የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በላከው የሀገሪቱ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት ኮሚሽኑ በተገባደደው በጀት ዓመት ባከናወናቸው የክትትል፣ የምርመራ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ የዳሰሳ ጥናቶች እና ልዩ ልዩ ተግባራት የተመለከታቸውን መልካም ጅማሮዎችን፣ እንዲሁም በአፋጣኝ መፍትሔ ሊያገኙ እና ሊሻሻሉ የሚገቡ አሳሳቢ ጉዳዮችን የሚያካትት መሆኑን ገልጿል።
ኢትዮጵያ በምትገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ በፍጥነት ተለዋዋጭ መሆኑን የገለጸው ኢሰመኮ፣ ዓመታዊ ሪፖርቱ በሚሸፍነው ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ እና በርካታ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መከሰታቸውን አብራርቷል፡፡
ኮሚሽኑ እጅግ አስከፊ የሆኑ በማለት ያመላከታቸውን የበርካታ ሰዎች ሞት፣ የአካልና ሥነልቡና ጉዳት፣ ጾታዊና ወሲባዊ ጥቃት፣ መፈናቀልና፣ ንብረት ውድመት ጥሰቶች በመንግሥት ኃይሎችና ከመንግሥት ውጭ በሆኑ የታጠቁ ኃይሎችና ቡድኖች በጦርነትና ግጭት አውድ ውስጥ የተፈጸሙ፣ በሲቪል ሰዎች ላይ ያነጣጠሩ፣ ሴቶች፣ ሕፃናት፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞችንም ጨምሮ በከፍተኛ ግፍና ጭካኔ የተፈጸሙ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በሪፖርቱ በዝርዝር አብራርቷል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ከተካሄደው ጦርነት ጋር ተያይዞ በጦርነቱ ተሳታፊ የነበሩ ሁሉም ኃይሎች ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶችን እና የሰብአዊነት ሕጎችን ድንጋጌ በሚጥስ መልኩ በሲቪል ሰዎች ላይ ጥሰቶችን ፈጽመዋል፡፡ ጦርነቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች በሕይወት የመኖር መብት፣የአካል ደኅንነት መብት፣ፍትሕ የማግኘት መብት፣ ከጭካኔ፣ ኢሰብአዊና አዋራጅ አያያዝና ቅጣት ነፃ የመሆን መብቶች ጥሰቶች በመንግሥት ወታደሮች፣ በሕወሓት ኃይሎችና በተለያዩ የታጠቁ ቡድኖች ተፈጽመዋል። ተጎጂዎች በአብዛኛው ሲቪል ሰዎች ሲሆኑ፣ በጦርነት ተሳታፊ የነበሩና የተማረኩ ተዋጊዎችም ለመብት ጥሰቶች ተጋልጠዋል። በሌሎችም ክልሎች በተወሰኑ ፖሊስ ጣቢያዎችና መደበኛ ባልሆኑ የእስር ቦታዎች ከጦርነቱ ጋር በተያየዘ በታሰሩ ሰዎች ላይ ላይ ተገቢ ያልሆነ አያያዝ፣ የተራዘመ የቅድመ ክስ እስር እና ድብደባ ተፈጽሟል፡፡
በሪፖርቱ በተሸፈነው ጊዜ በተለይ በሥራ ላይ ከነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር ተያይዞ በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች የዘፈቀደ እስራት፣ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማሰር፣ መደበኛ ባልሆኑ ቦታዎች ማሰር፣ የቤተሰብ እና የሕግ አማካሪ ጉብኝትን መከልከል እንዲሁም ምርመራ ሳይጀመር የተራዘመ የቅድመ ክስ እስራት በሰፊው ተስተውሏል። በተጨማሪም በአንዳንድ ቦታዎች ፍርድ ቤት በዋስትና እንዲለቀቁ የፈቀደላቸው፣ የክስ መዝገቦቻቸው ተዘግተው በፍርድ ቤት ውሳኔ በነፃ የተሰናበቱ እና በዐቃቤ ሕግ መዝገባቸው የተዘጋ ሰዎች ከእስር ሳይፈቱ አንዲቆዩ በማድረግ የፍርድ ቤት ውሳኔዎችም ተጥሰዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም በሕወሓት እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ሲደረግ ከቆየው ጦርነት ጋር ተያይዞ፤ በተለያዩ አካባቢዎች በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ ሰዎች አብዛኞቹ የተለቀቁ ቢሆንም የአፋር ክልል ፀጥታ ኃይሎች ከኪልበቲ ረሱ ዞን እና አካባቢ ከመኖሪያ አካባቢያቸው “ደኅንነታቸው ለማስጠበቅ እና በወንጀል የሚጠረጠሩ ሰዎችን ለመለየት” በሚል ምክንያት የሰበሰቧቸውን ወደ ዘጠኝ ሺህ የሚጠጉ የትግራይ ተወላጆች ሰመራ ከተማ በሚገኙ ሰመራ እና አጋቲና ካምፖች ከታኅሣሥ ወር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ይህ ሪፖርት ይፋ እስከተደረገበት ጊዜ ከፈቃዳቸው ውጭ ተይዘው የሚገኙ መሆናቸውን ኢሰመኮ በሪፖርቱ አስታውሷል፡፡ በካምፖቹ ከሰብአዊ እርዳታና የሕክምና አገልግሎት ውስንነት የተነሳም ለሕይወት መጥፋት ምክንያት መሆኑንም አክሎ ገልጿል፡፡
