የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል



በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አዘጋጅነት ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ የሚካሄደው ይህ ዓመታዊ ፊልም ፌስቲቫል በእ.ኤ.አ. ታኅሣሥ 10 የሚውለውን ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ቀን የሚያስብ ነው። በተለያዩ የፊልም እና የኪነጥበብ ባለሞያዎች እገዛና ትብብር የሚዘጋጀው ይህ ፌስቲቫል፣ በሰዎች የዕለት ተለት ሕይወት ተጽዕኖ በሚያሳድሩ የሰብአዊ መብቶች ዙርያ የሚያጠነጥኑ አጫጭር ወይም ሙሉ (ፊቸር ፊልሞች)፣ ዘገባዎች ወይም ልብወለድ ይዘት ያላቸው ፊልሞች የሚታዩበት፣ ተመልካቾች ፊልሞቹን ካዘጋጁ ባለሞያዎች ጋር ወይም ከተዋንያን ጋር የሚወያዩበት፣ እንዲሁም የኮሚሽኑን የሰብአዊ መብቶች ሥራዎች የሚደግፉ አጋር ድርጅቶች እና ባለሞያዎች የሚሳተፉበት መድረክ ነው።

ዝግጅቱ የፌስቲቫል ቅርጽ የያዘ እንደመሆኑ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች በሚገኙ ሲኒማዎች ወይም መሰል ስፍራዎች የሚካሄድ ሲሆን፣ ከተለያዩ የሙያ ዘርፎች ባለሞያዎች፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የከፍተኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እንዲሁም ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች የሚገኙበት ነው። የሰብአዊ መብቶች ቀን ለማሰብ ያለመ እንደመሆኑ ዓመታዊ ፊልም ፌስቲቫሉ የፊልሞቹን ይዘት የዓመቱን የሰብአዊ መብቶች ቀን መሪ ቃል/መሪ ሐሳብ ከወቅታዊ ሀገራዊ ዐውድ ጋር በማጣጣም፣ ተሳታፊዎችን፣ ባለሞያዎችን እና ተመልካቾችን ከመደበኛ የስብሰባ፣ ስልጠና እና መሰል ዝግጅቶች ለየት ባለ መልኩ ስለሰብአዊ መብቶች እንዲወያዩ በመጋበዝ ግንዛቤ ወይም የሰብአዊ መብቶች እይታ የሚሰጥ ነው።

የሰብአዊ መብቶች ሥራ ዘርፈ ብዙ፣ ሁሉንም ሰዎች የሚመለከት፣ ሁሉን የዕለት ተዕለት ሕይወት ጎኖች ላይ ተጽዕኖ ያለው እንደመሆኑ የሁሉን ሰዎች ተሳትፎ፣ ድጋፍ እና ትብብር የሚጠይቅ ነው። ስለሆነም ሰዎች ስለመብቶችና ግዴታዎቻቸው ማወቅ፣ በሙያቸውም ሆነ በሌሎች መንገዶች “ሰብአዊ መብቶች ባህል የሆኑባት ኢትዮጵያን ማየት” የሚለውን የኢሰመኮን ራዕይ ለማሳካት የሚያደርጉትን አስተዋጽዖ መረዳት እና መተግበር ይኖርባቸዋል። በዚህ ረገድ ኮሚሽኑ በሕግ ከተጣሉበት ኃላፊነቶች መካከል የመገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም የሕዝቡን የሰብአዊ መብቶች ግንዛቤ እና እውቀት ማሳደግ የሚለው ዋነኛውና በልዩ ትኩረት የሚያከናውነው ተግባር ነው።

