የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የዓለም አቀፍ የሕፃናት ቀን ለማሰብ ባዘጋጀው “ከልጆች ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ” በሚል መርኃ ግብር መሰረት በጥቅምት 26 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ እና ባሕር ዳር ጽሕፈት ቤቶቹ እንዲሁም ኅዳር 10 ቀን 2015 ዓ.ም. በጅማ፣ ጅግጅጋ፣ ሰመራ እና ሃዋሳ ጽሕፈት ቤቶች ከሕፃናት ፓርላማ አባላት፣ ከትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች ክበባት እና ከታዳጊዎች የኪነጥበብ ቡድኖች ከተውጣጡ ሕፃናት ጋር ምክክር አድርጓል። በዚህ ውይይት አካል ጉዳተኛ ሕፃናትን ጨምሮ ዕድሜአቸው ከ8 እስከ 16 የሆኑ ወደ 100 የሚጠጉ ሕፃናት ተሳትፈዋል፡፡ 

ውይይቱ የኢሰመኮ የሴቶች እና ሕፃናት መብቶች ሥራ ክፍል ‹‹ከልጆች ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ›› በሚል መሪ ቃል በጀመረው ንቅናቄ ስር ቀጣይት ያለው ክንውን ነው። የጅምሩ ዓላማ ሕፃናት በሚመለከታቸው ጉዳዮች ላይ ሁሉ የሚመካከሩበት፣ መረጃ የሚለዋወጡበት እና የሚሰበስቡበትን እንዲሁም የውሳኔ ሰጪነት አካል የሚሆኑባቸውን ዕድሎች ለመፍጠርና ለማበረታታት ነው።

መርኃ ግብሩ የሕፃናት ተሳትፎ መብት መሰረታዊ መርሆችን በማራመድ ሕፃናት ከተፅዕኖ ነፃ የሆነ ሕዝባዊ ተሳትፎ እንዲያጎለብቱ፣ ኮሚሽኑ በሕፃናት ሰብአዊ መብቶች ዙሪያ በሚያከናውናቸው ሥራዎች ውስጥ እንደ ባለቤት እንዲሳተፉ፣ የሚሰጡት ሃሳብ ቅቡልነት እንዲያገኝና አግባብነት ባለው መልኩ በኮሚሽኑም ሆነ በሌሎች ባለድርሻዎች የሥራ ሂደቶች ውስጥ እንዲካተት ለማድረግ ነው። በተጨማሪም ሕፃናትን ትርጉም ባለው መልኩ ማሳተፍ የሕፃናትን ጥቅምና ደኅንነት ማዕከል በማድረግ፣ ሕፃናት ሊረዱት በሚችሉትና በሚገባቸው ቋንቋ፣ የዕድሜና የብስለት ደረጃቸውን ባገናዘበ በመልኩ፣ በሚመለከቷቸው ጉዳዮች ሁሉ ላይ እንዲገኙ፣ በተሳትፏቸው የሚገኝ ምልከታም ቅቡልነት እንዲያገኝና አግባብነት ባለው መልኩ እንዲተገበርም ነው፡፡ 

የመድረኮቹ ዓላማ የኮሚሽኑን ዕቅዶች ለሕፃናት ለማጋራት እንዲሁም ከሕፃናት አደረጃጀቶች ጋር ትርጉም ያለው የሥራ አጋራነት ለመመሥረት ነው፡፡ በዚህም መሰረት በ2014 ዓ.ም. ኮሚሽኑ ሕፃናትን በተመለከተ ያከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት እና የኮሚሽኑ ዓመታዊ የሕፃናት መብቶች ሁኔታ ሪፖርት ቀርቧል። በተጨማሪም በ2015 ዓ.ም. በሕፃናት መብቶች ዙሪያ በኮሚሽኑ የታቀዱ ክንውኖች ተገልጸው ሕፃናቱ በሚረዱት ቋንቋ የአካል ጉዳተኛ ሕፃናትንም ፍላጎት ባማከለ መልኩ በማቅረብ ሕፃናቱ ጋር ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡

“ሁሉም ተቋማት፣ የመንግሥትም ሆኑ የግል መሥሪያ ቤቶች ሕፃናትን ማካተት እንዳለባቸው በመርህ ደረጃ ቢታወቅም በተግባር አካትተው ባለመሥራታቸው ምክንያት ለሕፃናት መደረግ ያለበት ነገር እየቀረ፤ የሕፃናት ተሳትፎ ጉዳይ የወረቀት ብቻ፣ የሪፖርት ብቻ ሆኖ እየቀረ ሥራው ወደ መሬት ስለማይወርድ በመንፈሱ የዳበረ ሕፃን እንዳይፈጠር ሆኗል::” በማለት የአዲስ አበባ የሕፃናት ፓርላማ አባል የሆነችው ታዳጊ ዮርዳኖስ አሰፋ በዝግጅቱ ወቅት ተናግራለች።

ተሳታፊ ሕፃናት ይህን መሰል መድረክ እንዲዳብርና ሕፃናት በተደራጀ መልኩ እንዲሳተፉ፣ በሚመለከቷቸው ጉዳዮች ላይ ሁሉ በአግባቡ መሳተፍ እንዲችሉ በተለይም በገጠሪቱ የሀገራችን ክፍል የሕፃናት ፓርላማን እና የትምህርት ቤት ክበባትን በማጠናከር እና ለሕብረተሰቡ በማስተዋወቅ ረገድ ኮሚሽኑን ጨምሮ ሌሎች ባለግዴታ አካላት ተገቢውን ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በሕፃናት መብቶች አጠባበቅ ዙሪያ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ያሉአቸውን ጉዳዮች ለይተው ተወያይተዋል የመፍትሔ ያሏቸውን ሃሳቦችንም አመላክተዋል፡፡

