የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከመስከረም 2014 ዓ.ም. እስከ ነሐሴ 2014 ዓ.ም. ያለውን ጊዜ የሚሸፍን የሴቶችና የሕፃናት ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ባለ 36 ገጽ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል፡፡

ይህ ዓመታዊ የሴቶችና የሕፃናት መብቶች የዘርፍ ሪፖርት ኢሰመኮ ሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ ካደረገው አጠቃላይ የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት በተጨማሪነት በተለይ የሴቶችና የሕፃናት ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ በዝርዝር በማተኮር ኮሚሽኑ የለያቸውን አበረታች እመርታዎችን፣ ዋና ዋና አሳሳቢ ጉዳዮችን እና ምክረ-ሃሳቦችን አካቷል፡፡ ኮሚሽኑ ሪፖርቱን ያዘጋጀው ባከናወናቸው ክትትሎች፣ ምርመራዎችና የመስክ ምልከታዎች፣ ባስተናገዳቸው የግለሰቦች አቤቱታዎች፣ የሕግና የፖሊሲ ግምገማዎች፣ ጥናቶች እና ምክክሮች፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እንዲሁም የውትወታ እና ሌሎች ሥራዎቹ ላይ በመመስረት ነው። 

የሴቶችና የሕፃናት ሰብአዊ መብቶችን ከማስጠበቅ እና ከማስፋፋት አንፃር በሕግ ረገድ የታዩ ክፍተቶች፣ የሴቶችና የሕፃናት ከጥቃት እና ከብዝበዛ የመጠበቅ፣ ፍትሕ እና ውጤታማ መፍትሔ የማግኘት፣ ሕዝባዊ ተሳትፎ የማድረግ፣ በፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ያለው አያያዝ፣ የቤተሰብ መብቶች እንዲሁም የሴት ሠራተኞች ሁኔታ ሪፖርቱ ትኩረት ያደረገባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው።

በኢትዮጵያ በተከሰቱት ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት ሕፃናት ከመንግሥት፣ ከማኅበረሰብ እና ከቤተሰብ ማግኘት ያለባቸው ጥበቃ በመጓደሉ ለተደራራቢ የመብቶች ጥሰት መጋለጣቸው እና ሴቶች በተፈጸሙባቸው ጾታዊ መድሎዎችና ጥቃቶች ምክንያት መሰረታዊ መብቶቻቸውን የሚጥሱ፣ ነጻነቶቻቸውን የሚገድቡ እንዲሁም ሰብአዊ ክብራቸውን የሚያጎድፉ በደሎች እንደደረሱባቸው በሪፖርቱ ተገልጿል። በተጨማሪም በብሔራዊ የሕግ ማዕቀፍ ውስጥም ለሕፃናትና ለሴቶች ሰብአዊ መብቶች በቂ የሕግ ከለላ በመስጠት ረገድ የተለያዩ ክፍተቶች መስተዋላቸው ተጠቅሷል።

በኢትዮጵያ የሰሜኑ ክፍል በተነሳው ጦርነትና ቀጥሎም በየመሀሉ ማገርሸቱ በሴቶች እና በሕፃናት ላይ መጠነ-ሰፊ ጥቃቶች፤ በአንዳንድ ሁኔታዎች ለጦርነት ዓላማ ስልታዊ በሆነ መልኩ ጭምርም መፈጸማቸውን ተዘግቧል። ይሁን እንጂ ለተፈጸሙ ጥቃቶች ውጤታማ ፍትሕ እና መፍትሔ የሚያስገኝ የወንጀልና የፍትሐ-ብሔር የሕግ ማዕቀፍ አለመኖር፣ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን ያሟላ የወንጀል ምርመራና የክስ አመሰራረት መጓደል በሪፖርቱ ከተዘረዘሩት ዋና ዋና አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል ናቸው። በሌላም በኩል በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሶማሌ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልሎች በተለያየ ወቅት በተነሱ ግጭቶችም ሴቶችና ሕፃናት ለተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መጋለጣቸው ተጠቅሷል። 

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶችና ሕፃናት ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸው፣ በተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥም ለጾታዊ ጥቃቶች እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ተጋላጭ መሆናቸውና ልዩ ፍላጎታቸውን መሰረት ያደረጉ የሰብአዊ ድጋፎች አለማግኘታቸው ተደራራቢ የመብቶች ጥሰትን አስከትሏል። በሀገሪቱ በተከሰቱ የኮቪድ ወረርሽኝ፣ ድርቅ፣ ጦርነትና ግጭት ሳቢያ የትምህርት እና የጤና አገልግሎቶች በመቋረጣቸው፣ ወይም የተለያዩ ገደቦች መኖራቸው በሴቶችና ሕፃናት ትምህርትና ጤና የማግኘት መሰረታዊ መብቶች ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደራቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል። እንዲሁም ሴቶችና ሕፃናት ለሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ለብዝበዛ መጋለጥ፣ በኢንደስትሪ ፓርኮች የሚሠሩ ሴት ሠራተኞች መሰረታዊ መብቶች ጥሰቶች መቀጠል እና በእነዚህ የመብቶች ጥሰት ረገድ የቁጥጥርና የተጠያቂነት መላላት ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑ በሪፖርቱ ።

