የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀን ጋር በማስተሳሰር በየዓመቱ የሚያካሂደው የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል 5ኛ ዙር የፎቶግራፍ እና የአጫጭር ፊልም ሥራዎች ውድድር ዛሬ ጥቅምት 4 ቀን 2018 ዓ.ም. በይፋ ተጀምሯል። ውድድሩ በኢሰመኮ የ2017 በጀት ዓመት የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ሪፖርት በከፍተኛ ደረጃ አሳሳቢ በመሆን ከተለዩት ጉዳዮች መካከል በነጻነት መብት እና በትምህርት መብት ላይ ያተኩራል።
ውድድሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚደረግ ሲሆን አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች የሚገኙ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች እንዲሳተፉ ተጋብዘዋል። ከግለሰቦች በተጨማሪ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ማለትም የመገናኛ ብዙኃን፣ የኮሙኒኬሽን፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ፣ የትምህርትና ስልጠና ድርጅቶች ወዘተ. በውድድሩ መሳተፍ ይችላሉ።
ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ በኢሰመኮ አዘጋጅነት የሚካሄደው ዓመታዊ ፊልም ፌስቲቫል ዓላማ በኪነ ጥበብ ሥራዎቻቸው ስለ ሰብአዊ መብቶች የሚያወሱ እና የሰብአዊ መብቶች መከበር፣ ጥበቃና መስፋፋትን የሚያበረታቱ ሰዎችን፣ ተቋማትን እና ድምፆችን ማሰባሰብ ነው። በተጨማሪም ፌስቲቫሉ ሰዎችን በአንድ ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ በማስተባበር በሰብአዊ መብቶች ላይ ግንዛቤ ማሳደግ እና በኪነጥበብ አማካኝነት ለተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችን ተደራሽ ለማድረግ ያለመ ነው።
ኢሰመኮ በዘንድሮው 5ኛ ዙር ፌስቲቫል ውድድር የሚሳተፉ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን እንዲሁም ዝግጅቶቹ የሚካሄዱባቸውን ከተሞች ብዛት በመጨመር የፎቶግራፍ እና የአጫጭር ፊልም ሥራዎች ውድድሮችን የሚያካሂድ ሲሆን ውድድሩም እስከ ኅዳር 3 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ ክፍት ሆኖ ይቆያል።
የፎቶግራፍ ውድድሩ ትኩረቱን ትምህርት በማግኘት መብት ላይ ሲያደርግ የአጫጭር ፊልም ሥራዎች ውድድር ደግሞ በነጻነት መብት ላይ የሚያተኩር ነው። የአጫጭር ፊልም ሥራዎች ውድድር በሁለት ምድብ ማለትም በጀማሪዎች (በተንቀሳቃሽ ስልኮች በመጠቀም የፊልም ሥራዎቻችውን ለውድድር በሚያቀርቡ) እና በባለሙያዎች ዘርፎች የሚደረጉ ናቸው። ለውድድር የሚቀርቡ የአጫጭር ፊልም ሥራዎች ለጀማሪዎች ከ5 እስከ 6 ደቂቃዎች ቆይታ፤ ለባለሙያዎች ደግሞ ከ10 እስከ 15 ደቂቃዎች ቆይታ ያላቸው ሊሆኑ ይገባል። በፎቶግራፍ እና በአጫጭር ፊልም ዘርፎች የሚቀርቡ የኪነጥበብ ሥራዎች ዘጋቢ፣ ምናባዊ ወይም እውነተኛ ታሪክ ላይ መሠረት ያደረጉ ሊሆኑ ይገባል።
ውድድሩ የፌስቲቫሉ ተሳታፊዎች የተመረጡት የሰብአዊ መብቶች መከበር ወይም መጣስ በሰዎች ሕይወት ላይ ያለውን አንድምታ የሚገልጹ፣ የተለያዩ ሐሳቦችን የሚሰጡ፣ ጥያቄዎችን የሚያጭሩ እና ለማሰላሰል የሚጋብዙ የኪነጥበብ ሥራዎችን የሚያቀርቡበት ይሆናል። ለውድድር የሚቀርቡ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ልዩ ትኩረት የሚሹ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ማለትም ሕፃናትን እና ታዳጊዎችን፣ ሴቶችን፣ አረጋውያንን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ወይም ስደተኞችን ማእከል እንዲያደርጉ ይጠበቃል።
በሦስቱም የኪነ ጥበብ ስራ ውድድሮች ለሚሳተፉ ሰዎች እና ተቋማት በሙሉ የዕውቅና ምስክር ወረቀት የሚሰጥ ሲሆን፣ በሁሉም ዘርፎች ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ የሚወጡ አሸናፊ የኪነጥበብ ሥራዎች ፌስቲቫሉ በአዲስ አበባ ከተማ በሚካሄድበት መድረክ የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ይወስዳሉ።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ኪነጥበብ በተለያየ ዕድሜ እና ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎችን ስለሰብአዊ መብቶች በቀላሉ እና ሁሌም ሊታወስ በሚችል መልኩ ለማስገንዘብ ያለውን ፋይዳ በመግለጽ፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች በሥራዎቻቸው የሰብአዊ መብቶች መጠበቅ ወይም መጣስ ያለውን ውጤት የሚያመላክቱ ምናባዊ ትዕይንቶችን በማካተት ሰብአዊ መብቶች ባህል የሚሆንበት ማኅበረሰብን በመፍጠር ሂደት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጠይቀዋል። አክለውም ኢሰመኮ ዘንድሮ ለሚያካሂደው 5ኛው ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል በተዘጋጀው የፎቶ ግራፍ እና የአጫጭር ፊልሞች ውድድር ክህሎት እና ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች እና ተቋማት በሙሉ እንዲሳተፉ ጋብዘው ለሁሉም መልካም ዕድል ተመኝተዋል።
ስለ ፌስቲቫሉ እና ውድድሩ ተጨማሪ ማብራሪያ እዚህ ተያይዟል።