የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የሰብአዊ መብቶች ክበባት በትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዲስፋፉ እና በንቃት እንዲንቀሳቀሱ ለማስቻል በተዘጋጀ የአደረጃጀት እና የአሠራር ረቂቅ መምሪያ ላይ መስከረም 13 እና 14 ቀን 2018 ዓ.ም. ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ የትምህርት ሚኒስቴር እና የክልል ትምህርት ቢሮ የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች፣ የተማሪዎች ተወካዮች እንዲሁም በትምህርት ዘርፍ ውስጥ የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር በሰኔ ወር 2015 ዓ.ም. ያወጣው እና በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ተፈጻሚ በሆነው የተጓዳኝ ትምህርት አደረጃጀት አና አተገባበር መመሪያ መሠረት በትምህርት ቤቶች መቋቋም ከሚችሉ ክበባት መካከል የሰብአዊ መብቶች ክበብ አንዱ ነው። በዚሁ መሠረት የሰብአዊ መብቶች ዕውቀት እና አመለካከት በትምህርት ቤት ማኅበረሰብ ዘንድ እንዲጎለብት ኢሰመኮ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የሰብአዊ መብቶች ክበባት አደረጃጀት እና አሠራር ረቂቅ መምሪያ እና ክበባቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ተሰጥቷቸው ከሚከበሩ ቀናት ጋር በማገናኘት የሚያከናውኗቸው ተግባራትን የሚዘረዝር ረቂቅ አጋዥ ሰነድ አዘጋጅቶ ለውይይት አቅርቧል።


በመድረኩ የሰብአዊ መብቶች ክበባትን በትምህርት ቤቶች የማቋቋም አስፈላጊነት እና ዓላማ፣ ክበባቱ የሚመሩባቸው መርሖች፣ የተፈጻሚነት ወሰን፣ የክበባቱ አደረጃጀት እና አመራር፣ ዋና ዋና ተግባራት እና የማስፈጸሚያ ስልቶች እንዲሁም ክበባቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት እና የመሳሰሉት ጉዳዮች የተነሱ ሲሆን የኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲ እና የተጓዳኝ ትምህርት አስፈላጊነት ሐሳብ ቀርቦ ውይይት ተካሄዷል።
በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሰብአዊ መብቶች ክበባትን ማቋቋም ተማሪዎች ስለእኩልነት፣ አካታችነት፣ የሰው ልጅ ክብር፣ መቻቻል እና ሌሎች የሰብአዊ መብቶች እሴቶች እና መርሖች ያላቸውን ግንዛቤ እንዲያሳድጉ ከማስቻሉ በተጨማሪ በክፍል ውስጥ የተማሯቸውን የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ከክፍል ውጪ በተግባር እንዲለማመዱ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ተብሏል። ክበባቱ ተማሪዎች ስለሰብአዊ መብቶች መወያያና መማማሪያ መድረክ እንዲኖራቸው እንዲሁም በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ኃላፊነት የሚሰማቸው፣ መብትና ኃላፊነታቸውን የሚገነዘቡ፣ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ዕድል እንደሚሰጧቸውም አስተያየት ተሰጥቷል።

በትምህርት ሚኒስቴር የሥርዓተ ትምህርት ማበልጸጊያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ቴዎድሮስ ሸዋረገጥ በቅርቡ የተከናወነውን የሥርዓተ ትምህርት ለውጥ ተከትሎ በርካታ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች በግብረገብ እና ዜግነት ትምህርት ዐይነቶች እንደተካተቱ ገልጸው ተማሪዎች በተጓዳኝ ትምህርት ስለሰብአዊ መብቶች እንዲማሩ ማድረግ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር የስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ ዶ/ር ሚዛኔ አባተ ኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ትምህርትን በመደበኛ እና መደበኛ ባልሆኑ የትምህርት ሥርዓቶች ውስጥ በአግባቡ ለማካተት እና ለማጠናከር ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙን አስታውሰው፣ ይህንን ተከትሎ ሲያከናውናቸው ከቆዩ በርካታ ተግባራት መካከል በትምህርት ቤቶች አካባቢ ስለሰብአዊ መብቶች ዕውቀት እና ግንዛቤ እንዲስፋፋ ማድረግ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም ኢሰመኮ የተማሪዎችን የሰብአዊ መብቶች ግንዛቤ ለማሳደግ የሚያከናውናቸውን ዘርፈ ብዙ ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።