቸውን እና የሚወዷቸውን ሰዎች ያጡ፣ እና መሰረታዊ አገልግሎቶች የተቋረጠባቸው ሲቪል ወንዶች፣ ሴቶች እና ሕፃናት አሁንም ሙሉ በሙሉ ወደ ማኅበረሰቡ እንደገና መቀላቀልን ጨምሮ ካሳ፣ መልሶ መቋቋምንና ፍትሕን በመጠበቅ ላይ ይገኛሉ። በአፋር፣ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ በሁሉም የጦርነቱ ተፋላሚ ኃይሎች ለተፈጸሙት የግፍና ጭካኔ ወንጀሎች ተጠያቂነት አሁንም ሊረጋገጥ የሚገባው ነው።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የዋጋ ንረት፣ የመሰረታዊ አቅርቦቶች እጥረትና በአብዛኛው የሀገሪቷ ሰሜኑ ክፍል የሚደረጉ የምርት እንቅስቃሴዎች መቋረጣቸው፣ እንዲሁም በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ያሉት የሰብአዊ እርዳታ ፍላጎቶች በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥረዋል፡፡ በዚህ አውድ ውስጥ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የሚከሰት ተጨማሪ ግጭት እና ጦርነት ሸክም ከፍተኛና ለመገመት አዳጋች የሚሆን ነው፡፡ የሲቪል ሰዎችን በጽኑ ከመጉዳት ባለፈ ተጨማሪ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕጎች ጥሰቶችንም ያስከትላል፡፡ 

ስለሆነም ኢሰመኮ የሚከተለውን ጥሪ ያቀርባል፡-

  • ሁሉም የግጭቱ አካላት፣ ሀገራዊ ባለድርሻዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የብዙኃን መገናኛዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች እና ሌሎች ተዋናዮች፣ ለገንቢ ውይይቶች እና ምክክሮች የበኩላቸውን በማበርከት እና ከማንኛውም የግጭት ቅስቀሳ ወይም የጥላቻ ንግግር በመቆጠብ ይልቁንም ለጋራ መግባባት፣ መቻቻል እና ለሰላም አስተዋጽኦ በማድረግ ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያደርጓቸውን ጥረቶች እንዲያድሱ፣
  • የአፍሪካ ሕብረት፣ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ አጋሮች ጦርነትን ለማስቀረት እና ሰላም እንዲሰፍን የሚደረጉ ሀገራዊ ጥረቶችን እንዲደግፉ፣ እና ውይይቶችን እንዲያመቻቹ፣ 
  • የፌደራል መንግሥት፣ እንዲሁም የአፋር እና የአማራ ክልል ባለስልጣናት የሰብአዊ እርዳታዎች ደኅንነታቸው በተጠበቀ እና ባልተገደበ ሁኔታ ወደ ትግራይ እንዲገቡ የማመቻቸት ስራዎችን እንዲያሻሽሉ፣
  • የትግራይ ክልል ባለስልጣናት ሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ የሚገቡባቸውንና በአጎራባች ክልሎች የሚገኙ አካባቢዎችን ከመቆጣጠር ብሎም የሰብአዊ እርዳታን የሚያጓጉዙ መኪኖችን ከመያዝ መቆጥብ ጨምሮ፣ ለሲቪል ሰዎች በአስቸኳይ ሊደርሱላቸው የሚገቡየሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቶችን እንዲያገኙ ለሚደረጉ ጥረቶች አስፈላጊውን ትብብር ሁሉ እንዲያደርጉ።

የእንግሊዘኛውን ይፋዊ መግለጫ ለማንበብ እዚህ ጋር ይጫኑ