ኪነጥበብ በተደራሽነቱ፣ በፈጠራ አቅሙ፣ የተለያዩ ውስብስብ ጉዳዮችን በቀላሉ ለመረዳት በሚያስችል መልኩ በማቅረብ አቅሙ፣ እንዲሁም የሰዎችን ትኩረትና የማስታወስ ችሎታ በመጠቀም አቅሙ ትምህርትንና ግንዛቤን ለማስፋፋት ከሚያገለግሉ መንገዶች አንዱ ነው። በተጨማሪም የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር በሁለተኛው ዙር ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል መክፈቻ ባደረጉት ንግግር እንዳስታወሱት “የጥበብ ሥራዎች ወደውስጣችን እንድንመለከት የሚረዱ፣ አንድነት እና ሰብአዊነትን የሚያወሱ፣ እንዲሁም እርስ በእርስ መከባበርንና መዋደድን አስተማሪ ናቸው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል የመሳሰሉ መድረኮች የኪነጥበብ ሰዎችን ለተሻለ ራዕይ በማነሳሳት እና ለአንድ ዓላማ በማስተባበር ያለው ድርሻ ከፍተኛ ነው።” የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ከኪነጥበብ ዘርፉ ጋር ግንኙነት በመፍጠር እነዚህን መሰል ፌስቲቫሎች የሚያዘጋጁት በሥነ ጥበብ እና በኪነ ጥበብ ሥራዎች የሚተላለፉ መልእክቶች እንዲሁም ባለሞያ ያልሆንነው ሌሎች ሰዎች ስለምናስተላልፋቸው መልእክቶች በታሰበበት እና በታቀደበት መልኩ እንድንጠነቀቅ የሚያስታውስ ነው። ስለሆነም የሁለቱ ዘርፎች መተባበርና በጋራ መሥራት አስፈላጊም የሚጠበቅም ነው።

በ2014 ዓ.ም. የተጀመረው ይህ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል፣ በመጀመሪያው ዙር በአዳማ፣ በአዲስ አበባ እና በሃዋሳ ከተሞች፣ በሁለተኛው ዙር ደግሞ በአዳማ፣ በአዲስ አበባ፣ በባሕር ዳር፣ በሃዋሳ እና በጅግጅጋ ከተሞች ተካሂዷል። በሁለቱ ዙሮች በአጠቃላይ ከ15 ያላነሱ እና በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ አጫጭር እና ፊቸር ፊልሞች፣ ዘገባዎችና የተለያዩ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ልብወለድ ታሪኮች ፊልሞች ታይተዋል፣ 20 የሚሆኑ የፊልም አዘጋጆችና ባለሞያዎች ሥራዎቻቸውን ለመድረክ አቅርበውበታል፣ እንዲሁም ከ10 ያላነሱ የኮሚሽኑ አጋር ተቋማት ተሳትፈውበታል።

በፌስቲቫሎቹ ላይ የፊልም እና በሌሎች የኪነጥበብ ዘርፍ ሙያ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች እና ተማሪዎችን ጨምሮ በሰብአዊ መብቶች ላይ የሚሠሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች፣ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል። አዲስ አበባን ጨምሮ ፌስቲቫሎቹ በሁለት ዙር በተካሄዱባቸው አምስት ከተሞች፣ በኮሚሽኑ ድረ ገጾች፣ በመገናኛ ብዙኃን ሽፋን እና በአጋር ድርጅቶች ድጋፍ ዝግጅቱ የተለያዩ የሰብአዊ መብቶች እና ተያያዥ ጉዳዮችን በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ተደራሽ ሆነዋል።

የምልክት ቋንቋን ጨምሮ በተለያዩ ቋንቋዎች የተሠሩ ፊልሞችን በመተርጎም ፌስቲቫሉን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት የሚቀጥል ነው። ኢሰመኮ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የሚያቀርበው ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ኪነ-ጥበብን ከሰብአዊ መብቶች ትምህርት እና ግንዛቤ ማሳደግ ጋር አጣምሮ በይዘቱ፣ በተደራሽነቱ እና በአሳታፊነቱ እየጎለበተ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

በ2014 ዓ.ም. እና በ2015 ዓ.ም. በተካሄዱት የፊልም ፌስቲቫሎች ከታዩ ፊቸር እና ዘጋቢ ፊልሞች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡-

በኢሰመኮ ገንዘብ ድጋፍ የተዘጋጁ፡-

  • ሰብአዊ መልካችን በፊልሞቻችን (ዘጋቢ ፊልም)– አቀናባሪ ሱራፌል ተፈራ (በተለይም በአማርኛ ቋንቋ ፊልሞች ውስጥ የተለያዩ ማኅበረሰብ ክፍሎች ሰብአዊ መብቶች የሚገለጹበትን መንገድ የሚዳስስ) 
  • ተጠርጣሪው፡– ደራሲና አዘጋጅ ዳዊት ተስፋዬ (በኢትዮጵያ ውስጥ በወንጀል ተጠርጠረው የሚያዙና የሚታሰሩ ሰዎችን አያያዝ ሁኔታ የሚዳስስ አጭር ፊልም) 
  • መፈናቀል (ዘጋቢ ፊልም)– አቀናባሪ ዘሌማን ፕሮዳክሽንስ (ከተለያዩ ክልሎች በግጭት ምክንያት ተፈናቅለው በአማራ ክልል፣ በባሕር ዳር ከተማ አቅራቢያ መጠለያ ውስጥ በሚኖሩ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ሕይወት የሚዳስስ) 
  • ቆሎጂ (ዘጋቢ ፊልም)፡- አዘጋጅ መዓዛ ፊልም ፕሮዳክሽንስ (በሶማሌ ክልል ቆሎጂ መጠለያ ካምፕ ውስጥ በተራዘመ የሀገር ውስጥ መፈናቀል ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን የዕለት ተለት ውጣ ውረዶች የሚያስቃኝ) 

