የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በመተባበር ለስደተኞች፣ ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ለፍልሰተኞች ማንነታቸውን የሚገልጹ እና መብቶቻቸውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልጉ ሰነዶች ተደራሽነትን በተመለከተ ታኅሣሥ 7 እና 8 ቀን 2017 ዓ.ም. ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዲስ አበባ ከተማ ተወያይቷል። በመድረኩ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌዴራል እና የክልል መንግሥት ተቋማት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲሁም የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ተወካዮች ተሳትፈዋል።

በውይይት መድረኩ ኢሰመኮ ያከናወናቸውን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ክትትሎች መሠረት በማድረግ፤ ሰነድ የማግኘት መብት ከስደተኞች፣ ከሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች እንዲሁም ፍልሰተኞች መብቶች አንጻር ምን ማለት እንደሆነ፣ ሰነዶቹን ባለማግኘታቸው የሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች፣  ሰነዶችን ተደራሽ ከማድረግ አንጻር የመንግሥት ግዴታ፤ እንዲሁም ስለ ብሔራዊ መታወቂያ ምንነት፣ ተዛማጅ የሕግ ማዕቀፎች፣ ከባለመብቶች አንጻር ያለው ጠቀሜታ የሚገልጽ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች ማንነታቸውን የሚገልጹ እና መብቶቻቸውን ለመተግበር የሚያግዟቸውን ሌሎች ሰነዶች ባለማግኘታቸው ምክንያት በተጨባጭ የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች በተመለከተ ለተሳታፊዎች አቅርበዋል። ሰነዶቹን ተደራሽ ለማድረግ በፌዴራል እና በክልል ደረጃ ያሉ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ያላቸው ሚና ላይ ምክረ ሐሳብ ቀርቧል። በዚህም መሠረት ሰነዶች ባለማግኘታቸው ምክንያት የመታወቅ መብታቸው መጓደሉ ሌሎች መብቶቻቸውን ለማስከበር የሚከናወኑ ሥራዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ በመሆኑ መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባ ተጠቅሷል።

ከዚህም ሌላ የብሔራዊ መታወቂያን በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ የሚከናወኑ ተግባራት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ተጠልለው የሚገኙባቸው ቦታዎች አብዛኞቹ ከከተማ ራቅ ያሉ ቦታዎች በመሆናቸው የአካባቢያዊና የቋንቋ ተደራሽነት ሁኔታ ከግንዛቤ እንዲገባ፣ ብሔራዊ መታወቂያ ሌሎች ማንነትን የሚገልጹ ሰነዶችን የሚተካ ባለመሆኑ ለስደተኞች፣ ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ ለጥገኝነት ጠያቂዎች እንዲሁም ፍልሰተኞች መብቶች በአግባቡ መተግበር አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶች ተደራሽነት ሊረጋገጥ እንደሚገባ እና ባለድርሻ አካላት የሰነዶቹን ጠቀሜታ በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ተነስቷል፡፡

የኢሰመኮ የስደተኞች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና የፍልሰተኞች መብቶች ዳይሬክተር እንጉዳይ መስቀሌ በውይይቱ ተሳታፊዎች ስደተኞችን በሚመለከት የተነሱ ችግሮችን የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት እንዲያጣራ እና መፍትሔ እንዲሰጥ ሐሳብ አቅርበው መብቶችን ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶችን ተደራሽ የማድረግ ሂደት የሰብአዊ መብቶች መስፈርቶችን መሠረት ያደረገ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። አያይዘውም ስደተኞች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ ጥገኝነት ጠያቂዎች እና ፍልሰተኞች መብቶቻቸውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልጓቸው ሰነዶች ተደራሽ እንዲሆኑ ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።