የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች አቤቱታ ቅበላ እና አያያዝ ዙሪያ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚገኙ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚዎች ግንዛቤ ማሳደጊያ መድረክ ሰኔ 19 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አካሂዷል። በመድረኩ ከአዲስ አበባ፣ አማራ፣ ማእከላዊ ኢትዮጵያ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ እና ትግራይ ክልሎች የተወጣጡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚዎች ተገኝተዋል።

በመድረኩ ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት እና የሴቶች ሰብአዊ መብቶች እንዲሁም ሥርዓተ ጾታን ያማከለ የአቤቱታ አቀባበልና አያያዝ መርሖች ዙሪያ የመነሻ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸል። በተጨማሪም ተሳታፊዎች በዩኒቨርሲቲዎቻቸው የሚስተዋሉ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመከላከልና ለማስተናገድ የተዘረጉ አሠራሮችን፣ የተጎጂዎች ድጋፍ እና የቅብብሎሽ (referral) ሥርዓቶችን፣ እንዲሁም ተጠያቂነትንና ፍትሕን ለማረጋገጥ የሚተገበሩ አሠራሮችን በመገምገም መልካም ተሞክሮዎችን እና መሻሻል የሚያስፈልጋቸው ክፍተቶች እንዲሁም በቀጣይ ሊወሰዱ በሚገቡ እርምጃዎች ላይ ልምድና ሐሳብ ተለዋውጠዋል።

ተሳታፊዎች በዩኒቨርሲቲዎቻቸው ውስጥ የሚፈጸሙ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን በመከላከል እና ተገቢ ምላሽ በመስጠት ሂደት የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች አጋርተዋል። ከእነዚህም መካከል ወጥ የሆነ ፖሊሲ፣ መመሪያ እና የአሠራር ሥርዓት አለመኖር፤ የግንዛቤ ክፍተት፣ የሚስጥራዊነት ጥበቃ አለመኖር፣ ግልጽና ተደራሽ ያልሆነ የአቤቱታ ቅበላ ሥርዓት፤ እንዲሁም የተጎጂዎች ፍትሕ የማግኘት ሂደት አድካሚ፣ ረጅምና መጉላላት የበዛበት መሆኑ ይገኙበታል። በተጨማሪም የመረጃ አያያዝ፣ የቅብብሎሽ (Referral) ሥርዓት፣ የሥነ-ልቦና ድጋፍ አገልግሎቶች እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ውስንነት መኖር እንዲሁም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሠራር ደካማ መሆን በተግዳሮትነት ተጠቅሰዋል።

የኢሰመኮ የሴቶችና ሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር አሸነፈች አበበ፤ በርካታ ሴቶች ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች የሚደርስባቸውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ለመከላከል ነጻና ደኅንነቱ የተጠበቀ የመማሪያ አካባቢ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተቋቋሙ የሥርዓተ ጾታ ሥራ ክፍሎች የሴት ተማሪዎች መብቶችን በማስከበር እና ተጠያቂነትን በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው አስገንዝበዋል።