የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የታራሚዎች እና የተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝን አስመልክቶ በ2017 ዓ.ም. ባከናወነው ክትትል የተለዩ ግኝቶች እና በ2016 ዓ.ም. ለክልሉ የሰጣቸው ምክረ ሐሳቦች አፈጻጸም ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሐምሌ 6 ቀን 2017 ዓ.ም. በጅማ ከተማ ውይይት አካሂዷል። የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤን ጭምሮ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት፣ የዐቃቤ ሕግ ኃላፊ፣ የፖሊስ እና የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነሮች እና በፍትሕ ዘርፍ ላይ የሚሠሩ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በውይይቱ ተሳትፈዋል።

በመድረኩ ኢሰመኮ በ2016 ዓ.ም. ባከናወነው ክትትል መሠረት ለክልሉ ፖሊስ እና ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን የሰጣቸው ምክረ ሐሳቦች አፈጻጸም ሪፖርት በሥራ ኃላፊዎች ቀርቧል። የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ አበረታች ሁኔታ መኖሩ የተመላከተ ሲሆን ለመተግበር ጊዜ የሚፈልጉ ምክረ ሐሳቦችንም አስፈላጊውን ሁኔታ በማሟላት ለመፈጸም ቅድመ ዝግጀት መኖሩ ተመላክቷል።

በ2017 ዓ.ም. በፖሊስ እና በማረሚያ ቤቶች የተከናወነ የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሪፖርትም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። በዚህም መሠረት በተወሰኑ ማረሚያ ቤቶች የመኝታ ክፍሎች ግንባታ መጀመሩ፣ ትምህርት ቤት መከፈቱ፣ የመድኃኒት፣ የጤና እና የውሃ አቅርቦት መሻሻሉ፣ በሁሉም ማረሚያ ቤቶች ተጨማሪ የጤና ባለሙያዎች መቀጠራቸው፣ የቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት መጀመሩ በአበረታችነት የተለዩ ግኝቶች ናችው። በተጨማሪም የይቅርታ መመሪያው ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የይቅርታ መመሪያ ጋር በሚጣጣም መልኩ ተሻሽሎ መቅረቡ፣ የአመክሮ አስጣጥ ሂደቱን የሚገመግሙ ኮሚቴዎች መቋቋም እንዲሁም ከአካባቢያቸው ርቀው የሚገኙ ታራሚዎች በስልክ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ ለማድረግ ጅምር ሥራዎች መኖራቸው መሻሻል ከታየባቸው ጉዳዮች መካከል መሆናቸው ተመላክቷል።

በሌላ በኩል የታራሚዎች ምግብ በቂ እና ተመጣጣኝ አለመሆኑ፣ የመድኃኒት አቅርቦት ችግር፣ ታራሚዎችን በፈርጅ ለይቶ አለመያዝ፤ የተደራጀ የታራሚዎች መረጃ አያያዝ አለመኖር፣ ከእናቶቻቸው ጋር በማረሚያ ቤት ለሚኖሩ ሕፃናት፣ ለሚያጠቡና ነፍሰ-ጡር እናቶች እንዲሁም ለአካል ጉዳተኛና የአእምሮ ሕመም ላለባቸው ታራሚዎች ተገቢው እንክብካቤና ተመጣጠኝ ማመቻቸት አለመኖር፣ የመኝታ ችግሮች፣ የሥራ ዕድል እና መዝናኛ አማራጮች ለሴት ታራሚዎች ተደራሽ አለመሆኑ በማረሚያ ቤቶቹ የቀጠሉ ክፍተቶች መሆናቸው ተጠቅሷል።

በተጨማሪም በፖሊስ ጣቢያዎች ላይ በተደረገ ክትትል ሥልታዊ የሆነ ኢ-ሰብአዊ አያያዝ አለመኖሩ፣ የሚሰጡ ምክረ ሐሳቦችን ተቀብሎ ለመፈጸም ዝግጁነት መኖሩ እና የተጠርጣሪዎች ጉብኝት ክልከላ የማይደረግበት መሆኑ በጠንካራ ጎን የተነሱ ናቸው። ተጠርጣሪዎችን ያለፍርድ ቤት ፈቃድ እና መጥሪያ መያዝ፣ በተወሰኑ ፖሊስ ጣቢያዎች ሕገወጥ እስር መኖሩ፣ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር በሚውሉበት ጊዜ ድብደባ የሚፈጸም መሆኑ፣ ለተጠርጣሪዎች በጉብኝት ወቅት በሚስጥር የሚገናኙበት ስፍራ አለመዘጋጀቱ፣ በምርመራ ወቅት የተጠረጠሩበት ወንጀልና ተጠርጣሪዎች ያላቸው መብቶች በወንጀል መርማሪዎች በግልጽ አለመነገሩ፣ ዐቅም ለሌላቸው ተጠርጣሪዎች ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት እንዲያገኙ የተመቻቸ ሁኔታ አለመኖሩ፣ የሴት እና ወንድ ተጠርጣሪዎች ማቆያ ክፍሎች በአጥር አለመለየቱ፣ የማረፊያ ክፍሎች፣ የምግብ እና የውሃ አቅርቦት ጥራትና እጥረት መኖሩ እንዲሁም ልዩ ትኩረት የሚሹ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ያማከለ አሠራር አለመኖሩ የሚሉት ሊስተካከሉ ከሚገባቸው ግኝቶች መካከል የተጠቀሱ ናቸው።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ከዚህ ቀደም በኢሰመኮ የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን በመፈጸም ያሳዩትን ምላሽ በማጠናከር በቀጣይም ለክልሉ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ መሻሻል በትጋት እንደሚሠሩ ገልጸዋል። በተጨማሪም ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መፈጸም ምክንያት የሆኑ የዕውቀት፣ የክህሎት እና ግንዛቤ ክፍተቶች በመኖራቸው ኢሰመኮ በታራሚዎችና ተጠርጣሪዎች አያያዝ ላይ የሰብአዊ መብቶች ሥልጠና በመስጠት የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የተከበሩ ወንድሙ ኩርታ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ የተከበሩ ወንድሙ ኩርታ፣ በመልካም አፈጻጸም የተጠቀሱ ተግባራትን ይበልጥ በማጠናክር ኢሰመኮ በክፍተትነት ያቀረባቸውን ግኝቶች ለማሻሻል ጉዳዩ የሚመለከታቸዉ የሥራ ኃላፊዎች የየድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበው የክልሉ ምክር ቤት የሚጠበቅበትን ድርሻ እንደሚወጣ፤ የድጋፍና ክትትል ሥራዎችንም እንደሚያከናውን ገልጸዋል።

ዶ/ር አብዲ ጅብሪል፣ የኢሰመኮ የሲቪልና ፖለቲካ፤ የማኅበራዊ እና የኢኮኖሚ መብቶች ኮሚሽነር

የኢሰመኮ የሲቪልና ፖለቲካ፤ የማኅበራዊ እና የኢኮኖሚ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል የውይይቱ ተሳታፊዎች የሚሰጡ ምክረ ሐሳቦችን ለመፈጸም ላሳዩት ቁርጠኝነት ምስጋና አቅርበዋል። አክለውም ሰብአዊ መብቶች ባህል የሆኑበት ክልል በመፍጠር ረገድ መልካም አፈጻጸሞችን ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል ወሳኝ መሆኑን አስታውሰው፤ ከተሳታፊዎች የተነሱ የዕውቀት፣ የግንዛቤ እና የክህሎት ክፍተቶችን ለመቅረፍ ኢሰመኮ የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።