የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከኢንተርናሽናል ሚዲያ ሰፖርት (International Media Support) ጋር በመተባበር ሐሳብን በነጻ የመግለጽ መብት ላይ የሚካሄድ ክትትል እና የጥላቻ ንግግር መከላከልን በተመለከተ ለኮሚሽኑ ባለሙያዎች ኅዳር 13 እና 14 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ስልጠና ሰጥቷል፡፡

በስልጠናው ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ምንነት እና በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች ላይ የተቀመጡ ገደቦች እንዲሁም በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት እና በሌሎች ሕጎች የተካተቱ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት እና የጥላቻ ንግግር ድንጋጌዎች ላይ ገለጻ ተደርጓል፡፡ ገለጻ የተደረገባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች ጨምሮ በኢትዮጵያ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት የሕግ ጥበቃ እና ተፈጻሚነት ሁኔታ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡

የስልጠናው ተሳታፊዎች

በተጨማሪም የጥላቻ ንግግርን በተመለከተ የሌሎች ሀገሮች ሕጎች እና አሠራሮች ላይ ማብራሪያ የቀረበ ሲሆን በኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግርን ለመከላከል በወጣው አዋጅ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች ዙሪያ ማብራሪያ ተሰጥቷል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የጥላቻ ንግግርን ለመከላከል መወሰድ የሚገባቸው እርምጃዎች እና የሕግ ማሻሻያዎችም ተዳሰዋል። ይህንንም ተከትሎ የስልጠናው ተሳታፊዎች ውይይት ያካሄዱ ሲሆን በተደጋጋሚ እና በስፋት ስለሚስተዋሉ የጥላቻ ንግግሮች እና የመከላከያ ዘዴዎች ሐሳቦቻቸውን አቅርበዋል።

በተያያዘም ትኩረቱን በኢትዮጵያ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት እና የጋዜጠኞች ጥበቃ ላይ ያደረገ ማብራሪያ የቀረበ ሲሆን በቅርቡ የተከናወኑ የሕግ ማሻሻያዎች፣ በተግባር የሚስተዋሉ ችግሮች እና መወሰድ የሚገባቸው እርምጃዎች ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል፡፡

ተሳታፊዎች በስልጠና ላይ

የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ሰብአዊ መብት መሆኑን እና ለሌሎች መብቶች መረጋገጥ የሚያበረክተውን አስተዋጽዖ ገልጸዋል። አክለውም ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ለማረጋገጥ የወጡ ሕጎች ተግባራዊነትን መከታትል ያለውን አስፈላጊነትና ጠቀሜታ አብራርተዋል፡፡