የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) ከሚያዝያ 2010 ዓ.ም. እስከ ሚያዝያ 2015 ዓ.ም. ባሉት አምስት ዓመታት ነጻነታቸውን በተነፈጉ ሰዎች መብቶች ዙሪያ በአራት ክልሎች ባከናወናቸው 4  ብሔራዊ ምርመራ /National Inquiry/ የተገኙ ዋና ዋና ግኝቶችን እና ምክረ ሐሳቦችን ያጠናቀረ ባለ 130 ገጽ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል።

ብሔራዊ ምርመራ (ግልጽ የአቤቱታ መቀበያ መድረክ) ማለት ውስብስብና ተደጋጋሚ በመሆናቸው፣ አልያም በሀገር አቀፍ ደረጃ ወይም በበርካታ አካባቢዎች የሚታዩ፣ በርካታ ሰዎችን (በተለይም ሕፃናትን፣ ሴቶችን፣ የአካል ጉዳተኞችን) የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ሰለባዎች የሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ በጥልቀት ለመወያየትና  ዘላቂ መፍትሔዎችን ለማፈላለግ የሚጠቅም ዘዴ ሲሆን፣ እያንዳንዱ መድረክ በአማካይ ለ4 ቀናት የሚቆይ ነው። ኢሰመኮ ይህንን  ለሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን የምርመራ ስልት ለማስተዋወቅ የካቲት 10 ቀን 2014 ዓ.ም. ከፌዴራልና ከዘጠኝ ክልሎች የተውጣጡ የፖሊስ ኮሚሽነሮች፣ የፍትሕ ተቋማት ተወካዮች እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በአዲስ አበባ ከተማ ስብሰባ ማካሄዱ የሚታወስ ነው። የብሔራዊ ምርመራው ዓላማ የነጻነት መብት ጥሰቶችን መመርመርና መሰነድ፣ ተጎጂዎች የደረሰባቸውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዲናገሩ፣ እንዲሁም አቤቱታ የቀረበባቸው ጉዳዩ የሚመለከታቸው ልዩ ልዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለጉዳዩ ወዲያውኑ ምላሽ እንዲሰጡበት የሚያስችል  መድረክ መፍጠር፣ በሁሉም ባለድርሻ አካላት መካከል የውይይት ዕድል ማመቻቸት፣ በዘፈቀደ እስራት መንስኤዎችና ችግሩን በሚያባብሱ እና በሚያወሳስቡ ሁኔታዎች ዙሪያ ግንዛቤ ማሳደግ እና የመፍትሔ ሐሳቦችን ማቅረብ ነው።

ኢሰመኮ ከኮሚሽነሮች እና ከባለሙያዎች በተውጣጣ መርማሪ ቡድን ለብሔራዊ ምርመራው በሕዝብ ብዛታቸው እና በመልክዓ ምድራዊ ወሰናቸው ስፋት በተመረጡት በአማራ፣ ኦሮሚያ እና ሶማሊ ክልል፣ እንዲሁም በቀድሞው የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ከሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም.  እስከ ሚያዝያ 18 ቀን 2015 ዓ.ም. የአቤቱታ መቀበያ መድረኮችን አካሂዶ መረጃዎችን አሰባስቧል። የጾታ፣ የአካባቢያዊ ውክልና፣ የሃይማኖት ወዘተ. ስብጥርን ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ የተመረጡ ተጎጂዎችንና ምስክሮችን፣ እንዲሁም የመንግሥት ባለሥልጣናትን፣ ምሁራንን፣ የሃይማኖት አባቶችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ የሲቪክ ማኅበራት ተወካዮችን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ጨምሮ በአጠቃላይ 365 ሰዎች በአራቱ ሕዝባዊ ምርመራ መድረኮች ተሳትፈዋል። ኮሚሽኑ ከቃል ምስክርነቶች ባሻገር የሰነድ ማስረጃዎችን እና ምልከታዎችን በማከናወን ተጨማሪ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን አሰባስቧል።

