የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔዎች ማፈላለግን አስመልክቶ ከፌዴራል የመንግሥት ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች፣ ከአምስት የክልል ርእሰ መስተዳደሮች ተወካዮች፣ በኢትዮጵያ ከሚገኙ የተለያዩ ኤምባሲዎች፣ ከተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች፣ ከዓለም አቀፍ የልማት ተቋማት እንዲሁም ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ጋር ውይይት አድርጓል።

ከጥር 17 እስከ 18 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው ከፍተኛ የምክክር መድረክ፤ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት የማቋቋም ሀገራዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ አውድ ምን እንደሚመስል፣ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት የማቋቋም ሂደት ላይ የተለያዩ ሀገራዊ ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ሚና ምን መሆን እንዳለበት ሃሳቦች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። በተጨማሪ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሚደረጉ ጥረቶች ያሉ ዕድሎች እና ተግዳሮቶች ምን እንደሚመስሉ፣ ትምህርት ሊወሰድባቸው የሚገቡ በጎ ተሞክሮዎች እንዲሁም ጥረቶችን ለማጠናከር ወደ ፊት መከናወን ስላለባቸው ተግባራት ምክክር ተደርጓል።

በምክክሩ ኮሚሽኑ በተፈናቃዮች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ዙሪያ የሠራቸውን የክትትል ሥራዎች መሠረት በማድረግ ለተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ ለማመቻቸት የሚደረጉ ጥረቶች እና ሊያከብሯቸው የሚገቡ የሰብአዊ መብቶች መርሆች ላይ ውይይት ተደርጓል። በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃ እና ድጋፍ ዙሪያ የተዘጋጀው ረቀቂ አዋጅ የተፈናቃዮችን ዘላቂ መፍትሔ የማመቻቸት ሥራዎች በበቂ የሕግ ማዕቀፍ እንዲደገፍ ከማስቻል ረገድ ያለው ፋይዳ ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን፤ ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በወከሏቸው ክልሎች ያለውን የተፈናቃዮች ነባራዊ ሁኔታ እና ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችን ለተሳታፊዎች አጋርተዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በመክፈቻ ንግግራቸው፤ ኮሚሽኑ የተፈናቃዮችን ሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ለማሻሻል መደበኛ የክትትል ሥራዎች እና ውትወታዎችን ማከናወንን ጨምሮ የተፈናቃዮች ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰዋል። “በተለያዩ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ እና የደኅንነት ሥጋት ሰዎች በተራዘመ የመፈናቀል ሁኔታ ውስጥ እንዲቆዩ እያደረገ ነው። ይህም ለተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ ለማመቻቸትም ዋና ተግዳሮት ሆኗል” ሲሉ በአጽንዖት ገልጸዋል። አክለውም “መንግሥት ለመፈናቀል መንስዔ ለሆኑ ግጭቶች እልባት መስጠት አለበት። እንዲሁም በመፈናቀል ወቅት የጥበቃ እና ድጋፍ ሥራዎችን የሚያሳልጥ እና ዘላቂ መፍትሔን የማመቻቸት ሥራዎችን በበላይነት የሚመራ እና የሚያስተባብር በሕግ ግልጽ ኃላፊነት እና ሥልጣን የተሰጠው ተቋም አስፈላጊ ነው” ብለዋል፡፡

የዕለቱ የክብር እንግዳ የነበሩት የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጽሕፈት ቤት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ ልዩ አማካሪ ሮበርት ፓይፐር ባደረጉት ንግግር፤ ተፈናቃዮች ለመብቶች ጥሰት ተጋላጭ መሆናቸውን እና በተራዘመ የመፈናቀል ሁኔታ ውስጥ ሲቆዩ ደግሞ ለመብቶች ጥሰት እና ለችግር ተጋላጭነታቸው የበለጠ ይጨምራል። የሰብአዊ ድጋፍ ማቅረብ ብቻውን ለመፈናቀል ችግር ዘላቂ መፍትሔ እንደማይሆን ጠቅሰው፤ ዋናው መፍትሔ መፈናቀልን መከላከል እንደሆነ ገልጸዋል። አክለውም “የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ጥበቃ በማረጋገጥ ረገድ እና ዘላቂ መፍትሔዎች በማፈላለግ ሂደት መንግሥት ተቀዳሚ ኃላፊነት ያለበት ቢሆንም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ጥረቶቹ ስኬታማ እንዲሆኑ የጋራ ኃላፊነት አለበት” ብለዋል። በተጨማሪም “ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ማቋቋም የሰብአዊነት ሥራዎችን ከሰላም እና ልማት ሥራዎች ጋር ማስተሳሰር እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን የተቀናጀ ርብርብ የሚፈለግ ጉዳይ ነው” ያሉ ሲሆን “የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ በማፈላለግ ዙሪያ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ሲሆን፤ ለዚህም ትምህርት ሰጪ የሚሆኑ ተሞክሮዎችን መሰነድ ይቻል ዘንድ ከተመረጡት 16 ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ለሁለት ቀናት ሲካሄድ በቆየው የከፍተኛ ደረጃ ምክክር መድረክ፤ የተባበሩት መንግሥታት እና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን መንግሥት በመደገፍ ለተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔዎች ለማፈላለግ በሚደረገው ጥረት በቀጣይ በፌዴራል እና ከፍተኛ የተፈናቃይ ቁጥር በሚያስተናግዱ ክልሎች እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት፣ በዓለም አቀፍ እርዳታ እና ልማት ድርጀቶች የተጠናከረ ርብርብ እንደሚያስፈልግ መተማመን ላይ ተደርሷል። በሂደቱም ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች በመለየት እና የመፍትሔ አቅጣጫዎች በማስቀመጥ የምክክር መድረኩ ተጠናቋል፡፡