የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጎጂዎች ስለሚሰጥ ድጋፍ፣ ማካካሻ እና የመፍትሔ አማራጮች ላይ ዘርፈ ብዙ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የውይይት መድረክ ሚያዚያ 03 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አካሂዷል፡፡ በውይይቱ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የተጎጂዎች ማኅበራት፣ የሙያ ማኅበራት እና ሌሎች የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡ 

የውይይት መድረኩ ዐላማ በሀገራችን ወደፊት ተግባራዊ ለሚደረገው የሽግግር ፍትሕ ሂደት ግብዓት መስጠት ሲሆን በመድረኩ ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጎጂዎች ስለሚሰጥ ድጋፍ፣ ካሳ እና መፍትሔ ዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ የሕግ ማዕቀፎች እንዲሁም የሌሎች ሀገራት ተሞክሮን የሚዳስሱ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡ በተጨማሪም ኢሰመኮ የሽግግር ፍትሕን በተመለከተ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተወካዮች ጋር ባካሄዳቸው ምክክሮች የተሰበሰቡ ዋና ዋና ግኝቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡  

ከሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጎጂዎች መፍትሔ የማግኘት መብትን በተመለከተ በኢትዮጵያ በንብረት መብት እና በሠራተኛ መብቶች ላይ ለደረሱ ጥሰቶች ካሳ ለማግኘት የተሻለ የሕግ ማዕቀፍ እና አፈጻጸም መኖሩ ተገልጿል፡፡ በሌላ በኩል ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የወጣው አዋጅ እና የፀረ-ሽብር አዋጁ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እና በሽብር ተግባራት የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የደረሰባቸው ተጎጂዎች ካሳ የማግኘት መብት እንዳላቸው የሚደነግጉ ቢሆኑም ተፈጻሚነታቸው ክፍተት እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡ በተጨማሪም የሕገ ወጥና የዘፈቀደ እስራት እንዲሁም የማሰቃየትና የጭካኔ ተግባራት ሰለባ የሆኑ ተጎጂዎችን የካሳ መብት ለማረጋገጥ ሁሉን አቀፍ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩንና ያሉትም ጥቂት የሕግ አንቀጾች ተፈጻሚነታቸው ውስን እንደሆነ በቀረበው መነሻ ጽሑፍ ተመላክቷል፡፡

ኢሰመኮ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት (OHCHR) ጋር በመተባበር በአፋር፣ በሱማሌ፣ በሐረሪ፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተወካዮች ጋር የሽግግር ፍትሕን በተመለከተ ምክክር አካሂዶ መሪ ሰነድ ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡ በሂደቱም የማኅበረሰብ ተሳትፎ ሊረጋገጥ እንደሚገባ፣ ተጎጂዎች ካሳ ማግኘት እና ወደቀደመ ሕይወታቸው መመለስ እንዳለባቸው የማኅበረሰብ ተወካዮቹ በአጽንኦት ካነሷቸው ሐሳቦች መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸው በውይይቱ ተብራርቷል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የውይይት መድረኩን ሲከፍቱ ባስተላለፉት መልእክት የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የሚፈጽሙ ሰዎችን የሕግ ተጠያቂነት ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው “ከዚሁ ጎን ለጎን ተጎጂዎች በቂ ካሳ እና ማካካሻ እንዲያገኙ ማድረግና የመብት ጥሰቱ እንደማይደገም ማረጋገጥ ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡ አክለውም በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ለሰብአዊ መብቶች ተጎጂዎች የገንዘብ ካሳ የመክፈል በጎ ጅምሮች የታዩ ቢሆንም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሰብአዊ መብቶች ተጎጂዎች የካሳ ፈንድ ማቋቋምና ተቋማዊ ቅርጽ የሚይዝበትን አሠራር ከወዲሁ መጀመር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