የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሚያዝያ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በአማራ ክልል የሚታየው የጸጥታ ችግር በተለይ ከነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም. ወዲህ ተስፋፍቶ ወደ ትጥቅ ግጭት ማምራቱን ተከትሎ፣ አጠቃላይ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታዎችን በቅርበት መከታተሉን ቀጥሏል፡፡

ግጭቱና የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች እርምጃዎች የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ላይ በተለይም በሲቪል ሰዎች ላይ እያደረሰ ያለውንና ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት አስመልክቶ በነሐሴ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ ማፈላለግን ጨምሮ በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመከላከል አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ ማሳሰቡ የሚታወስ ነው። በተጨማሪም ከሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ሥራ ላይ የዋለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሰብአዊ መብቶች ላይ ያለውን ተጽእኖ በመከታተል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ እና የአዋጁ መርማሪ ቦርድን ጨምሮ የሚመለከታቸውን የመንግሥትና የጸጥታ አካላትን በማነጋገርና ምክረ ሐሳቦች በመስጠት በቅርበት ክትትል በማድረግ ላይ ይገኛል።

ኮሚሽኑ ይህን መግለጫ ይፋ እስከአደረገበት ጊዜ ድረስ ባደረገው ክትትል መሠረት፤ በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች፣ ከሕግ/ፍርድ ውጭ የተፈጸሙ ግድያዎች እና የዘፈቀደ እስር እጅግ አሳሳቢ ሆነው ከተለዩ ጉዳዮች መካከል ናቸው፡፡

በተለይም በአማራ ክልል ኮሚሽኑ ከነዋሪዎች፣ ከተጎጂዎች፣ ከተጎጂ ቤተሰቦችና ከዐይን ምስክሮች ባሰባሰባቸው መረጃዎች መሠረት የትጥቅ ግጭቱ ወደ ክልሉ ልዩ ልዩ ወረዳዎች መስፋፋቱን ተረድቷል፤ በነዋሪዎች ላይ የሚያደርሰው ጉዳትም ተባብሶ ቀጥሏል። ለምሳሌ ከነሐሴ 19 እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ በተለይም በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረማርቆስ ከተማ፣ በሰሜን ጎጃም ዞን አዴትና መራዊ፣ በደቡብ ጎንደር ዞን ደብረታቦር፣ በማእከላዊ ጎንደር ዞን ደልጊ፣ በሰሜን ሸዋ ዞን ማጀቴ፣ ሸዋ ሮቢት እና አንጾኪያ ከተሞች እና በአካባቢዎቻቸው በሚገኙ አንዳንድ የገጠር ቀበሌዎች በግጭቱ ዐውድ በርካታ ሲቪል ሰዎች መሞታቸውን፣ ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን እና የንብረት ውድመት እንደደረሰባቸው ለመረዳት ተችሏል። በተኩስ ልውውጦች ወይም በከባድ መሣሪያ ተኩስ ከሚሞቱ ሰዎች መካከል በመንገድና በእርሻ ሥራ ላይ እንዲሁም በቤታቸው ውስጥ የነበሩ ሰዎች ጭምር የሚገኙ መሆኑን ቤተሰቦች እና የዐይን ምስክሮች ያስረዳሉ።

በዚሁ የግጭቱ ዐውድ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በመንግሥት የጸጥታ አካላት ከሕግ/ፍርድ ውጭ የተፈጸሙ ግድያዎች (extrajudicial killings) እጅግ አሳሳቢ ነው። ለምሳሌ ከሐምሌ 24 እስከ ጳጉሜን 4 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ በተለይም በአዴት፣ ደብረማረቆስ፣ በደብረ ታቦር፣ ጅጋ፣ ለሚ፣ ማጀቴ፣ መራዊ፣ መርጦ ለማርያምና ሸዋ ሮቢት ከተሞች ተስፋፍተው በተፈጸሙ ከሕግ/ፍርድ ውጪ የሆኑ ግድያዎች ሰለባ ከሆኑ ሰዎች መካከል ቤት ለቤት በተደረገ ፍተሻ የተያዙ ሰዎች፣ በግጭቱ ወቅት መንገድ ላይ የተገኙ እና ያልታጠቁ ሰዎች፣ “የጦር መሣሪያ ደብቃችኋል አምጡ” በሚል የተያዙ ሰዎች፣ የሰዓት እላፊ ገደቦችን ተላልፈው የተገኙ ሲቪል ሰዎችና በቁጥጥር ስር የዋሉ የታጣቂው ቡድን (በተለምዶ ፋኖ በመባል የሚታወቀው) አባላት የሚገኙበት ሲሆን፤ በኮሚሽኑ እና በአስቸኳይ ጊዜ መርማሪ ቦርዱ አማካኝነት የተሟላ ምርመራ ሊደረግበት የሚያስፈልግ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የአስቸኳይ ጊዜ መምሪያ ኮማንድ ፖስት በይፋ ካሳወቃቸው እስሮችና ቦታዎች ውጪ በተለይ በአማራ ክልል፣ በኦሮሚያ ክልል እና በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በአስቸኳይ ጊዜ ዐውዱ የተስፋፋና የዘፈቀደ እስር የተፈጸመ ሲሆን፣ ለምሳሌ በአማራ ክልል በባሕር ዳር፣ ደብረ ታቦር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ፍኖተ ሰላም፣ ጎንደር፣ ላሊበላ፣ መካነሰላም፣ ቆቦ እና ሸዋ ሮቢት ከተሞች፤ በኦሮሚያ ክልል በተለይ በሸገር ከተማ እና በአዲስ አበባ ከተማ የተፈጸሙ የዘፈቀደ እስሮች ይገኙበታል፡፡ ከእነዚህ ታሳሪዎች ውስጥ በደቡብ ክልል ፖሊስ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ግቢ (በተለምዶ አቦስቶ በመባል የሚታወቀው ቦታ) የነበሩ ታሳሪዎችን ጨምሮ ከተለያየ ጊዜ መጠን በኋላ የተለቀቁ መኖራቸውን ማወቅ የተቻለ ቢሆንም፤ በአንጻሩ ገና ቁጥራቸው በትክክል ያልታወቀ ሰዎች ይህ መግለጫ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በእስር ላይ ይገኛሉ። በመንግሥት የጸጥታ አካላት የሚታሰሩ ሰዎች በአብዛኛው “ለታጣቂ ቡድኑ ድጋፍ ታደርጋላችሁ” እና/ወይም “የጦር መሣሪያ ደብቃችኋል” በሚል ምክንያት ነው፡፡

በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ገላን ክፍለ ከተማ ውስጥ ሲዳ አዋሽ ወረዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው ጊዜያዊ ማቆያ ማእከልን በተመለከተ በዚህ ማእከል ውስጥ ተይዘው የነበሩ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፊትና በኋላም ከተለያዩ ክልሎች የመጡ ሕፃናትና ሴቶችን ጨምሮ በርካታ ውሏቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ ነዋሪዎች ከጎዳና ላይ ተነስተው እንዲቆዩ የሚደረግበት ቦታ መሆኑን፣ በቅርቡ ወደ ማእከሉ ከተወሰዱት ውስጥ 29 ሰዎች በመታወቂያ ካርዳቸው ተለይተው እንዲለቀቁ መደረጉን፣ የተወሰኑት ደግሞ በመልሶ ማቋቋም ፕሮግራም ወደየመጡበት አካባቢዎች እንዲመለሱ የተደረገ መሆኑን፣ በጣቢያው ውስጥ ተከስቶ የነበረው ተላላፊ በሽታ በቁጥጥር ስር የዋለ መሆኑን ኮሚሽኑ በክትትሉ ተመልክቷል። እንዲሁም የጎዳና ላይ ተዳዳሪዎችን በተለይም ሕፃናትን በተመለከተ በችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ላይ ከዚህ በፊትም ኮሚሽኑ ያቀረባቸውን ምክረ ሐሳቦች አፈጻጸም ክትትሉን ይቀጥላል፡፡

በኮማንድ ፖስቱ ትእዛዝ በእስር ላይ መሆናቸው ከሚታወቁት ሰዎችና ቦታዎች ውስጥ ኮሚሽኑ በአዋሽ አርባ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የምዕራብ ዕዝ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፕ ውስጥ ተይዘው የሚገኙትን ታሳሪዎች ነሐሴ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. መጎብኘቱና ማሳወቁ የሚታወስ ሲሆን፤ በሌሎቹም ቦታዎች ተመሳሳይ ክትትል ያደርጋል።

ስለሆነም ኢሰመኮ ከዚህ በፊትም ባቀረበው ጥሪ እንደገለጸው ግጭቱን በዘላቂነት ለመፍታት ላሉት ሰላማዊ አማራጮች በሙሉ ቅድሚያ መስጠትን ጨምሮ፤

  1. በየትኛውም ወገን የሚወሰዱ እርምጃዎች ሲቪል ሰዎችን ወይም የመሠረተ ልማቶችን ዒላማ ከማድረግ ሙሉ በሙሉ እንዲቆጠቡ፣ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዳይቋረጥ መከላከል ጨምሮ ለሲቪል ሰዎች ተገቢው ጥበቃ እንዲደረግ፤ በማናቸውም ሁኔታ ሊገደቡ የማይችሉ መብቶችን በተለይም በሕይወት የመኖር መብት እና ከኢ-ሰብአዊ አያያዝ የመጠበቅ መብት እንዲከበሩ፣
  2. በሲቨል ሰዎች ላይ ግድያ በፈጸሙና በዘፈቀደ እስራት ላይ በተሳተፉ አካላት ላይ አስፈላጊው ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ፣
  3. ከአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ ትእዛዝ ውጪ የታሰሩ ሰዎችን በሚመለከት ጉዳዩ በመደበኛው የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር መከናወኑ እንዲረጋገጥ፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት የታሰሩ ሰዎችም የተጠረጠሩበት ወንጀል ምርመራ በአስቸኳይ በማጠናቀቅ ፍትሕ የማግኘት መብታቸው እንዲረጋገጥ፣
  4. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለመተግበር የሚወሰዱ እርምጃዎች በሙሉ በተለይም እስራትና የሰዓት እላፊ ገደብ ማስፈጸም በአስፈላጊነት፣ ተመጣጣኝነት፣ ከአድልዎ ነጻ የመሆን እና ሕጋዊነት መሠረታዊ መርሖች እንዲመሩ እንዲደረግ ያሳስባል፡፡

የእንግሊዘኛውን ጋዜጣዊ መግለጫ ከዚህ በታች ያንብቡ ⬇️

Amhara Region: Concerning human rights violations in the context of the armed conflict