በትግራይ፣ በአፋር እና በአማራ ክልሎች የተካሄደው ጦርነት በአካባቢዎቹ በመሰረታዊ አገልግሎቶች መቋረጥ፣ በጤና እና በትምህርት ተቋማት፣ እንዲሁም በግል ንብረቶች ላይ ያደረሰው ውድመት፣ እንዲሁም ጦርነቱ ባስከተለው መፈናቀል ሳብያ በተከሰተው የእርዳታ ፈላጊዎች መጨመር፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ ምርት መስተጓገሉ በተለይም ምግብ የማግኘት መብት፣ በጤናና ትምህርት አገልግሎት የማግኘት መብቶችን ጨምሮ በሁሉም ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መብቶች ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳደረ መሆኑን በሪፖርቱ ተመልክቷል። ከዚህም በተጨማሪ በኦሮሚያ እና በሶማሌ ከልሎች የሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች በድርቅ በመጠቃታቸው ምክንያት በመንግሥት እና መንግሥታዊ ባልሆኑ የእርዳታ ድርጅቶች የሚያቀርቡ ድጋፍ የመስጠት አቅም ላይ ጫና ያሳደረ መሆኑን ገልጿል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከ4 ሚልየን በላይ የሚቆጠሩ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች አሁንም አሳታፊ የሆነ ዘላቂ መፍትሔ የሚጠብቁ መሆናቸውን እና የእርዳታ አቅርቦቱም ሆነ በአጠቃላይ ሀገራዊው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች የተጠለሉ ስደተኞችን ሕይወት ላይም ተጽዕኖ ያሳደረ መሆኑም ተገልጿል። በተመሳሳይ መልኩ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች ሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ክትትል እና በተለይም የመንግሥት አካላትን ትኩረት የሚጠይቅ መሆኑንም ኢሰመኮ በሪፖርቱ አስረድቷል።
የአመለካከት፣ ሃሳብን በነጻ የመያዝና የመግለጽ እንዲሁም መረጃ የማግኘት መብቶችን በተመለከተ ኢሰመኮ ባደረገው ክትትል መሰረት፣ ከሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም. እስከ ግንቦት ወር 2014 ዓ.ም. ድረስ በተለያዩ ወቅቶች፣ በትግራይ ክልል ተይዘው የሚገኙ መሆናቸውን የተገለጹ 15 የሚድያ ሠራተኞችን ጨምሮ 54 የሚዲያ ሠራተኞች ተይዘው ከቀናት እስከ በርካታ ወራት ለሚሆን ጊዜ በእስር መቆየታቸውን አመላክቷል፡፡
የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርቱ በ2014 በጀት ዓመት መጀመሪያ ላይ የተካሄደውን 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በተመለከተ፣ ለኢሰመኮ የቀረቡ አቤቱታዎች ላይ የተመረኮዙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን፣ እንዲሁም መደበኛ ባልሆኑ ማቆያ ስፍራዎች፣ በማረሚያ ቤቶች እና በፖሊስ ጣቢያዎች በጥበቃ ሥር ያሉ (የታሰሩ) ሰዎች መብቶች እና የተያዙ ሰዎች ሁኔታን በተመለከተ ዝርዝር መረጃዎችን እንደሚያካትት ኮሚሽኑ ባዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ተብራርቷል።
በበጀት ዓመቱ በተለያዩ የመንግሥት መዋቅሮች ከተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በተጨማሪ መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላትም ዘርፈ ብዙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተፈጽመዋል። በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ከተከሰተው ጦርነት ጋር በተያያዘ እና በሌሎችም አካባቢዎች በታጠቁ ኃይሎች፣ በኢመደበኛ ቡድኖች እና በግለሰቦች በሲቪል ሰዎች ላይ ብሔርን ወይም ሃይማኖትን መሰረት ያደረጉ ጾታዊና ወሲባዊ ጥቃቶችን ጨምሮ፤ የግድያ፣ የአካል ጉዳት፣ ማፈናቀል እና የንብረት ማውደምና ዘረፋ ድርጊቶች መፈጸማቸውን ኮሚሽኑ በበጀት ዓመቱ ባከናወናቸው የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሪፖርቶች ማረጋገጡን ሪፖርቱ ያስታውሳል፡፡
“በአጠቃላይ በሀገሪቷ የተከሰተው ጦርነት፣ ግጭት እና የተስፋፉ በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች መንስዔያቸው የፖለቲካ አለመግባባት/አለመረጋጋት ውጤት ስለሆኑ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ሁሉን አቀፍ ፖለቲካዊ መፍትሔ አስፈላጊ መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው” በማለት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በሪፖርቱ ባሰፈሩት መልዕክት ጥሪ አቅርበዋል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም “የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርቱ ኮሚሽኑ ለአንድ ዓመት ባከናወናቸው የሰብአዊ መብቶች ሥራ አማካኝነት በምርመራ፣በክትትል፣ በጥናት እንዲሁም በሰብአዊ መብቶች ትምህርት ተግባራት የሰነዳቸውን ጉዳዮች የሚዳስስ እንደመሆኑ የአካባቢያዊ፣ የጊዜና የሰብአዊ መብቶች ዘርፎች ሽፋን ውስንነቶች ቢኖሩበትም፣ እጅግ አሳሳቢና አፋጣኝ መፍትሔ ሊያገኙ የሚገባቸው የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን የሚያመላክት ነው። ስለሆነም በተለይም ለፌዴራል እና ለክልል መንግሥታዊ ባለድርሻ አካላት በየዘርፋቸው የሚመለከታቸውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ለማድረግ እና ለማሻሻል ተገቢውን ምክረ ሃሳብ የሚያቀርብ ነው” ብለዋል። ሪፖርቱ ለሌሎች መንግሥታዊ ላልሆኑ ሀገራዊና ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም ለሥራቸው አስፈላጊ የሆነ ግብዓት የሚሰጥ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