የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) የቀረቡ አቤቱታዎችን መነሻ በማድረግ እና በመደበኛ የክትትል ሥራው በተለያዩ ክልሎች ለሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እየቀረበ ስላለው ሰብአዊ ድጋፍ ሲከታተል የቆየ ሲሆን፣ ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት ወር 2016 ዓ.ም. ድረስ በተለያዩ ጊዜያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚገኙባቸውን የአፋር፣ የአማራ፣ የኦሮሚያ እና የትግራይ ክልሎች የተወሰኑ አካባቢዎች፣ በአካል በመገኘትና በሌሎች መንገዶች ክትትል በማድረግ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ከፍተኛ ኃላፊዎችን ጨምሮ የሚመለከታቸውን የክልል መንግሥት ተቋማት፣ ተፈናቃዮችን እና የተፈናቃይ ተወካዮችን እንዲሁም የዓለም አቀፍ የተራድዖ ድርጅቶችን በማነጋገር መረጃዎች እና ማስረጃዎች አሰባስቧል። በዚህም መሠረት ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም. እስከ መስከረም ወር 2016 ዓ.ም. ድረስ በሁለት ዙር በተለይ የምግብ ድጋፍ እንደሚፈልጉ በአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽኑ በተለዩ በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ በፌዴራል እና በክልሎች የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ቢሮዎች አማካኝነት የተወሰነ አቅርቦት መደረጉን ማወቅ የተቻለ ሲሆን፣ እየተሰጠ ያለው ድጋፍ ተፈናቃዮች ካሉበት እጅግ አሳሳቢ የሰብአዊ ቀውስ አንጻር በቂ እንዳልሆነ፣ ልዩ ፍላጎት/ልዩ ድጋፍ (Special needs) የሚያስፈልጋቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎችን ያላማከለ መሆኑን (ሕፃናት፣ ነፍሰጡር እና የሚያጠቡ እናቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን፣ የጤና እክል/ሕመም ያለባቸውን ተፈናቃዮች) ተወካዮች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ያስረዳሉ።
በአፋር ክልል በአጠቃላይ ከ800,000 በላይ የምግብ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች እንዳሉ የክልሉ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር እና ምግብ ዋስትና የገለጸ ሲሆን፤ 120,000 በላይ የሚሆኑት በምግብ እጥረት የተጠቁ እናቶችና ሕፃናት መሆናቸው ታውቋል። በክልሉ አብዛኞቹ አካባቢዎች የምግብ ድጋፍ ከ4 ወራት በላይ እንዳልተሰጠ፣ ከመስከረም ወር 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ከበራሃሌ ወረዳ አላ ቀበሌ እና ከመጋሌ ወረዳ ሂዳ እና አራዱ ቀበሌዎች በጦርነት ምክንያት ተፈናቅለው በዴሳኮሪማ እና በድርማ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች በክልሉ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር እና ምግብ ዋስትና ቢሮ በኩል የተወሰነ ምግብ ድጋፍ ያገኙ ቢሆንም፣ ከተፈናቃዮች ብዛት አንጻር በቂ እንዳልሆነ እና ለሁሉም ተፈናቃዮች ተደራሽ ማድረግ እንዳልተቻለ ተገልጿል።
