የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋዜጣዊ መግለጫ
ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም.

በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አዘጋጅነት ነፃነታቸውን አላግባብ እና በዘፈቀደ የተነፈጉ ሰዎች መብቶች ላይ ያተኮረ፣ በኢትዮጵያ በዓይነቱ የመጀመሪያው የሆነ ብሔራዊ ምርመራ አካል የሆነውን ሕዝባዊ የአቤቱታ ቅበላ መድረክ ከሰኔ 27 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. በሃዋሳ ከተማ ተካሂዷል። ሕዝባዊ የአቤቱታ ቅበላ መድረክ ግልጽ እና ሕዝባዊ ተሳትፎ የሚደረግበትና የመብቶች ጥሰቶች የደረሰባቸው ተጎጂዎች፣ ምስክሮች፣ ሌሎች ባለድርሻ አካላት፣ እንዲሁም የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በአንድ መድረክ በተገኙበት የሚከናወን የምርመራ ስልት ሲሆን፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ወይም በበርካታ አካባቢዎች የሚታዩ ውስብስብና ተደጋጋሚ የሆኑ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በጥልቀት ለመመርመር እና ስልታዊና ዘርፈ ብዙ መፍትሔዎችን ለማፈላለግ የሚጠቅም ዘዴ ነው። በተለይ በአንድ ተቋም በበርካታ አካባቢዎች ለመመርመር አዳጋች የሆኑ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመመርመር ምቹ አጋጣሚን የሚፈጥር እና አነስተኛ የሕዝብና የፖለቲካ ትኩረት ያላቸውን የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ጎልተው እንዲታዩ የሚያስችል ነው። 

በሃዋሳ ከተማ የተከናወነው የመጀመሪያው ብሔራዊ ምርመራ ነፃነታቸውን አላግባብ እና በዘፈቀደ የተነፈጉ ሰዎች መብቶች ላይ ያተኮረ ነው። ነፃነታቸውን አላግባብ የተነፈጉ ሰዎች ሲባል የዘፈቀደ እና ሕገ ወጥ እስርን ጨምሮ ከሕግ አግባብ ውጪ በፖሊስ ጣቢያ የተያዙ፣ በማረሚያ ቤት ያሉ ፣ ያለፈቃዳቸው ጤና ተቋማት የገቡ፣ በግጭት ወቅት የተያዙ ሲቪል ሰዎችን እና የታጠቁ ኃይሎች አባላትን የሚያካትት ነው። ሆኖም ኮሚሽኑ በሃዋሳ ከተማ የተካሄደው ብሔራዊ ምርመራ በይበልጥ ትኩረት ያደረገው በሕገ ወጥ እና በዘፈቀደ ነፃነታቸውን በተነፈጉ ሰዎች እና በተያያዙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ላይ ነው፡፡

ሕዝባዊ የአቤቱታ ቅበላ መድረኩን የመሩት የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ፣ የሲቪል፣ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጂብሪል እና የሴቶች እና ሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ ሲሆኑ፣ ሌሎች የኮሚሽኑ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና አማካሪዎች ከዚሁ መድረክ ጋር የተያያዙ በርካታ ተግባራቶችን በማከናወን ተሳትፈዋል።

በዝግጅቱ የመክፈቻ ንግግር ያሰሙት የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ “ይህ የሕዝብ አቤቱታ መቀበያ መድረክ ስልታዊ እና ተደጋጋሚ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመመርመር፣ ተገቢ እና ዘርፈ ብዙ እርምጃዎች እንዲወሰዱባቸው ለማድረግ እንዲሁም ስለሰብአዊ መብቶች በማስተማር ረገድ ውጤታማ ዘዴ እንደሆነ በሌሎች ሀገራት የታየው ተሞክሮ ተስፋ ሰጪ ነው” ብለዋል። አክለውም ብሔራዊ ምርመራ የፍርድ ሂደት ሳይሆን በሰዎች ላይ የደረሰውን የመብቶች ጥሰቶች በመስማት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመመካከር መፍትሔ የሚፈለግበት መንገድ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ ኮሚሽኑ በሕዝባዊ የአቤቱታ መቀበያ መድረኩ ላይ የቀረቡ አቤቱታዎች ላይ ተጨማሪ መረጃዎችን እና ማስረጃዎችን በማሰባሰብ፣ በመመዘን በዓለም አቀፍ አጣሪ ኮሚሽኖች ጥቅም ላይ የሚውለውን “ምክንያታዊ አሳማኝነት” ተብሎ የሚታወቀውን የማስረጃ ምዘና መስፈርትን በመጠቀም የሚሰንድና የመፍትሔ አቅጣጫ የሚጠቁሙ ምክረ ሃሳቦች ያቀርባል” በማለት መርኃ ግብሩን በይፋ አስጀምረዋል፡፡ 

