የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከታኅሣሥ 19 እስከ የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም. በማእከላዊ ኢትዮጵያ፣ በሲዳማ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ፍትሕ የማግኘት መብት ሁኔታን በተመለከተ ባደረገው ክትትል በለያቸው ግኝቶች ላይ ጥቅምት 5 ቀን 2018 ዓ.ም. ከባለድርሻ አካላት ጋር በአርባምንጭ ከተማ ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ የሦስቱ ክልሎች ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች እና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ተወካዮች፣ የመንግሥት ሠራተኞች አስተዳደር ፍርድ ቤቶች ተጠሪ ዳኞች፣ የክልልና የዞን የፍትሕ (ዐቃቤያነ ሕግ)፣ የፖሊስና ማረሚያ ተቋማት እንዲሁም የክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።




በመድረኩ ኢሰመኮ በሦስቱ ክልሎች ያለውን ፍትሕ የማግኘት መብት ሁኔታ አስመልክቶ ባከናወነው ክትትል የለያቸው አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችና ምክረ ሐሳቦች ቀርበዋል። በቁጥጥር ሥራ የዋሉ ተጠርጣሪዎችን በ48 ሰዓት ፍርድ ቤት ሳያቀርቡ ለተራዘመ ጊዜ በእስር ማቆየት እና አቤቱታቸውን ፍርድ ቤት እንዳያቀርቡ በፖሊስ የሚደረግ ክልከላ መኖሩ በውይይቱ ተገልጿል። በተለይም ‘ኮማንድ ፖስት’ በሚል ተግባራዊ በሚደረግ የሕግ ማስከበር እንቅስቃሴ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎችን መደበኛ ባልሆኑ ቦታዎች አስሮ ማቆየት፣ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች የሚያቀርቡት አካልን ነጻ የማውጣት አቤቱታ ፍርድ ቤቶች ሥልጣን የለንም በሚል የሚመልሱ መሆኑ አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ መሆኑ ተጠቅሷል።



በተጨማሪም በተጠርጣሪዎች ላይ የሚፈጸሙ የበቀል እርምጃዎችን፣ በፖሊስ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን እና በወንጀል የተጠረጠሩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ላይ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን ለመመርመር ፖሊስ ፈቃደኛ አለመሆኑ በክትትሉ የተለየ አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑ ተገልጿል። በጸጥታ ችግር ምክንያት የወደሙ ፍርድ ቤቶች በቶሎ ወደ ሥራ አለመመለሳቸው፣ የከፍተኛ ፍርድ ቤቶች አገልግሎት የተደራሽነት ችግር ያለበት መሆኑ፣ ፖሊስ በተለይም ጠለፋ የተፈጸመባቸውን ሴቶች አቤቱታ በአግባቡ አለማስተናገዱ፣ የዋስትና እና አካልን ነጻ የማውጣት አቤቱታ የማቅረብ መብትን የሚገድቡ ልማዳዊ አሠራሮች መኖራቸው፣ እንዲሁም ወንጀል ባልሆነ ጉዳይ የሚፈጸም እስር መኖሩ እናሰዎች ከእስር እንዲለቀቁ በፍርድ ቤት የሚሰጥ ትእዛዝ በፖሊስ አለመከበር እንዲሁም የአስተዳደር ፍርድ ቤቶች የመንግሥት ሠራተኞችን አቤቱታዎች ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆናቸው በአሳሳቢነት ከቀጠሉ ተግዳሮቶች መካከል መሆናቸው ተመላክቷል።


የውይይቱ ተሳታፊዎች በኢሰመኮ ክትትል የቀረቡ ግኝቶች በጸጥታ ችግሮች፣ በፍትሕ ባለሙያዎች እጥረት፣ በግንዛቤ ማነስና በልማድ ላይ በተመሠረቱ አሠራሮች፣ በትኩረት ማነስ፣ በፍትሕ አካላት መካከል ውጤታማ ቅንጅት ባለመኖሩ እና የፍትሕ አካላት የሥነ-ሥርዓት ሕጎችን ተከትለው በመሥራት ረገድ በሚፈጥሯቸው ክፍተቶች የተከሰቱ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን የቀጣይ ሥራ ዕቅድ አካል በማድረግ ለችግሩ ውጤታማ መፍትሔ ለመስጠት በትኩረት እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና የኢኮኖሚ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል ክትትሉ የተከናወነው ከዚህ ቀደም ለኢሰመኮ በቀረቡ ተደጋጋሚ አቤቱታዎች መሠረት መሆኑን እና የተወሰኑት ችግሮች ከዚህ ቀደም ኢሰመኮ ባወጣቸው ሌሎች ሪፖርቶች ላይ የተመላከቱ መሆኑን ጠቅሰዋል። በክትትሉ የተለዩ ችግሮችን ለመፍታትና የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የተፈጸመባቸው ሰዎች ውጤታማ ፍትሕ የሚያገኙበትን ሁኔታ ለመፍጠር ባለድርሻ አካላት በሕግ የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡም አሳስበዋል።