ኮሚሽኑ ክትትል ባደረገባቸው እና በሰሜኑ ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት ባስተናገዱት ኪልባቲ ረሱ ኤረብቲ፣ አብዓላ፣ በራሃሌ እና መጋሌ ወረዳዎች፤ እንዲሁም ፋንቲ ረሱ ጎሊና ወረዳ ውስጥ ለሚገኙ ተፈናቃዮች በቅርቡ በመንግሥት አካላት የተወሰነ የምግብ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን፣ እንዲሁም የሚቀርበው የምግብ ድጋፍ ለሁሉም ተፈናቃዮች እና ተመላሾች ተደራሽ እንዳልሆነ እና ካለው የምግብ ድጋፍ ፍላጎት ጋር ሲነጻጸር ሰፊ ክፍተት እንዳለ ማወቅ ተችሏል። በተለይም ጦርነቱ በንግዱ ሴክተር ላይ ባሳደረው አሉታዊ ተጽዕኖ ነጋዴዎች ለገበያ በቂ የምግብ ነክ ሸቀጦች ማቅረብ አለመቻላቸው እና በዚህ ምክንያት የተከሰተው የምግብ ዋጋ ማሻቀብ ሁኔታውን ማባባሱን መረዳት ተችሏል።
በአማራ ክልል በተመሳሳይ በተወሰኑ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የምግብ ድጋፍ የተደረገ ቢሆንም (ለምሳሌ በሰሜን ወሎ ዞን፣ በሚገኘው የጃራ መጠለያ ከ4 ወራት መቋረጥ በኋላ በመስከረም ወር 2016 ዓ.ም. የተደረገ ድጋፍ)፤ በአብዛኛው በክልሉ ካለው የሰብአዊ ድጋፍ ፍላጎት በተጨማሪ ይህ ሪፖርት በሚዘጋጅበት ጊዜ ድረስ የቀጠለው የትጥቅ ግጭት እና ተያያዥ የጸጥታ ሥጋት እና የእንቅስቃሴ ውስንነት ምክንያት የምግብ ድጋፍ ለማቅረብ አዳጋች ሆኗል። ለአብነት በምዕራብ እና በሰሜን ጎጃም፤ በደቡብ፣ በማእከላዊ እና በሰሜን ጎንደር በዋናነት ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ተፈናቃዮች ሰብአዊ ድጋፍ እያገኙ አይደለም። ከሰሜን ሸዋ ዞን፣ ምንጃር ወረዳ (አውራ ጎዳና ቀበሌ) ተፈናቅለው በመልካ ጅሎ ቀበሌ በሚገኘው የመልካ ጅሎ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የውሃ ሥራዎች ድርጅት ባስገነባው የቆርቆሮ ጥላ፣ እንዲሁም በዛፍ ጥላ ሥር ተጠልለው የሚገኙ ከ3,000 በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮች በአካባቢው ነዋሪዎችና በአንድ ተራድዖ ድርጅት ከተደረገላቸው መጠነኛ የምግብ ድጋፍ ውጪ ይህ መግለጫ ይፋ እስከሆነበት ጊዜ ድረስ በመንግሥት በኩል የተደረገ ድጋፍ አለመኖሩን ለማወቅ ተችሏል። በማእከላዊ ጎንደር ዞን፣ ቀበሮ ሜዳ በሚባለው መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች ምንም ዓይነት ሰብአዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው አለመሆኑን፣ ሰዎች በምግብ እጥረት ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠው እንደሚገኙ፣ ተጽዕኖውም በሴቶች፣ በሕፃናት፣ በአረጋውያን እና በአካል ጉዳተኞች ላይ የበረታ እንደሆነና፣ ተፈናቃዮች በሕብረተሰቡ ከሚደረግ ምግብ እና የገንዘብ መዋጮ ድጋፍ ውጪ ሁኔታውን የሚቋቋሙበት ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው መረዳት ተችሏል።
በኦሮሚያ ክልል ኮሚሽኑ ሲያካሂደው በነበረው ክትትል በምዕራብ ወለጋ፣ በምሥራቅ ወለጋ፣ በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞኖች የተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች በዞኖቹ እና በወረዳ ደረጃ የሚገኙ የመንግሥት አስተዳደር አካላት፣ የአካባቢ ማኅበራት እና በሀገራዊ እና በዓለም አቀፍ በጎ አድራጊ ድርጅቶች በተወሰነ ደረጃ ሰብአዊ ድጋፎች ሲደረጉላቸው የቆዩ ቢሆንም፣ የሚቀርበው የምግብ ድጋፍ በቂ፣ ተደራሽ እና ወቅቱን የጠበቀ እንዳልሆነ፤ እንዲሁም ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ፍላጎት