በኪነጥበብ ባለሞያዎቹ ፈቃድ ለእይታ የቀረቡ፡-

  • ቁራኛዬ:– በጸሐፊና ዳይሬክተር ዶ/ር ሞገስ ታፈሰ የተዘጋጀው ቁራኛዬ በኢትዮጵያ ተቋማዊ የሆነ የፍትሕ ሥርዓት ከመጀመሩ በፊት የነበረውን የፍትሕ አሠራር የሚያሳይ ነው።
  • ሰውነቷ:– ለሥራ ዕድል ወደ መካከለኛ ምሥራቅ ያቀናች ሴት ታሪክ፣ ሕይወት እና ውጣውረድ ላይ በማተኮር ተስፋ፣ ሰብአዊነት እና ለወገን ተቆርቋሪነት ያሳያል። በሰውመሆን ይስማው (ሶሚክ) ዳይሬክት የተደረገው ሰውነቷ በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ነው። 
  • ሀዲ ስንቄ:- ሀደ ሚልኪ በኦሮሞ ማኅበረሰብ ውስጥ የእኩልነት የእድል እና የፍትሕ እናት ነች፡፡ በሀገሪቱ የተለያዩ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውሶች ሲከሰቱ ከአባ ገዳዎች ጋር በመሆን የማረጋጋት እና የማስታረቅ ሚና ይጫወታሉ፡፡ በፍፁም ዘገየ የተዘጋጀው ሀዲ ስንቄ ያለተነገረላቸው የፍትሕ ሥርዓት ባለቤቶች እና የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ሴት የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ ያጠነጥናል።
  • አዲባና፡- በፋንታ ስንታየሁ ዳይሬክተርነት የቀረበ ባህል ተኮር ፊልም ሲሆን በጉጂ ኦሮሞ ባህል ሴት ልጅ የወደደችውንና የመረጠችውን ባል ያለማንም ጣልቃ ገብነት መርጣ እንድታገባ የሚያስችል የጋብቻ ሥነ ሥርዓትን ያስቃኛል።
  • ክሱት:– በአብ በቀለ የተዘጋጀው ክሱት አንዲት ጀግና ገጸ-ባሕርይ በማምጣት የጀግንነትን ምንነት የሴቶችን ሚና ወደፊት በማምጣት ማኅበራዊ ቀውስ እና የሕግ የበላይነትን በሰፊው ይዳስሳል። 
  • ያልተሰፉ ቀዳዶች፡– አካል ጉዳተኞች መሠረተ ልማቶችን መጠቀም የማይችሉት አካል ጉዳተኞች ስለሆኑ ሳይሆን መሰረተልማቶች አካል ጉዳኞችን ለማገልገል ምቹ ሆነው ባለመሠራታቸው መሆኑን የሚያሳይ በቴዎድሮስ ወርቁ የተዘጋጀ ፊልም ነው። 

በእነዚህ እና በሁለት ዙር በተካሄዱት ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫሎች በቀረቡ ሌሎች ፊልሞች አማካኝነት የሴቶች እና ሕፃናት ሰብአዊ መብቶች፣ በስደት እና በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወቅት የሚደርሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች፣ አካል ጉዳተኝነት፣ የእስረኞች እና የተጠርጣሪዎች አያያዝ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ተዳስሰዋል። ከእያንዳንዱ ፊልም እይታ በኋላ የኢሰመኮ ከፍተኛ ኃላፊዎችና ባለሞያዎች፣ የፊልሙ አዘጋጆች እንዲሁም ተጋባዥ ባለሞያዎች በጋር በመሆን አጭር የጥያቄና መልስ እና የውይይት መድረኮች ለተመልካቾች እና ታዳሚዎች አቅርበዋል።

