የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋዜጣዊ መግለጫ 
መጋቢት 14 ቀን 2014 ዓ.ም.

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የከረዩ የሚችሌ ገዳ የጅላ አባላት ግድያ ላይ ያደረገውን የምርመራ ሪፖርት ጥር 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ በማድረግ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በጅላ አባላቱ ላይ ግድያ የፈጸሙና ያስፈጸሙ አባላት ላይ ተገቢ የሆነ የወንጀል ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ እና ለተጎጂ ቤተሰቦች ተገቢ የሆነ ካሳ እንዲከፈላቸው ምክረ ሃሳብ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ ይህንኑ የኮሚሽኑ ጥሪ ተከትሎ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፖሊስ ኮሚሽን ጉዳዩን በመመርመር ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሚሰራ መሆኑን ጥር 25 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ማሳወቁም የሚታወስ ነው፡፡

ይህንኑ መሰረት በማድረግ ኮሚሽኑ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የተሰሩ ስራዎች ያሉበትን ደረጃ ለመገምገም ከየካቲት 28 እስከ መጋቢት 3 ቀን 2014 ዓ.ም ክትትል አድርጓል፡፡ በክትትሉም የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፖሊስ ኮሚሽን፣ የምሥራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ፣ ግድያውን ለመመርመር የተዋቀረውን የምርመራ ቡድን እንዲሁም የከረዩ ማኅበረሰብ የሀገር ሽማግሌዎችን አነጋግሯል፡፡

በዚህም መሰረት በአንድ በኩል የተፈጸመውን ግድያ ለመመርመር ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የተውጣጣ መርማሪ ቡድን ተቋቁሞ ሥራ የጀመረ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡ በሂደቱም እስከ መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው የሚገኝ መሆኑን ኮሚሽኑ ተጠርጣሪዎቹ የሚገኙበትን የማቆያ ቦታ በመጎብኘት አረጋግጧል፡፡

የክልሉ መንግሥት ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎች አበረታች መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ኢሰመኮ የተሻለ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ክፍተቶችንም ተመልክቷል፡፡

በአንድ በኩል በአካባቢው ማኅበረሰብ በግድያው ላይ ተሳትፎ ያላቸው መሆኑን የተጠቆሙ፣ አልያም በድርጊቱ ዋነኛ ፈጻሚ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች ገና በቁጥጥር ስር ያልዋሉ ወይም ምርመራ እየተደረገባቸው አለመሆኑን ምክንያታዊ አሳማኝ ሁኔታዎችን ኮሚሽኑ ተገንዝቧል። ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች ውስጥ የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ቦታዎች ላይ የሚገኙ ጭምር ያሉ በመሆናቸው በምርመራ ሂደቱ ላይ ጫና እያደረሱ መሆናቸውን ወይም ለሂደቱ አስፈላጊ ድጋፍ ማድረግ የሚገባቸው የፀጥታ እና የአስተዳዳር አካላትም ሥራው በሚፈለገው ፍጥነት እንዲጠናቀቅ በቂ ትብብር እያደረጉ እንዳልሆነ ተዓማኒ የመረጃ ምንጮች ለኮሚሽኑ አስረድተዋል፡፡ በሌላ በኩል የምርመራ ሂደቱን በተመለከተ፣በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች በሕግ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ፍርድ ቤት ያልቀረቡ መሆኑን ኮሚሽኑ ተረድቷል፡፡ 

የክልሉ መንግሥት የኮሙኒኬሺን ቢሮ መጋቢት 13 ቀን 2014 ዓ.ም. በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ እየተካሄደ ካለው የወንጀል ምርመራ ሥራ ጎን ለጎን በኦሮሚያ ክልል የአባገዳዎች ምክር ቤት አስተባባሪነት በክልሉ መንግሥት እና በከረዩ ማኅበረሰብ የሀገር ሽማግሌዎች መካከል ሽምግልና እየተካሄደ መሆኑን ኢሰመኮ ተረድቷል፡፡ 

መንግሥት በሕዝቡ ላይ የተፈጠረውን ቅሬታ በእርቅ እንዲፈታ ጥረት ማድረጉ ተገቢ ቢሆንም የእርቅ ሂደቱ የወንጀል ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ሊያስቀር ስለማይችል የሕግ ተጠያቂነት ሂደቱ ሊደናቀፍ አይገባም፡፡ ተጠያቂነትንና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚወሰዱ የሕግና የወንጀል ምርመራ እርምጃዎችን በአካባቢዎች ባሕልና ልማድ መሰረት በሚደረጉ የእርቅ ሂደቶች መደገፍ በአንዳንድ ሁኔታዎች የተለመደ ሂደት ቢሆንም፣ የዚህ አይነቱ አሰራር በተጎጂዎች፣ በተጎጂዎች ቤተሰቦችና በአካባቢው ማኅበረሰብ ሙሉ ፈቃድና ተሳትፎ ሊሆን ይገባል። 

ይህን መሰል ሂደቶች በአካባቢው ማኅበረሰብ የሕግ ተጠያቂነትን ለመተካት አልያም ለማስቀረት የሚደረግ መሆኑን የሚያመላክት ቅሬታ ካለ ከጥቅሙ ይልቅ አሉታዊ ተጽዕኖው ሊያመዝን ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄ ይሻል። ስለሆነም የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “የተጎዱትን መካስ፣ ዕርቅና ሰላም፣ ፍትሕና ተጠያቂነት በአንድነት ሊተገበሩ የሚችሉና የሚገቡ በመሆናቸው፣ የመንግሥት ኃላፊዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ ለዚህ አይነት የተሟላ ዕርቅ፣ ሰላምና ፍትሕ በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል” በማለት አሳስበዋል፡፡