የኢትዮጵያ ሰበአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለመስክ ጉብኝት ግንቦት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ መሥሪያ ቤት የተገኙትን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተቀብሎ አሰተናግዷል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው የመስክ ጉብኝት ኮሚሽኑ ይበልጥ ተደራሽ ወደሆነው አድራሻው ከተዛወረ ወዲህ እና ኮሚቴውም በአዲስ መልኩ ከተዋቀረ በኋላ የተደረገ የመጀመሪያው ጉብኝት ነው። በጉብኝቱ ወቅት የተለያዩ የኮሚሽኑ የሥራ ዘርፍ ኀላፊዎች እና ባለሙያዎች ስለ ኮሚሽኑ አደረጃጀት፣ የሥራ አካባቢ እና የሚያከናውኗቸው ተግባራትን የሚያስገነዝብ ገለጻ አድርገዋል፡፡ የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው በገለጻው ወቅት የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት ከባለሙያዎቹ ጋር ተወያይተዋል።
የኮሚቴው አባላት ከኮሚሽኑ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ጋር በተወያዩበት ወቅት ኮሚሽኑ አሳሳቢነታቸው ቀጥሏል በማለት የ9ወር የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱ ለኮሚቴው ባቀረበበት ወቅት ያደረገውን አጭር የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ገለጻ አስታውሶ ስለ ተቋሙ ተቋማዊ እና የሰው ሀብት አደረጃጀት፣ የተሰጡትን ኀላፊነቶች ለመወጣት ኮሚሽኑ የሚያደርገውን ጥረት አስረድቷል።
ኮሚሽኑእያከናወነ ያለው ሥራ የሚበረታታ መሆኑን የገለጹት የቋሚ ኮሚቴው አባላት መሻሻል ያስፈልጋቸዋል በማለት የለዩአቸውን ጉዳዮች ከምክረ ሐሳቦች ጋር አያይዘው ለኮሚሽኑ ከፍተኛ ኅላፊዎች አካፍለዋል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የቋሚ ኮሚቴ አባላቱን እንኳን ደኅና መጣችሁ ለማለት ባስተላለፉት መልእክት “ጉብኝቱ ኮሚሽናችን ተጠሪነቱ ለምክር ቤቱ ብቻ ስለሆነም ሳይሆን፣ የኮሚሽኑን ምክረ ሐሳቦች አፈጻጸም በአስፈጻሚው አካል ዘንድ ክትትል በማድረግ የምክር ቤቱን ተጨማሪ ድጋፍ በማግኘት ረገድ የሚረዳ በመሆኑ ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጠው ነው” ብለዋል። ዋና ኮሚሽነሩ አያይዘውም በርካታ ትኩረት የሚሹ አስቸኳይ የሰብአዊ መብቶች ሥጋቶች፣ አሳሳቢ ጉዳዮች እና ጥሰቶች እንዳሉ መጥቀሳቸውን አስታውሰዋል።
የዘፈቀደ እስርና ተገቢ ያልሆነ አያያዝ መበራከት፣ ተመጣጣኝ ያልሆነ የኀይል አጠቃቀም፣ ሕጋዊ ሂደትን ያልተከተለ የቤቶች ፈረሳ እና በግዳጅ ማስነሳት፣ በሚዲያና ተቃዋሚዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃትን እንዲሁም የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ሁኔታ ለአብነት በማንሳት በዝርዝር አብራርተዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ እውነቱ አለነ በበኩላቸው አንዳንድ የኮሚሽኑ የሰው ሀብት አስተዳደር ተሞክሮዎች ዐቅም በፈቀደ መጠን በሌሎች ተቋማት ጭምር ቢተገበሩ መልካም ነው ብለዋል አክለውም ኮሚሽኑ ከአስፈጻሚው አካልም ሆነ ሌሎች ሥራውን ለማከናወን ወይም የምክረ ሐሳቦቹን ተፈጻሚነት ለመከታተል አዳጋች ሁኔታዎች ቢገጥሙት ቋሚ ኮሚቴው ሕጉ እና ዐቅም እስከፈቀደ ድረስ ኮሚሽኑን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።