ዓመታዊው የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል የሚያዘጋጀው ኢሰመኮ ቢሆንም፣ የተለያዩ የኪነ ጥበብ ባለሞያዎች በዋና አስተባባሪነት፣ በፌስቲቫሉ የሚታዩ ፊልሞችን ይዘቶች በማዘጋጀት፣ በመዳኘት፣ በማቅረብ እና በፊልሞቹ ላይ ለሚደረጉ ውይይቶች ግብዓት በማቅረብ የሚሳተፉበት ነው። የኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶችን ሥራ በቴክኒክ፣ በፋይናንስ እና ሌሎች ድጋፎች የሚሰጡ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ኤምባሲዎች እና የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች በዓመታዊ ፊልም ፌስቲቫሉም ላይ ይሳተፋሉ፣ በተሳትፏቸውም አማካኝነት ሥራዎቻቸውን እና ተቋሞቻቸውን ማስተዋወቅ ችለዋል።

በዚህም መሠረት የመጀመሪያው ዙር ፊልም ፌስቲቫል አጋር ድርጅቶች ከነበሩ መካከል ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶችን ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ በጋራ የሚያከብሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት (ጽ/ቤት) የምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና ጽ/ቤት (OHCHR- EARO)፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፣ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች ሕብረት (ኢሰመድሕ) እና አምስት አባላቶቹ በ2013 ዓ.ም. ተሳትፈዋል።

በተመሳሳይ መልኩ በ2015 ዓ.ም. የተካሄደው የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል አጋር ድርጅቶች መካከል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ድርጅት፣ የስዊዘርላንድ፣ የኖርዌውይ፣ የእንግሊዝ፣ የጀርመን፣ የዴንማርክ ኤምባሲዎች፣ አይሪሽ ኤይድ እንዲሁም የዳኒሽ ኢንስቲትዩት ፎር ሂውመን ራይትስ ይገኙበታል።

ፊልም ፌስቲቫሉ በተካሄዱባተው ከተሞች የሚገኙ የመንግሥት ኃላፊዎችና የመንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ እንዲሁም የአካባቢው የኪነጥበብ ባለሞያዎች የሚያደርጉት ትብብር ለዝግጅቱ በስኬት መጠናቀቅ ክፍተኛ አስተዋጽዖ የሚያደርግ ነው።

ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫሎች ሰዎችን በአንድ ወቅታዊና አንገብጋቢ ጉዳይ ዙርያ የማሰባሰብና የማስተባበር ጠቀሜታቸው የጎላ የሚሆነው በቅርጻቸው፣ በይዘታቸውና በአጠቃላይ ዝግጅታቸው በየጊዜው የሚሻሻል ሲሆን ነው። ስለሆነም በኢሰመኮ አዘጋጅነት የሚካሄደው ይህ የኪነጥበብና የሰብአዊ መብቶች ጥምር መድረክ ለዝግጅቱ መሳካት አዳዲስ ሐሳብ በማቅረብ፣ የተለያዩ ዓይነት ድጋፎችን በማድረግ፣ በማስተዋወቅ፣ ፊልሞቻቸውን በመድረኩ እንዲታዩ ፈቃድ በመስጠት ወይም በተለያዩ የዝግጅቱ ሂደቶች በአስተባባሪነትም ሆነ በሌላ መንገድ በመተባበር የሚሳተፉ ድርጅቶች ጋር ይተባበራል። በተለያዩ ሀገራዊ ቋንቋዎችና በልዩ ልዩ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ዙርያ የተሠሩ ጥራት ያላቸው ፊልሞችን ያፈላልጋል እንዲሁም እነዚህን የተመረጡ ፊልሞች ተደራሽነት ለማሳደግ የሚያደርገውን ጥረት ይቀጥላል።

በሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫሉ የሚሳተፉ የኪነ ጥበብ ዘርፎችን ከዓመት ዓመት በማስፋት፣ በመድረኩ የሚታዩ ፊልሞችና ሌሎች የኪነጥበብ ሥራዎችን ይዘት ጥራት ለማሳደግ የሚረዱ ውድድሮችና መሰል አሳታፊ ዝግጅቶችን በማካሄድ፣ የሚሳተፉ የኪነ ጥበብ ባለሞያዎችን ቁጥር በመጨመር፣ ዝግጅቶቹ የሚካሄዱባቸውን ከተሞች ቁጥር በማብዛት ኢሰመኮ የፊልም ፌስቲቫሉ እድገትና ዓላማ ለማሳካት ይሠራል።




ጠቃሚ ሰነዶች


በሦስተኛው የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ላይ መሳተፍን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት

filmfest@ehrc.org or +251-973149236