ታኅሣሥ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. በአጋርነት ጉዳዮች የስራ ክፍል የተዘጋጀ የምክክር አውደጥናት

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከተለያዩ በሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ላይ ከሚሰሩ ሀገራዊ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ያቋቋመውን የትብብር መድረክ አንድ ዓመት አፈጻጸም ለመገምገምና ለቀጣዩ ዓመት መደረግ ስለሚኖርባቸው ማሻሻያዎች ላይ ለመወያየት ያለመው ይህ ስብሰባ፣ ከ40 በላይ የመሪ ጥምረት ድርጅቶችን፣ ማኅበራትን፣ የሰብአዊ መብቶች  ላይ የሚሰሩ ድርጅቶችን እና ከሌሎች ክልሎች የተውጣጡና የየትኛውም ማኅበር አካል ያልሆኑ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ተወካዮችን ያሳተፈ ነበር።

በምክክር አውደ ጥናቱ የኢሰመኮ-የሲቪል ማኅበራት ትብብር መድረክ  ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ምንም እንኳን በሀገሪቱ ባለው ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ እና በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተጽዕኖ ምክንያት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የቆየ ቢሆንም በእቅዱ የያዛቸውን የተለያዩ ተግባራትን በተሳካ ሁኔታ መፈጸም መቻሉ ተመልክቷል። እነዚህ ስኬቶች በኢሰመኮ እና ከአንዳንድ የሲቪል ማኅበራት ጋር በጋራ አጀንዳዎቻቸው ላይ ተቀራርበው እንዲሰሩ ማድረግ አስችሏል።

ዓመታዊ የአፈጻጸም ዳሰሳ ለማድረግ የተዘጋጁ መረጃ መሰብሰቢያ ቅጾች  በተሳታፊዎች  እንዲሞሉ የተደረገ ሲሆን የትብብር መድረኩ አባላትን ቁጥር ለመጨመር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተደርጎ ቀጣይ፣ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል። እንዲሁም በስብሰባው የትብብር መድረኩን ቀጣይ ዓመት ምክትል ሰብሳቢ (co-chair) የተመረጠ ሲሆን ከተጠቆሙት 5 የሰብአዊ መብቶች ድርጀቶች መከከል በድምጽ ብልጫ የሰብአዊ መብት ድርጀቶች ህብረት (CEHRO) በድጋሚ ተመርጧል። 

በተጨማሪም በኢሰመኮ- ሲቪክ ማኅበራት ትብብር መድረክ ስር ከኢሰመኮ ዘርፍ የስራ ክፍሎች ጋር ተናቦ ለመስራት የሚያስችሉ 4 ንዑስ የትብብር መድረኮች የተመሰረቱ ሲሆን፣ በንዑስ መድረኮቹ ሚናና ኃላፊነት ላይ በቂ መረጃ ተሰብስቧል። በሀገር አቀፍ ደረጃ የሰብአዊ መብት ባሕሉ የዳበረ ማኅበረሰብ ለመፍጠር፣ የትብብር መድረኩ በቅድሚያ ሊያተኩርባቸው የሚገቡ ጉዳዮችን መለየት ተችሏል።

ታኅሣሥ 26 ቀን 2014 ዓ.ም. በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች የስራ ክፍል የተዘጋጀ ወርክሾፕ 

በስራና ሰራተኛ መብቶች ላይ ያተኮረው ይህ ወርክሾፕ ከፌዴራልና ክልል የእምባ ጠባቂ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ቢሮ፣ የስራና ሰራተኞች ክህሎት ልማት ጽሕፈት ቤቶች፣ ከአሰሪና ሰራተኞች ጉዳይ ቢሮዎች እንዲሁም ከሚመለከታቸው የሴቶችና ሕፃናት ቢሮዎች የስራ ክፍሎችና በስራና ተያያዥ መብቶች ላይ የሚሰሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮችን አሳትፏል። በወርክሾፑ ኢሰመኮ “ከኖርዝ ኢስት ፖሊሲ ቲንክ ታንክ” ጋር በመተባበር በስራና ሰራተኞች መብቶች ላይ ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ የሚዳስስ ጥናት ቀዳሚ ግኝቶች ቀርበው፣ የስብሰባው ተሳታፊዎች ዳሰሳው ሊያካትታቸው ስለሚገባ ነጥቦች ግብዓት ሰጥተዋል። 