በዚሁም መሠረት ነጻነታቸውን በተነፈጉ ሰዎች ላይ በተደጋጋሚ እና ስልታዊ በሆኑ መንገዶች የሚደርሱ የመብት ጥሰቶች መደበኛ ባልሆኑ ቦታዎች ማሰርን፣ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ መያዝን፣ በፍርድ ቤት የተሰጠ የዋስትና መብትን በመጣስ ማሰርን ጨምሮ የዘፈቀደ እስራትን፣ ወሲባዊ ጥቃትን፣ ደብዛን አጥፍቶ ማሰርን፣ በግዳጅ መሰወርን፣ እና በቂ ምግብና ውሃ በሌላቸው፣ በተጨናነቁ፣ የንፅሕና እና የሕክምና አገልግሎት ባልተሟላላቸው እስር ቤቶች ማሰርን ጨምሮ ማሠቃየትን እና ያልተገባ አያያዝን፤ እንዲሁም በቤተሰብ፣ በሃይማኖት አማካሪዎች እና በሕግ አማካሪዎች የመጎብኘት መብትን መከልከልን ያካትታሉ። ነጻነታቸውን የተነፈጉ ሰዎች በማቆያ ቤቶች እና በማረሚያ ቤቶች ረዘም ላለ ጊዜ ከመቆየታቸው አንጻር የመተዳደሪያ ገቢያቸውን የሚያጡ መሆናቸው እንዲሁም ለጥሰቶቹ የመፍትሔ እና የካሳ ሥርዓት አለመኖሩ በእነዚሁ ብሔራዊ ምርመራ መድረኮች የተለዩ ተጨማሪ ክፍተቶች ናቸው።

አንዳንድ ጥሰቶች እና ችግሮች ስልታዊ ከመሆናቸውም ባሻገር በብዙ ሰዎች ላይ በተደጋጋሚ የመፈጸም አዝማሚያን ያሳያሉ። አብዛኛዎቹ የመብት ጥሰቶች የተፈጸሙባቸው ዐውዶች ከግጭት፣ ካልተመጣጠነ የመንግሥት የኃይል እርምጃ፣ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሁኔታዎች፣ ከምርጫ እንዲሁም ሌሎች ተመሳሳይ ሁኔታዎች ጋር የተያያዙ መሆናቸውን እና ጥሰቶቹን በመፈጸም ረገድ ሚሊሻዎች፣ የቀበሌ አስተዳዳሪዎች፣ የመደበኛ እንዲሁም የልዩ ኃይል ፖሊስ፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና የማረሚያ ቤት ፖሊስ አባላት ተሳትፎ የነበራቸው መሆኑን በሕዝባዊ መድረኮቹ ከተለዩ ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል።

ነጻነታቸውን ያጡ ሰዎች ሰብአዊ መብቶች አስተማማኝ ጥበቃ የሚያገኙበትን፣ በአጥፊዎች ላይ ተጠያቂነት የሚረጋገጥበትን እንዲሁም ተጎጂዎች ካሳ የሚያገኙበትን ሥርዓት ለመዘርጋት የሕግ፣ የአስተዳደር፣ የፍትሕ፣ የፋይናንስ እና ሌሎች እርምጃዎችን መውሰድ የሚገባ መሆኑም በሪፖርቱ ተመላክቷል። የብሔራዊ ምርመራውን ግኝቶች ተመሥርቶ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት ስልታዊ እና ተደጋጋሚ የዘፈቀደ እስራትን እና ተያያዥ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለማስቆም እንዲሁም መንስኤዎቻቸውን በዘላቂነት ለመፍታት እንዲሠሩ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “ነጻነታቸውን የተነፈጉ ሰዎች ሰብአዊ መብቶች የሚጣሱባቸውን ዐውዶች በመመርመር፣ የጥሰት መንስኤዎችን እልባት ለመስጠት፣ ጥሰቶችን ለማስቆም፣ በጥሰቶች ተሳታፊ የሆኑ አጥፊዎችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ እና ለተጎጂዎች ተገቢ የሆነውን የካሳ ሥርዓት ለመዘርጋት እንዲሁም ይህንኑ በሥራ ላይ ለማዋል የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት ቁርጠኛ ሊሆኑ ይገባል” ብለዋል።