የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች ምቹ መሆናቸውን እና የተማሪዎች የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ሁኔታን አስመልክቶ በአዲስ አበባ፣ አፋር፣ አማራ፣ ጋምቤላ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች በሚገኙ 61 የመንግሥት እና የግል 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ባደረገው ክትትል የተለዩ ግኝቶች እና ምክረ ሐሳቦች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ነሐሴ 27 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የውይይት መድረክ አካሂዷል። በውይይቱ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የክልሎች የትምህርት እና የገንዘብና ኢኮኖሚ ቢሮ ኃላፊዎችና ተወካዮች እንዲሁም የትምህርት ቤቶች ርዕሰ መምህራን ተሳትፈዋል።

በመድረኩ ኢሰመኮ በክትትሉ የለያቸው ቁልፍ እመርታዎች፣ አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። በአብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች የመጠጥ እና የንጽሕና መጠበቂያ ውሃ እና በጾታ የተለዩ መጸዳጃ ቤቶች መኖር፣ ከጤና ተቋማት ጋር በሽታ የመከላከልና ክትባት የመስጠት ሥራዎች የሚከናወን መሆኑ፣ የተማሪዎች እና የሠራተኞች የሥነ ምግባር ደንብ መኖር እንዲሁም በአብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ሴት ተማሪዎች እኩል ተሳትፎ እንዲኖራቸው ጥረት መደረጉ ክትትሉ በአበረታችነት ከለያቸው ጉዳዮች መካከል ናቸው።

የውይይቱ ተሳታፊዎች

በሌላ በኩል በአብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ምቹ ባልሆነና በተጨናነቀ ሁኔታ የሚማሩ መሆናቸው፣ በበርካታ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች የመጀመሪያ እርዳታ የሚያገኙበት የጤና ክፍል (ክሊኒክ) አለመኖር፣ የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና ቁሳቁስ (First Aid kit) እና የጤና ባለሙያ እጥረት፣ የተለየ እንክብካቤ የሚፈልጉ የጤና ችግር ያለባቸው እና በተከታታይነት የሚወሰድ መድኃኒት የሚወስዱ ተማሪዎችን መረጃ በመያዝ ወጥ የሆነ ድጋፍ እንዲያገኙ ከማድረግ አንጻር ክፍተት መኖሩ፣ የተሟላ እና ለሕፃናት ምቹ የሆነ የሥነ አእምሮ ጤና፣ የሥነ-ተዋልዶ የግንዛቤ ትምህርት እና ሌሎች የምክር አገልግሎቶች አለመኖር፣ ከትምህርት ቤት ውጪ በተማሪዎች መካከል የሚፈጠሩ የእርስ በርስ ግጭቶች እና የቡድን ጸቦች በአብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች እየተበራከቱ መምጣታቸው የተስተዋሉ ተግዳሮቶች ናቸው።

በተጨማሪም በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በታጣቂዎች እና በመንግሥት የጸጥታ አካላት መካከል የቀጠሉ ግጭቶች በተማሪዎች ላይ ሥጋት የፈጠሩ መሆናቸው፣ በጥቂት ትምህርት ቤቶች ሕፃናት አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳትን የሚያስከትሉ ቅጣቶች መኖራቸው፣ ዛቻ፣ ማስፈራራት እና ጾታዊ ትንኮሳዎች በሴት ተማሪዎች ላይ በመምህራን እና በተማሪዎች የሚፈጸም መሆኑ፣ በሁሉም ክትትል በተደረገባቸው ትምህርት ቤቶች የሕፃናት ጥበቃ እና የጸረ መድልዎ ፖሊሲዎች አለመኖር፣ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች አካባቢ ጫት፣ ሺሻ እና ፑል ቤቶች መበራከት፣ እንዲሁም ለሕፃናት ምቹ የሆነ የተማሪዎች የቅሬታ መቀበያ ሥርዓት አለመኖር በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳደሩ አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች መሆናቸው ተገልጿል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች

የውይይቱ ተሳታፊዎች ሕፃናት ምቹ እና ሰብአዊ መብቶቻቸውን ያከበረ የትምህርት አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ የትምህርት ግብዓት አቅርቦቶችን በማሟላት እንዲሁም በዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና ብሔራዊ ሕጎች የታወቁ የሕፃናት መብቶች መከበራቸውን በማረጋገጥ ረገድ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በቅንጅት ሊሠሩ እንደሚገባ ገልጸዋል። በተጨማሪም በኢሰመኮ የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ ለመፈጸም የሚያግዝ የድርጊት መርኃ ግብር አዘጋጅተዋል።
የኢሰመኮ የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ሰላማዊት ግርማይ የውይይቱ ተሳታፊዎች የሕፃናት መብቶችን የማስጠበቅ ግዴታ የመንግሥት መሆኑን ከግምት በማስገባት በድርጊት መርኃ ግብር ያቀዷቸውን ተግባራት ትኩረት ሰጥተው እንዲተገብሩ አሳስበዋል። አክለውም ምቹ እና የሕፃናትን ሰብአዊ መብቶች ያከበረ የትምህርት አሰጣጥ ሂደት እንዲረጋገጥ ኢሰመኮ የሚያካሂደውን የውትወታ ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።