ከተሰጡት ግብዓቶች መካከል የሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል የመንግስት አካላት ወቅታዊ የሆነ የሰራተኞች መብቶች አፈጻጸም ቁጥጥር አለማድረጋቸው፣ በኢመደበኛ ሴክተሩና በተለይም በግል ሰራተኛ አፈላላጊ ኤጀንሲዎች የሚቀጠሩ ሰራተኞች በሰራተኛና አሰሪ ሕግ አለመሸፈናቸው፣ በግሉ ዘርፍ የተቀጠሩ ሰራተኞች የአነስተኛ ደሞዝ ወለል አለመኖሩ እንዲሁም በኢንዱስትሪያል ፓርክ የተቀጠሩ ሰራተኞች ደሞዝ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ ከፍተኛ ክፍተት በመሆኑ በዚህ ረገድ ውትወታ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ በዳሰሳው ምክረ ሃሳቦች ውስጥ እንዲካተቱ የሚሉት የገኙበታል። የስብሰባው ተሳታፊዎች ዳሰሳው በተለየ ሁኔታ ከሚያተኩርባቸው የኢንዱስትሪያል ፓርክ ውጪ የሚገኙ ሰራተኞችን የመብቶች ሁኔታም እንዲያካትትም ጠይቀዋል። 


ከጥር 2 እስከ 6 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ በሰብአዊ መብቶች ትምህርት የስራ ክፍል የተዘጋጀ የአሰልጣኞች ስልጠና 

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል በጅማ ከተማ ከሚገኙ ስድስት የወጣት ማኅበራት ለተወጣጡ 34 ወጣቶች (10 ሴቶች እና 24 ወንዶች) ከጥር 2 እስከ 6 ቀን 2014 ዓ.ም. ለአምስት ተከታታይ ቀናት የቆየና በሰላም፤ በአብሮነት እና በመቻቻል ላይ ያተኮረ የሰብአዊ መብቶች የአሰልጣኞች ስልጠና ሰጥቷል፡፡ 

ስልጠናው በተለይም የወጣት ማኅበራት አመራሮችን እውቀት፤ ክህሎት እና አመለካከት በመገንባት ሰብአዊ መብቶችን ተግባራዊ ለማድረግ፤ ለመጠበቅ እና ለማስፋፋት የሚያስችል ብቃት እንዲኖራቸው የማድረግ ዓላማ ያነገበ ሲሆን፣ በቀጣይም በሁሉም ክልሎች ለሚገኙ ተመሳሳይ ማኅበራት የሚሰጥ ነው፡፡

ወጣቶች በሰላምና በጋራ መኖርን እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ ካሉ ልዩነቶች በመነሳት የሚከሰቱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በመከላከል ስራ ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ የማስቻል ዓላማ ያለው ይህ ስልጠና ሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ ሃያ አምስት ክንውኖችን ያካተተ ነው፡፡ የመጀመሪያው ክፍል መሰረታዊ የሰብአዊ መብቶችን እውቀት ከማስጨበጥ አኳያ የሰብአዊ መብት ትርጉምን፤ እሴቶችን፤ መርሆዎችን፤  በሀገር አቀፍ ፤ አህጉር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ የሕግ ማዕቀፎችን፤ ግዴታዎችንና ገደቦችን እንዲሁም መብቶችን በማስከበር ረገድ ኃላፊነት ያለባቸው አካላት የትኞቹ እንደሆኑ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ነው፡፡ 

ሁለተኛው ክፍል ሰልጣኞች ሰብአዊ መብቶችን በኢትዮጵያ ካሉ ነባራዊ ሁኔታዎች አንጻር እንዲመለከቱ በማስቻል በተለይም ከግጭቶች እና ከጥላቻ ንግግር ጋር በተያያዘ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ላይ ትንተና እንዲሰጡ የሚያስችል ሆኖ የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጡ የተቀረጸ ነው፡፡ ሦስተኛው ክፍል ተሳታፊዎች ሰብአዊ መብቶችን ለማስከበርና ለማስፋፋት የሚረዱ ከህሎቶችን እንዲያዳብሩ የሚያደርግ ነው፡፡ ከእነዚህ ክህሎቶች መካከል የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን የመለየት፤ አቤቱታ የማቅረብ፤ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በተመለከተ የዘገባ አጻጻፍና አላላክ ሂደት እና የሰብአዊ መብቶች ማስፋፍያ ዘመቻ ስልት ማዘጋጀት ይገኙበታል፡፡ ስልጠናው ተሳታፊዎች ሰብአዊ መብቶች ምን ያህል ከእለት ተእለት ኑሮ ጋር የተቆራኙ እንደሆኑ እንዲያስተውሉ የሚረዳ ሆኖ የእርስ በእርስ መማማርን፤ ጥልቅ እሳቤን እና የእውቀት ፈጠራን የሚያበረታታ አሳታፊና መስተጋብራዊ የስልጠና ዘዴዎችን ተግባራዊ ያደረገ ነው፡፡ 

በአጠቃላይ የስልጠናው ተሳታፊዎች በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ዙሪያ ሰፊ ግንዛቤ እንዲኖራቸው፤ የእለት ተእለት ሁኔታዎችን ከሰብአዊ መብት አንፃር እንዲተነትኑ እና  ወደመጡበት አካባቢ ሲመለሱ በተቋምም ሆነ በግለሰብ ደረጃ በተግባር ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎችንና ተግባራትን እንዲለዩ የሚያስችል ነው፡፡