ባገናዘበ መልኩ የሚቀርብ እንዳልሆነ መገንዘብ ተችሏል። ለአብነት በቤጊ ወረዳ፣ ቤጊ ከተማ፣ ቀበሌ 1 እና 2 ውስጥ ከተቀባይ ማኅበረሰብ ጋር የሚኖሩ፣ እንዲሁም በከተማው የቀበሌ አዳራሽ እና ለማኅበራት የንግድ ሥራ አገልግሎት በተገነቡ የቆርቆሮ ጥላ ሥር ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች ለዓመታት በአካባቢው በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በታጣቂ ኃይሎች መካከል ሲከሰቱ በነበሩ ግጭቶች ምክንያት መቅረብ የነበረበት የሰብአዊ ድጋፍ ተስተጓጉሎ መቆየቱን፣ በሰላም እጦት የተነሳ በአካባቢው የሚገኙ ማኅበረሰቦች እና ተፈናቃዮች የግብርና ሥራ ማከናወን ሳይችሉ በመቅረታቸው ለከፋ የምግብ እጥረት መጋለጣቸውን ማረጋገጥ ተችሏል።
መፈናቀሉ በስፋት ከተከሰተበት ከ2013 ዓ.ም. እስከ 2015 ዓ.ም. መገባደጃ ድረስ በነበሩት ጊዜያት ከመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የቀረበላቸው የምግብ ድጋፍ አለመኖሩን ተፈናቃዮች ያስረዱ ሲሆን፤ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በበኩላቸው ምንም እንኳን በተባለው ወቅት በመንግሥት በኩል ምግብ ነክ እና ሌሎች ድጋፎች ወደ አካባቢው ሲላክ ቢቆይም፣ ሰብአዊ ድጋፉን በጸጥታ ችግር ምክንያት ማድረስ አለመቻሉን ወይም በታጣቂዎች በመንገድ ላይ እንደተዘረፈ አስረድተዋል።
ኮሚሽኑ ከአካባቢው የጤና ተቋማት፣ የዞን እና የወረዳ ጤና ቢሮዎች ባሰባሰበው መረጃና ማስረጃዎች መሠረት በምዕራብ ወለጋ ዞን በሐምሌ እና ነሐሴ 2015 ዓ.ም. ወራት ከ6 ወር እስከ 5 ዓመት ዕድሜ ክልል የሚገኙ ተፈናቃይ እና የአካባቢው ነዋሪ ሕፃናት ላይ በተከናወነ የልየታ ሥራ 1,350 የሚሆኑ ሕፃናት ለከፋ የምግብ እጥረት (Severe acute malnutrition)፣ 4,754 የሚሆኑት ደግሞ ለመካከለኛ የምግብ እጥረት (Moderate acute malnutrition) ተጋልጠው እንደሚገኙ እና ከእነዚህም መካከል በቤጊ ወረዳ መድረስ በተቻሉ ቀበሌዎች በተሠራ የልየታ ሥራ በድምሩ 1,281 ሕፃናት ለምግብ እጥረት ተጋልጠው እንደሚገኙ ማወቅ ተችሏል።
በትግራይ ክልል ኮሚሽኑ በአካል ተገኝቶ ክትትል ባደረገባቸው አካባቢዎች ለተፈናቃዮች የመጨረሻው የምግብ ድጋፍ የቀረበው በጥር ወር 2015 ዓ.ም. ሲሆን፤ በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ በመጋቢት ወር 2015 ዓ.ም. መሆኑን ለመረዳት ተችሏል። ለማሳያነት በምግብ ድጋፍ መቋረጥ ሳቢያ እና ተያያዥ ምክንያቶች በትግራይ ክልል ቁጥራቸው ከፍ ያለ ተፈናቃዮች መሞታቸውን እና በሞት አፋፍ ላይ እንደሚገኙ ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው ተጎጂዎች እና የሚመለከታቸው የክልሉ አካላት ገልጸዋል። የትግራይ ክልል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ቢሮ ኃላፊዎች ለኢሰመኮ በደብዳቤ በሰጡት ምላሽ በ5 ከተሞች በሚገኙት 53 የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎቸ እንደ ናሙና ተወስዶ በተደረገ ጥናት፣ በዚሁ ወቅት በሌሎች ምክንያቶች የሞቱትን ሰዎች ሳያጨምር ቢያንስ 1,329 ተፈናቃዮች በምግብ እጥረት ብቻ መሞታቸውን ጥናቱ እንዳሳየ ገልጸዋል። የዚህን ጥናት ግኝት ኢሰመኮ በራሱ ምርመራ ያረጋገጠው ባይሆንም የጉዳዩን ከፍተኛ አሳሳቢነት ያሳያል፡፡ በተጨማሪ ቁጥራቸው 970 የሆኑ ከ1 እስከ 5 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃይ ሕፃናት ለከፍተኛ የምግብ እጥረት (Malnutrition) መጋለጣቸው በተከናወነ የልየታ ሥራ መረጋገጡን እና በተወሰኑ የጤና ተቋማት እና የተራድዖ ድርጅቶች በኩል ተጨማሪ አልሚ ምግቦችን እየወሰዱ በክትትል ላይ እንደሚገኙ፤ አብዛኞቹም አሳሳቢ በሚባል ደረጃ ላይ የሚገኙ መሆኑን ኮሚሽኑ ከተፈናቃዮች፣ ከቤተሰብ አባላት፣ ከካምፕ አስተዳዳሪዎች፣ እንዲሁም ከአካባቢው የጤና ተቋማት ኃላፊዎች እና ከተራድዖ ድርጅቶች ተወካዮች ያሰባሰባቸው ማስረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ ምልከታ በተደረገባቸው መጠለያ ጣቢያዎች እና አካባቢዎች በተለይም ሕፃናት፣ አረጋውያን፣ የሚያጠቡ እናቶች፣ አካል ጉዳተኛ እና ተጓዳኝ በሽታ ያለባቸው ተፈናቃዮች ለከፍተኛ የምግብ እጥረት መጋለጣቸውን መገንዘብ ተችሏል። በዚህም የተነሳ በተለይ ሕፃናት እና አረጋውያን ቀን ላይ ከመጠለያ ውጭ በከተሞች ውስጥ እየተዘዋወሩ ምግብ ለምነው ማታ ወደ መጠለያ ጣቢያ የሚመለሱ መሆኑን፤ ወጣቶች ለስደት እና ሌሎች አሉታዊ ውጤት የሚያስከትሉ የገቢ ማግኛ አማራጮች ላይ ለመሰማራት መገደዳቸውን፤ ተጓዳኝ ወይም ቋሚ ሕመም ያለባቸው ተፈናቃዮች ከምግብ እጥረት የተነሳ የታዘዘላቸውን መድኃኒት በአግባቡ መውሰድ አለመቻላቸውን፤ መድኃኒቶቻቸውን በባዶ ሆዳቸው የሚወስዱ ወይም ለማቋረጥ የተገደዱ ተፈናቃዮች መኖራቸውን፤ እንዲሁም በመጠለያ ጣቢያዎች በተከፈቱ የሕፃናት መማሪያ ማእከላት ትምህርት ሲከታተሉ የነበሩ አብዛኞቹ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠው ምግብ ፍለጋ በከተሞች ጎዳና ለመዋል መገደዳቸውን አስረድተዋል።
በአጠቃላይ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በትግራይ ክልል ያለውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ በተመለከተም ኢሰመኮ ሲያከናውን የቆየው ክትትል ሪፖርት ተገቢው ሂደት እንደተጠናቀቀ ሪፖርቱ የሚቀርብ መሆኑን በድጋሚ ያስታውሳል።
ኢሰመኮ ክትትል ባደረገባቸው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በሶማሊ ክልል እና በጋምቤላ ክልል የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው አካባቢዎች ሁኔታው በአብዛኛው ተመሳሳይ ነው። በግጭት እና በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው ለሚገኙ ሰዎች እየቀረበ ያለው የምግብ ድጋፍ ላይ ባደረገው ክትትል ምንም እንኳን በተወሰነ ሁኔታ የምግብ ድጋፍ እየቀረበ ቢሆንም፣ ካለው የተፈናቃይ ቁጥር አኳያ የሚደረገው ድጋፍ እንደማይመጣጠን፣ በመሆኑም ድጋፉ ለሁሉም ተፈናቃዮች ተደራሽ እና በቂ አለመሆኑን ለመገንዘብ ተችሏል።
የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት ስርቆት ወይም ማሸሽ ተፈጽሟል በሚል ምክንያት ዓለም አቀፍ የተራድዖ ተቋማት በትግራይ ክልል ከመጋቢት ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ፣ በተቀረው የሀገሪቱ ክፍል ደግሞ ከሰኔ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ሲያቀርቡ የነበረውን የምግብ ድጋፍ ሙሉ ለሙሉ ካቋረጡ በኋላ፣ በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ተፈናቃዮች ቋሚ የሆነ የምግብ ድጋፍ አቅርቦት እያገኙ እንዳልነበር ይታወሳል ። ይህ የተቋረጠው የምግብ ድጋፍ በአስቸኳይ እንዲቀጥል ኢሰመኮ በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርብና ውትወታ ሲያደርግበት የቆየ ጉዳይ ሲሆን፤ የአሜሪካ የዓለም አቀፍ ልማት ድርጅት (USAID) እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) ከጥቅምት ወር 2016 ዓ.