በሕዝባዊ ጉዳዮች ላይ ከመሳተፍ መብት ጋር በተያያዘም፣ ሕፃናት በማናቸውም ጉዳይ ላይ ሃሳባቸውን በነፃ የመግለጽና በሚመለከታቸው ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ የማድረግ መብታቸውን ለመተግበር የሚያስችል ሕግ አለመኖር፤ ሴቶችም በምርጫና በፖለቲካ ውስጥ ውጤታማ ተሳትፎ እንዳያደርጉ የአመለካከት ችግሮች እና ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እክል መፍጠራቸው፤ እንዲሁም በሰላም ግንባታ እና በሀገራዊ ምክክር እና ሌሎች የሕዝባዊ ውይይት መዋቅሮች ውስጥም ጾታዊ አካታችነት በእጅጉ ውስን በመሆኑ፣ የሴቶች ተሳትፎ ተገድቧል፡፡ 

ከወንጀል ጉዳይ ጋር በተያያዘ በፍትሕ ሥርዓት ውስጥ የሚያልፉ ልጆች አያያዝ ከሕፃናት ፍትሕ መርሆዎችና መመዘኛዎች ውጪ መሆን፣ በወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ ሴቶች ሁኔታ ከመሰረታዊ የሴት እስረኞች አያያዝ መስፈርቶች ጋር አለመጣጣም፣ ከእናቶቻቸው ጋር በእስር ቤት የሚቆዩ ሕፃናት ትምህርትና አማራጭ እንክብካቤ የማግኘት መብቶች መጓደል፣ በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ያሉ ክፍተቶች በሪፖርቱ ከተለዩ ጉድለቶች መካከል ናቸው። ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መስፈርቶች ጋር በተጣጣመ ሁኔታ ለሕፃናት ነፃና ለሁሉ ተደራሽ የሆነ የልደት ምዝገባ አሠራር በሀገር አቀፍ ደረጃ በሕግ አለመደንገጉ እንዲሁም በተወሰኑ ክልሎች ደግሞ የቤተሰብ ሕግ አለመውጣቱ ከተስተዋሉት የሕግ ክፍተቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የደኅንነት ሥጋቶች መቀጠላቸው የሴቶችን እና ሕፃናትን ሁኔታ በሚፈለገው ቅርበት እና ፍጥነት ለመከታተል እንዳይቻል እንቅፋት የፈጠረ መሆኑ፣ በእነዚህ አካባቢዎች የሚሠሩ የሲቪል ማኅበራት እና አጋሮች አቅምም መዳከሙና በኮሚሽኑ የሚሰጡ ምክረ ሃሳቦችን ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ በቅንጅት ለመሥራት የሚያስችል ጠንካራ የጋራ መድረክ አለመኖር ፈታኝ ሁኔታ መፍጠሩም ተጠቁሟል፡፡

የኢሰመኮ የሴቶችና የሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ የሴቶችንና የሕፃናት መብቶችን በተመለከተ ኮሚሽኑ ባከናወናቸው ክትትሎች፣ ምክክሮች እና የተለያዩ ክንውኖች ትብብር በማድረግ እና ግብዓት በመስጠት ኃላፊነታቸውን ለተወጡ መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበው በኢትዮጵያ ለሚገኙ ሕፃናትና ሴቶች ከግጭት፣ ከጥቃትና ከመድልዎ ነፃ የሆነ፤ ዘላቂ ሰላምና እኩልነት የሰፈነበት ሕይወትን እውን ለማድረግ በሪፖርቱ የተካተቱትን ምክረ-ሃሳቦች በመፈጸምና በማስፈጸም የተቀናጀ ጥረት እና ርብርብ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

ኮሚሽነር መስከረም አክለውም “ሰብአዊ መብቶችን ማክበር፣ ማስጠበቅ እና ማሟላት የመንግሥት ዋነኛ ግዴታ በመሆኑ የሕግ ማዕቀፎችን፣ ተቋማትን እና አሠራሮችን በማሻሻል፣ ፍትሕን ተደራሽ በማድረግ፣ በግጭቶች የወደሙ የትምህርትና የጤና ተቋማትን እና ሌሎች መሰረተ-ልማቶችን መልሶ በመገንባት እና ለተጎጂዎች ሁለንተናዊ ተሐድሶን በማመቻቸት የሕፃናትንና የሴቶችን ሰብአዊ መብቶች የማሻሻል ኃላፊነቱን መወጣት አለበት። በተጨማሪም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላትና ጠቅላላ ማህበረሰቡ በሰብአዊ መብቶች ማዕቀፍ በተቀመጠው አግባብ በሀገሪቱ የሴቶችና የሕፃናት መብቶች አፈጻጸምን በማረጋገጥ ረገድ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቀርባለሁ” ብለዋል።

ሙሉ ሪፖርቱ እዚህ ተያይዟል