በመድረኩ ኢሰመኮ ከ30 በላይ ተጎጂዎችን አቤቱታና ደርሶብናል ያሏቸውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ያደመጠ ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል ያለክስ እና ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በተደጋጋሚ እና ለረጅም ጊዜ የታሰሩ፣ “የፓለቲካ ልዩነትን መሰረት ያደረገ” መሆኑ የተገለጸ እና ከሕግ አግባብ ውጪ እና በዘፈቀደ በተደጋጋሚ እና የተራዘመ ቅድመ ክስ እስር የተዳረጉ፣ ጭካኔ የተሞላበትና አሰቃቂ አያያዝ እንደደረሰባቸው የገለጹ፣ እንዲሁም በፖሊስ ጣቢያ እና በማረሚያ ቤት ቆይታ በተደጋጋሚ ሕክምና ተከልክለው ለጤና እክል የተዳረጉ  ይገኙበታል። በዚህ ሕዝባዊ የአቤቱታ ቅበላ መድረክ የተሳተፉ ተጎጂዎች የነፃነት መብታችን አላግባብ ተነፍጓል ያሉ ሰዎች አቤቱታ ኮሚሽኑ  ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እና ለሕዝብ ማካፈል እንዲችሉ እና በቀጣይ ይህንን ዓይነቶቹ ተደጋጋሚ እና ውስብስብ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመቀነስ፣ እንዲሁም መሰል ጥሰቶች ተፈጽመው ሲገኙ ተጎጂዎች የሚካሱበት እና አጥፊዎች ተጠያቂ የሚደረጉበት ጠንካራ ሕግ፣ ተቋም እንዲሁም አሠራር እንዲኖር ለማድረግ ኮሚሽኑ የሚያደርገውን ጥረት አመስግነዋል፡፡

በተጨማሪም በመድረኩ የተሳተፉ የዩኒቨርስቲ ተወካዮች እና የሃይማኖት አባቶች በክልሉ ከሕግ አግባብ ውጪ እና በዘፈቀደ በተደጋጋሚ እና ስልታዊ በሆነ መልኩ የሚፈጸመውን እስር ለመከላከል ሁሉም ኃላፊነት እንዳለበት ገልጸው፣ ኮሚሽኑ ችግሩን ለመቅረፍ የሚያደርገውን ሥራ ለማገዝ ዝግጁ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡ 

በተመሳሳይ መልኩ ከተለያዩ ዞኖች እና ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል የተውጣጡ  የመንግሥት ተወካዮች በበኩላቸው ይህ ዓይነቱ መድረክ በክልሉ ላሉ የሰብአዊ መብቶች ችግሮች አስፈላጊ ስለመሆኑ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ የመንግሥት አካላት ተወካዮቹ ለተገለጹት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ምክንያት የሆኑት መልስ ያላገኙ “የማንነት” እና የአስተዳደር ወሰን ጥያቄዎች መፍትሔ የሚሹ መሆኑን አውስተው፣ የተወሰኑትን አቤቱታዎች ተቀብለው መፍትሔ ለመስጠት ቃል ገብተዋል፡፡ ለተቀሩት ቀጣይ ውይይቶችና ምርመራ እንደሚያስፈልግ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡  

መሰል ብሔራዊ ምርመራዎች በሌሎች ክልሎችም እንደሚካሄድ የገለጹት የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ምርመራውን ተከትሎ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን እንዴት መለየት፣ መገምገም፣ መተንተን እና በተናጠል ጉዳዮች ላይ ስልታዊ የሆኑ ባሕሪያትን መለየት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ግኝቶችን እና ምክረ ሃሳቦችን የያዘ ሪፖርት፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ጨምሮ ለሚመለከታቸው የፍትሕ አካላትና በየደረጃው ለሚገኙ የመንግሥት መዋቅሮች በዝርዝር እንደሚቀርብ አስረድተዋል።