© UNICEF Ethiopia/2020/Mulugeta Ayene

የሳምንቱ የሰብአዊ መብቶች ጽንሰ-ሀሳብ
ጥር 30 – የካቲት 4 2014

ዓለም አቀፍ የሴት ልጅ ግርዛትን የማስወገድ ቀን እ.ኤ.አ. የካቲት 6 ቀን 2022 “የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስወገድ የበለጠ ሃብት መመደብ” በሚል መሪ ቃል በዓለም አቀፍ ደረጃ ታስቦ ውሏል፡፡

ሴቶችና ልጃገረዶች እንደ ማንኛውም ሰው ሰብአዊ መብቶቻቸው ሊከበሩላቸውና ሊጠበቁላቸው ይገባል። የተከበሩላቸው በመሆኑ መብቶቻቸውን የመጠቀም መብት አላቸው፡፡ የሴት ልጅ ግርዛት ጾታን መሰረት ካደረጉ የመድልዎ ዓይነቶች ውስጥ የሚካተት የሴቶችንና የልጃገረዶችን የእኩልነት፣ የአካል ደህንነት፣ ከጨካኝ፣ ኢሰብአዊ እና አዋራጅ አያያዝና ቅጣት የመጠበቅ፣ የነጻነት መብቶችን እንዲሁም ለኑሮ የሚያስፈልግ ዝቅተኛ ደረጃን የሚጥስ ድርጊት ነው፡፡ (ተ.መ.ድ.)

የአፍሪካ የሰዎችና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር አካል የሆነው የአፍሪካ ሴቶች መብቶች ፕሮቶኮል አንቀጽ 5 (ማፑቶ ፕሮቶኮል) ሀገራት ቅጣትን የሚያስከትሉ ሕጎችን በማውጣት ማንኛውንም አይነት የሴት ልጅ ግርዛትን መከልከል እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ 

ዩኒሴፍ እ.ኤ.አ. በ2020 ባወጣው መረጃ በኢትዮጵያ 25 ሚሊዮን ልጃገረዶችና ሴቶች የሴት ልጅ ግርዛት የተፈጸመባቸው መሆኑን የሚጠቁም ሲሆን ይህ አሃዝ በምስራቅ እና በደቡብ አፍሪካ ከተመዘገበው ከፍተኛው መሆኑን መረጃው ይገልጻል፡፡ ኢትዮጵያ ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ የሴት ልጅ ግርዛትን እና ሌሎች ኢ-ሰብአዊነታቸው የታወቀና ጎጂነታቸው በሕክምና ሙያ የተረጋገጠ ልማዳዊ ድርጊቶችን መፈጸም በኢፌዲሪ የወንጀል ሕግ መከልከሏ ይታወቃል፡፡ እንዲሁም በ10 ዓመት ፍኖተ ብልፅግና የሴት ልጅ ግርዛትን በአሁኑ ወቅት ካለበት 65% ደረጃ በ2022 ዓ.ም. መሉ ለሙሉ የማጥፋት ግብ ተካቷል። ሆኖም ድርጊቱን ለማጥፋትና የሴቶችንና የልጃገረዶችን ሰብአዊ መብቶች ለማስጠበቅ ተጨማሪ ስር-ነቀል እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል፡፡

በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን እና ጎጂ ልማዶችን ለማስቀረት የሚደረገው ጥረት ሊጠናከር ይገባል