የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከዋናው መሥሪያ ቤት እና ከከተማ ጽሕፈት ቤቶች ለተውጣጡ አዳዲስና ነባር የክትትልና ምርመራ ባለሙያዎች በአቤቱታ ማስተናገጃ መመሪያ እና ከነጻ ምንጮች መረጃ በማሰበሰብ ምርመራ የማካሄድ (Open-Source Intelligence (OSINT)) ስልት ላይ በአዳማ ከተማ ተከታታይ የዐቅም ማሳደጊያ ስልጠናዎችን ሰጥቷል።

ኢሰመኮ ከፕሮጀክት ኤክስፒዳይት ጀስቲስ (Project Expedite Justice – PEJ) ጋር በመተባበር በአቤቱታ ማስተናገጃ መመሪያ ላይ ከግንቦት 12 እስከ 15 ቀን 2018 ዓ.ም.  የተዘጋጀው ስልጠና አዲስ በተከፈቱ የኢሰመኮ ጽሕፈት ቤቶች እና በነባር ጽሕፈት ቤቶች ለተቀጠሩ አዳዲስ ባለሙያዎች ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ ያለመ ነው። ስልጠናውን የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ሚዛኔ አባተን ጨምሮ በዘርፍ ኮሚሽነሮች እና ሌሎች የሥራ ክፍሉ ኃላፊዎች የተሰጠ ነው።

በስልጠናው በአቤቱታ ማስተናገጃ መመሪያ ዓላማ፣ በአቤቱታ አያያዝ ሥነ ሥርዓት፣ በቅድመ ምርመራ ሂደት፣ በኤሌክትሮኒክ ኬዝ አስተዳደር ሥርዓት (Electronic Case Management) አጠቃቀምና በሪፖርት አዘገጃጀት ዙሪያ ሰፊ ውይይትና ተግባራዊ ልምምድ ተደርጓል።

ስልጠናውን ያስጀመሩት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ፤ ባለሙያዎች አስፈላጊውን ዕውቀትና ክህሎት አዳብረው ሥራቸውን በብቃት እንዲወጡ ለማስቻል ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳለው ጠቁመው፣ ሰልጣኞች ያገኙትን ዐቅም ለሰብአዊ መብቶች መከበር በሥራ ላይ እንዲያውሉት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በተጨማሪም በጸጥታ ችግር ምክንያት በአካል ተገኝቶ ምርመራ ለማድረግ አስቸጋሪ በሆኑ አካባቢዎች የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን በዲጂታል ዘዴዎች ለማጣራት የሚያስችል ስልጠና ከሚያዝያ 26 እስከ 30 እንዲሁመ ሁለተኛው ዙር ከግንቦት 3 እስከ 6 ቀን 2018 ዓ.ም. በሁለት ዙር ተሰጥቷል። በዚህም ከነጻ ምንጮች መረጃ የማሰባሰብ ዘዴዎች፣ የዲጂታል መረጃ ደኅንነት ጥበቃ፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ትንተና፣ የሚዲያ ይዘቶች እውነተኛነት ማረጋገጫ መሠረታዊ መርሖች፣ የምስልና ቪዲዮ መልክዓምድራዊ ቦታና ጊዜ መለያ ስልቶች (Geolocation and Chrono-location) እንዲሁም በምርመራ ወቅት የሚያጋጥም ቀጥተኛ ያልሆነ የሥነ ልቦና ጉዳት (Vicarious Trauma) ዙሪያ ሰፊ ግንዛቤ ተፈጥሯል።

ተሳታፊ ባለሙያዎቹም ስልጠናው በዲጂታል ምርመራ ላይ የነበራቸውን ክህሎት በእጅጉ እንዳሳደገው በመግለጽ፣ ኮሚሽኑ መሰል የዐቅም ግንባታ ሥራዎችን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ትምህርትና ስልጠና ኮሚሽነር በዳሳ ለሜሳ፤ በኢሰመኮ የአቤቱታ ቅበላ ሥርዓት መመርያ መሠረት ዲጂታል ምርመራ ቁልፍ መሣሪያ መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም ሰው ሠራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence) እና ሐሰተኛ መረጃዎች በተበራከቱበት በዚህ ዘመን የዲጂታል መረጃዎችን እውነተኛነት ማጣራት ለሰብአዊ መብቶች መከበር ወሳኝ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተዋል። በመጨረሻም ሰልጣኞች ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት ወደ ተግባር በመለወጥ በዲጂታል ምርመራ ሥራዎች ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።