ካነሷቸው ሃሳቦች መካከል “በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ልዩ ልዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ መምጣታቸው፣ በትምህርት ቤቶች አካባቢ የቁማር ቤቶች መብዛት፣ የአልኮል መጠጦችን ያለ ምንም ገደብ ለሕፃናት የሚሸጡ የንግድ ድርጅቶች መበራከትና በሕግ አግባብ አለመጠየቅ፣ የቤት ሠራተኛ ደላሎች በሴት ሕፃናት ሠራተኞች ላይ ከፍተኛ እንግልት እያደረሱ መሆናቸው፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደጎዳና ኑሮ የሚወጡ ሕፃናት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ እና ከጎዳና ኑሮ ለሚወጡ ሕፃናት የማገገምያ ማዕከል አለመኖር” ተጠቃሽ ናቸው። በተጨማሪም “የጠለፋ እና አስገድዶ መድፈር ወንጀሎች በከተማና በገጠር እየተበራከቱ መምጣታቸው፣ በከተማዎች ውስጥ ጭምር የሴት ልጅ ግርዛት በድብቅ የሚፈጸም መሆኑ፣ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች በስፖርት እና በኪነ-ጥበባት እንቅስቃሴዎች ላይ እንዳይሳተፉ በትምህርት ቤት አስተዳደር፣ በመምህራን እና በማኅበረሰቡ የሚደረጉ ክልከላዎች ወይም ጫናዎች መኖራቸው፣ የሴቶች ንጽሕና መጠበቂያ የሽያጭ ዋጋ መናር የመግዛት አቅሙ የሌላቸው ሴት ሕፃናት ተማሪዎች የመማር መብት ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑ እና የሕፃናት ሕገ-ወጥ ዝውውር መስፋፋት” መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

ሕፃናቱ ለእነዚህ አሳሳቢ ጉዳዮች ከመሰረቱ መፍትሔ ማግኘት፣ ለሕፃናት ሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ መሻሻል ቁልፍ ሚና እንዳለው ገልጸው፣ “ኢሰመኮ ለሕፃናት ተሳትፎ አደረጃጀቶች እና ለሕፃናት መብቶች ጥበቃ መሻሻል የሚያደርገውን ድጋፍ ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባው፣ በተለይም ከትምህርት ቤቶች ጋር በጥምረት መሥራት እንዳለበት እንዲሁም ከወላጆች ጋር ተከታታይነት ያለው ውይይት ማድረግ እንደሚገባ፣ የሴቶች እና ሕፃናት ሕገ-ወጥ ዝውውርን በተመለከተ አጥፊዎች ላይ ከሚሠራው የሕግ ተጠያቂነት ሥራ ባሻገር ለማኅበረሰቡና ለወላጆች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው እና ከጎዳና ኑሮ ለሚወጡ ሕፃናት የማገገምያ ማዕከል ግንባታን በተመለከተ ኮሚሽኑ የውትወታ ሥራ ሊሠራ እንደሚገባ፣ ለሴት ተማሪዎች የንጽሕና መጠበቂያ ሞዴስ በነፃ እንዲሰጥ ወይም ከቀረጥ ነፃ እንዲገባ ኮሚሽኑ መንግሥትን በመወትወት ረገድ ግዴታውን እንዲወጣ እንዲሁም የሕፃናት ሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመከላከል የወንጀል ፈጻሚዎችን ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ” ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢሰመኮ የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ ሕፃናትን በሚመለከቷቸው ጉዳዮች ላይ ትርጉም ባለው መልኩ ማሳተፍ የሕፃናት መብቶች ኮንቬንሽን እና የአፍሪካ የሕፃናት መብቶችና ደኅንነት ቻርተር መሰረታዊ መርህ መሆኑን አስታውሰዋል። አክለውም “እንደማንኛውም ባለመብት ሕፃናት የሕግና የፖሊሲ ቀረጻ፣ የሕዝባዊ ጉዳዮች ምክክርና ውሳኔ አሰጣጥ ይመለከታቸዋል፡፡ ሕፃናት በሚመለከታቸው ጉዳዮች ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ መንግሥት፣ ቤተሰብ፣ ትምህርት ቤቶች፣ ተቋማት፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ እና ሌሎች አካላት የበኩላቸውን ጥረት በማድረግ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ይገባቸዋል። ሕፃናትን አካታች ተቋማት፣ መዋቅሮች እና አሠራሮች መዘርጋት የሁላችንም ግዴታ ነው።” ብለዋል፡፡ የውይይት መድረኩ በሁሉም መንግሥታዊ ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላት ጠረጴዛ ዙሪያ እንዲካተት ሁላችንም ለሕፃናት ሕዝባዊ ተሳትፎ መበልጸግ የበኩላችንን አስተዋጾ እናድርግ በማለት ኮሚሽነር መስከረም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 

በተመሳሳይ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በዋናው ጽሕፈት ቤት በተደረገው ውይይት ላይ በመገኘት የልጆችን ተሳትፎ አበረታተዋል፡፡ እንዲሁም የኢሰመኮ የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረ ሐዋርያ ውይይቱ አካል ጉዳተኞችን ያሳተፈ መሆኑ የሚበረታታ እንደሆነ ገልጸው፣ በቀጣይም ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በአካል ጉዳተኛ ሕፃናት ሰብአዊ መብቶች ላይ ሰፊ ሥራ እንደሚሠራ እና ተሳትፎአቸውንም እንደሚያጎለብት አስታውቀዋል።