የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ ክልል የተለያዩ ዞኖች እና ከተማ አስተዳደሮች ሥር በሚገኙ 32 ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ባካሄደው የክትትል ሥራ ግኝቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ግንቦት 5 ቀን 2018 ዓ.ም. በባሕር ዳር ከተማ ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነርና የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ፤ የክልሉ ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የክልሉጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ፍትሕ ቢሮ፣ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ እንዲሁም ሚሊሻ ኮሚሽን፣ የተ.መ.ድ. የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር (Office of the High Commissioner for Human Rights / OHCHR) ባሕር ዳር ጽሕፈት ቤት እና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት የሥራ ኃላፊዎች እና ተወካዮች እንዲሁም የፖሊስ መምሪያ ኃላፊዎችና የጣቢያ አዛዦች ተሳትፈዋል።




በውይይቱ በክትትሉ የተለዩ መልካም ተሞክሮዎችና እና መሻሻል የሚገባቸው አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። የኢሰመኮ ክትትልን ተከትሎ በተደረገ ውትወታ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ለ172 ሰዎች መፍትሔ መሰጠቱ፤ በደቡብ ወሎ ዞን፣ ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች አብዛኛዎቹ ተጠርጣሪዎች በተያዙ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረባቸው፤ በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች ከትዳር አጋሮቻቸው ወይም ከቤተሰቦቻቸው፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው፣ ከሃይማኖትና ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር ሳምንቱን በሙሉ የሚገናኙበት የአሠራር ሁኔታ መዘርጋቱ፤ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጉን ድንጋጌዎች መሠረት ያደረገ የወንጀል ምርመራ አሠራር መኖሩ እንዲሁም በተወሰኑ ፖሊስ ጣቢያዎች ምቹ የተጠርጣሪዎች ማቆያ ክፍሎች መኖራቸው በመልካም እመርታነት ተጠቅሰዋል።




በሌላ በኩል በክትትሉ በተሸፈኑት በባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ሰሜን ጎጃም፣ እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች ስር በሚገኙ የፖሊስ ተጠርጣሪዎች ማቆያዎች ሰዎች ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ የሚያዙ እና በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት የማይቀርቡ መሆኑ፤ “ወቅታዊ ጉዳይ’’ በሚል የተያዙ ተጠርጣሪዎች እስከ 7 ወር ድረስ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለተራዘመ እስር የተዳረጉበት ሁኔታ መኖሩ፤ በተጠርጣሪዎች ላይ የሚፈጸም አካላዊ ቅጣት መኖሩ፤ የተጠርጣሪዎች የመጎብኘት መብታቸው መነፈጉ፤ አልፎ አልፎ በፖሊሶች የሚፈጸም ማስፈራራት፣ ዛቻ፣ ስድብ እና አካላዊ ቅጣት፤ ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚደረግ የተለየ ድጋፍ አለመኖር፤ ወጥነት ያለው የቅሬታ አቀራርብ ሥርዓት አለመኖር፤ ተጠርጣሪዎች ቀን ላይ ማረፊያ ክፍሎች ውስጥ ተዘግቶባቸው የሚውሉበት አሠራር መኖሩ ትኩረት የሚሹ እና ሊሻሻሉ የሚገባቸው አሳሳቢ ጉዳዮች መሆናቸው ተመላክቷል።




የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነርና የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው በኢሰመኮ የቀረቡት ግኝቶች ነባራዊ ሁኔታውን የሚያሳዩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም የተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝን የማሻሻል ሥራ የሚመለከታቸው አካላትን ድጋፍ የሚሻ መሆኑን እና ጠቅላይ መምሪያው የራሱን መመዘኛ (standard) አዘጋጅቶ ተግባር ላይ እያዋለ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ዮናስ ሙሉጌታ በግጭት እና የጸጥታ ችግሮች ዐውድ ውስጥም ፖሊስ ለሕግ የበላይነት እና ለሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎች እና መርሖዎች መከበር ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ገልጸው፤ ተጠርጣሪዎች ሰብአዊ ክብራቸው ተጠብቆ መያዛቸውን ለማረጋገጥ እና ለአጠቃላይ የክልሉ ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ መሻሻል ኢሰመኮ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሥራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።