ም. ጀምሮ የምግብ ድጋፍ ለስደተኞች እንዲጀመር ማድረጋቸው በጎ እርምጃ ሆኖ፤ በአንጻሩ ለተፈናቃዮች እና ለሌሎች ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች የሚሰጠው የምግብ ድጋፍ አቅርቦት እገዳ ይህ ሪፖርት ይፋ እስከሆነበት ጊዜ ድረስ አለመነሳቱ በምግብ እጥረትና ሰብአዊ ቀውስ ላይ ያሳደረው ጫና እንደቀጠለ ነው።
የፌዴራል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በጽሑፍ ለኢሰመኮ በሰጠው ምላሽ የተሟላ እና በቂ ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ቢኖርም፣ ባለፉት ወራት በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ላሉ ተፈናቃዮች ትኩረት በመስጠት በሁለት ዙር በአፋር ክልል 96%፣ በጋምቤላ 96%፣ በትግራይ 87%፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ 73%፣ በሶማሊ 52%፣ በአማራ 43% የሰብአዊ ድጋፍ ፍላጎት መሸፈን እንደተቻለ ገልጸዋል።
ነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም. የዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት (International Organization for Migration) መድረስ የቻላቸውን አካባቢዎች መሠረት አድርጎ ባወጣው ሪፖርት በአፋር ክልል 290 ሺህ የሚሆኑ፣ በትግራይ ክልል 2.3 ሚሊዮን የሚጠጉ፣ በአማራ ክልል 1.9 ሚሊዮን እንዲሁም በኦሮሚያ ከ1.1 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮች እና ተመላሾችን የሚያስተናግዱ ክልሎች መሆናቸውን ገልጿል። በክልሎቹ አብዛኞቹ አካባቢዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች አሳሳቢ በሚባል የሰብአዊ ቀውስ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ በመሆኑ፣ ከሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት ጋር በተገናኘ የሚስተዋሉ ችግሮች በአፋጣኝ እልባት ካልተሰጣቸው አሁን ካለው የከፋ ሰብአዊ ቀውስ ሊከሰት እንደሚችል ኮሚሽኑ ያለውን ሥጋት ይገልጻል።
ይህንን በተመለከተ የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ “ተፈናቃዮች የተጋረጠባቸውን አደጋ የሚመጥን አስቸኳይ ድጋፍ ማድረግ የሁሉንም አካላት ርብርብ እና እገዛ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ የተጀመረው የምግብ ድጋፍ በከፍተኛ መጠን ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ሁሉ ተደራሽ እንዲሆን ኮሚሽኑ ለሚመለከታቸው መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ላልሆኑ ተቋማት ጥሪውን ያቀርባል” ብለዋል። ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ አክለውም “ይህንን አፋጣኝ ድጋፍ ለማመቻቸት የፌዴራል መንግሥት ሰብአዊ ድጋፍ ከሚያቀርቡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ጋር የሚያደርገውን ቅንጅት እና ትብብር ሊያጠናክር ይገባል” በማለት አሳስበዋል፡፡