የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከኢንተርናሽናል ሚዲያ ሰፖርት (International Media Support) ጋር በመተባበር በጋዜጠኞች የሕግ ጥበቃ (ከለላ) ላይ ጥቅምት 04 ቀን 2018 ዓ.ም. በአርባ ምንጭ ከተማ ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ ከማእከላዊ ኢትዮጵያ፣ ከሲዳማ እና ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የሕግ አስፈጻሚ አካላት እና ከግልና ከመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

መድረኩ ሐምሌ 17 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ የተካሄደው ውይይት ቀጣይ ሲሆን፣ ኢሰመኮ በመገናኛ ብዙኃን ነጻነት እና ሐሳብን በመግለጽ መብቶች ላይ ያከናወነው ክትትል ግኝቶች፣ የመብቶቹ መከበር ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ያለው ሚና፣ በመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚጣሉ ገደቦችና በአጠቃላይ በጋዜጠኞች መብቶች ጥበቃ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲሁም ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የተመለከቱ ዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ የሕግ ማዕቀፎች፣ በጋዜጠኞች የሕግ ጥበቃ (ከለላ) ላይ የተደረጉ የቅርብ ጊዜ ለውጦችና ክፍተቶች እና የመንግሥት ተቋማት ኃላፊነቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ቃልኪዳን ደረጄ፣ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ

የጥላቻ ንግግርን እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን እንዲሁም የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጡ አዋጆችን ሽፋን በማድረግ የሚፈጸሙ ክልከላዎች እና ገደቦች፣ የመገናኛ ብዙኃን አባላት ስለመብታቸውና ግዴታቸው ያላቸው ግንዛቤ ማነስ እንዲሁም የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ለተወሰኑ የመገናኛ ብዙኃን ብቻ መረጃ የመስጠት አዝማሚያ በተለይም የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ኃላፊዎች ለግል መገናኛ ብዙኃን መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆን በዘርፉ የታዩ ክፍተቶች መሆናቸው በውይይቱ ተነስቷል። በሌላ በኩል የጥላቻ ንግግሮችን፣ ሐሰተኛ መረጃዎችን እንዲሁም ግጭት የሚቀሰቅሱ መልእክቶችን የሚያሰራጩ መገናኛ ብዙኃንን መቆጣጠር አለመቻሉ፣ በበይነ-መረብ ላይ የሚጣሉ ገደቦች እና በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት ተፈጽሟል በተባለ ወንጀል ጋዜጠኞች ከሕግ ውጭ እስራት የሚፈጸምባቸው መሆኑ በውይይቱ ተነስቷል።

በዞን እና በወረዳ ደረጃ በሚንቀሳቀሱና ሕግ ተላልፈዋል በሚል በሚጠረጠሩ ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ላይ የሚደረጉ ምርመራዎች መዘግየት፣ የመርማሪ ፖሊሶች ዐቅም ማነስ እንዲሁም መብቱን በተመለከተ በቂ ግንዛቤ አለመኖር በዘርፉ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች መሆናቸው በውይይቱ ተጠቅሷል። ይህንን ችግር ለመፍታት በክልል ደረጃ ስልጠና እና የዐቅም ግንባታ ሥራዎችን ማከናወን አስፈላጊ መሆኑ እንዲሁም ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ከግዴታዎችና ኃላፊነቶች ጋር የሚመጣ መሆኑን በመገንዘብ ጋዜጠኞች የሀገር እና የሕዝብ ደኅንነትን ከመጠበቅ አኳያ የተቀመጡ ግዴታዎችን በማክበር እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ ቀርቧል።

የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና የኢኮኖሚ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ዋናው ምሰሶ መረጃ የማግኘት መብት መሆኑን በማንሳት የመብቱ መጠበቅ መረጃን ተደራሽ ከማድረግ በተጨማሪ በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎችን ለማረም የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም ሐሳብን በነጻነት መግለጽ መሠረታዊ እና በዘፈቀደ ገደብ የማይደረግበት ሰብአዊ መብት መሆኑን እና ጋዜጠኞች የኅብረተሰቡን መረጃ የማግኘት መብት ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ መሆናቸውን አስታውሰው “የተሟላ የሕግ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል” ብለዋል።