ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረግ ዓመታዊ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል በአዲስ አበባ፣ በአዳማ እና በሀዋሳ ከተሞች ይዘጋጃል 

በሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥኑ ፊልሞች ለእይታ እና ለውይይት የሚቀርቡበት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል በሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ላይ ግንዛቤ ለማዳበር ሰፊ ተደራሽነት ያለውን የፊልም ጥበብ እንደአንድ መንገድ መጠቀም ዓላማው አድርጓል፡፡ በፊልም ፌስቲቫሉ ላይ ከዚህ በፊት ለእይታ የበቁ እና አዳዲስ የሙሉ ጊዜ፣ አጫጭር እና ዘጋቢ ፊልሞች ለእይታ ይቀርባሉ፡፡

በሴቶች እና የሕጻናት መብቶች፣ በአካል ጉዳተኝነት እና በአረጋውያን መብቶች ጥበቃ እና እንክብካቤ፣ የመደራጀት እና የመንቀሳቀስ መብቶች፣ በሕይወት የመኖር መብት፣ በሕግ እኩል ጥበቃ የማግኘት እና ፍትሕ የማግኘት መብቶች፣ በባሕል መብት ስርም በራስ ባሕል የመሳተፍ፣ በእኩልነት ሰብአዊ ክብርን በጠበቀና ከመድሎ በጸዳ መልኩ በራስ ቋንቋ የመማር መብቶች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ፊልሞች ይቀርባሉ፣ ውይይቶች ይደረጋሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል በኅዳር 28 ቀን 2014 ዓ.ም. በአዳማ ኦሊያድ ሲኒማ፣ በኅዳር 29 ቀን 2014 ዓ.ም. ደግሞ በሀዋሳ ከተማ ሌዊ ሲኒማ በመጨረሻም በታኅሣሥ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በጋርደን ግሩቭ ዎክ መናፈሻ የሚካሄድ ሲሆን፣ በፌስቲቫሉ ላይ ጥሪ የሚደረግላቸው የፊልም እና በሌሎች የኪነጥበብ ዘርፍ ሙያ ላይ የሚገኙ ባለሞያዎች፣ የተለያዩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ በሰብአዊ መብቶች ላይ ትኩረታቸውን አድርገው የሚሰሩ ተቋማት፣ ሚዲያዎች፣ ተማሪዎች እንዲሁም ፍላጎቱ ያላቸው ተመልካቾች ይታደሙበታል፡፡