የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋዜጣዊ መግለጫ

መስከረም 21 ቀን 2014 ዓ.ም.

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፡ በመተከልና ካማሺ ዞኖች የዜጎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ሊፋጠኑ ይገባል 

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል እና ካማሺ ዞኖች ያለውን የፀጥታ ሁኔታና የነዋሪዎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ በፌዴራል መንግስቱና በአካባቢው ኮማንድ ፖስት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች በተሻለ ፍጥነት ሊተገበሩና ሊጠናከሩ እንደሚገባ አሳሰበ። በተለይም በአሁኑ ወቅት ከሴዳል ወረዳ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ሸሽተው የሚገኙ ነዋሪዎች እንደሚገልጹት፣ ከጥር ወር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በወረዳው በሚደርሱ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ምክንያት በርካታ ነዋሪዎች የተፈናቀሉ ሲሆን፣ ከመጋቢት ወር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ዝግ ሆነው ቆይተዋል።

ከመስከረም 14 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ የአካባቢው ነዋሪዎች “የጉሙዝ ታጣቂዎች” ብለው የሚጠሯቸው ኃይሎች በወረዳው የሚኖሩ ሕጻናትን፣ ሴቶችንና አረጋውያንን ጨምሮ ወደ 145 የሚገመቱ የጉሙዝ ብሔር ተወላጅ የሆኑ አባወራዎችን (ቤተሰቦችን) ማገታቸውን ከዚሁ ሁኔታ የሸሹ ነዋሪዎች ለኮሚሽኑ አሳውቀዋል። ታጣቂዎቹ “ዓላማችንን አልደገፋችሁም” በሚል ምክንያት አፍሰው እንደወሰዷቸውና በተለምዶ “መርሻው” እና “ኤክፈት” ተብሎ በሚጠራ አካባቢ እንዳገቷቸው አክለው አስረድተዋል። ከታጋቾቹ መካከል “ቢያንስ ሁለት ሰዎች በታጣቂዎቹ መገደላቸውንና” ቀሪው “በአስከፊ ስቃይ ውስጥ የተያዙ” መሆናቸውንም ይገልጻሉ። በመስከረም 14 ቀን 2014 ዓ.ም.  በደረሰው ጥቃት ምክንያት ወደ 5000 የሚሆኑ ተጨማሪ የሴዳል ወረዳ ነዋሪዎች ተፈናቅለው ለጊዜው በወረዳው መስተዳደር ግቢ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ኮሚሽኑ ባደረገው ክትትል፣ ከመስከረም 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች እና በታጣቂ ኃይሎቹ መካከል “ውጊያ” በመካሄድ ላይ መሆኑንና ከመስከረም 19 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ ነዋሪዎችን ወደ ዳሊቲ ከተማ ለማሸሽ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተገንዝቧል። ይሁንና የሴዳል ወረዳ አመራሮችም ሆነ ከወረዳው የሸሹ ነዋሪዎች በአካባቢው የተሰማራው የፀጥታ ኃይል በቂ እንዳልሆነ ያስረዳሉ።

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በካማሺ እና በመተከል ዞኖች በተደጋጋሚ የሲቪል ሰዎችን ሕይወት፣ አካል እና ንብረት አደጋ ላይ የጣሉ ጥቃቶች ሲፈጸሙ ቢቆዩም፣ በፌዴራል እና ክልል መንግሥታት የተወሰዱት እርምጃዎች አደጋውን ለመቀልበስ እና የሲቪል ሰዎችን ሕይወት ከሞት ለመታደግ በቂ ባለመሆናቸው ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ሁለንተናዊ መፍትሔ የማፈላለጉ ሂደት አሁንም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ይህንኑ በማጠናከር “በአሁኑ ወቅት በሴዳል ወረዳ ታግተው የሚገኙ ነዋሪዎች ለተባባሰ የሰብአዊ ቀውስ እንዳይጋለጡና ከወረዳው ተፈናቅለው በዳሊቲ ከተማና በሌሎች ጊዜያዊ መጠለያዎች የሚገኙ ነዋሪዎች አስፈላጊው የሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስላቸው አፋጣኝ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ኮሚሽኑ በጥብቅ ያሳስባል” ብለዋል።