የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሶማሊ ክልል በወንጀል ነክ ጉዳዮች ውስጥ ገብተው የተገኙ ሕፃናት ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታን ከሕፃናት መብቶች መርሖች እና መስፈርቶች አንጻር ለመገምገም፣ የሚያጋጥሟቸውን የመብት ጥሰቶች ለመለየት እና ለመሰነድ እንዲሁም ምክረ ሐሳቦችን ለማቅረብ ባካሄደው ክትትል የተለዩ ግኝቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ታኅሣሥ 23 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ውይይት አካሂዷል።

የውይይቱ ዋና ዓላማ በወንጀል ነክ ጉዳዮች ውስጥ የተሳተፉ ሕፃናትን ሰብአዊ መብቶች ለማስከበር ባለድርሻ አካላትን አንድ ላይ በማምጣት ቀጣይ አቅጣጫ መንደፍ የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ሲሆን ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የክልሉ መንግሥት የፍትሕ አካላት ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የኢሰመኮ የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር የምስራች ለገሰ (በግራ በኩል)

በውይይቱ ሕፃናት በወንጀል ነክ ጉዳዮች ውስጥ እንዳይገቡ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው የቅድመ መከላከል ሥራዎች፤ ወንጀል ነክ የሆኑ ተግባራት ላይም በሚገኙበት ጊዜ ከመደበኛው የፍትሕ ሥርዓት ውጪ እንዲስተናገዱ የሚያስችሉ አማራጮች፣ የፍትሕና የእርምት እርምጃዎች፣ ለሕፃናት ምቹ የሆነ የፍትሕ ሥርዓት ለመዘርጋት እና ሕፃናት በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ የሚያዙበትን ሁኔታ አስመልክቶ በክትትል የተለዩ ግኝቶች እና ምክረ ሐሳቦች ቀርበዋል። በተጨማሪም ኮሚሽኑ ቀጣይነት ያለው፣ የተደራጀ እና ዘላቂ መፍትሔ ሊያስገኙ የሚያስችሉ ዝርዝር መንገዶችን አስቀምጧል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች የክትትሉ ግኝቶች በሶማሊ ክልል በወንጀል ነክ ጉዳዮች ውስጥ ገብተው የሚገኙ ሕፃናትን ነባራዊ ሁኔታ በግልጽ ያስቀመጠ መሆኑን ጠቅሰው ግኝቶቹን እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን ወደ ተቋማቸው በመውሰድ የማስፈጸም ሚናቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ጊዜ የማይሰጡ እና በአጭር ጊዜ ሊፈጸሙ የሚገቡ ምክረ ሐሳቦች ላይ በማተኮር ሥራዎችን ማከናወን እንደሚገባ ጠቁመው ለተግባራዊነቱና ውጤታማነቱ ቅንጅታዊ አሠራር እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡ በመጨረሻም በክልሉ በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ የሚያልፉ ሕፃናትን ሰብአዊ መብቶች ለማስጠበቅና በኮሚሽኑ የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን በተቀናጀ መልኩ ለማስፈጸም የሚሠራ ስምንት አባላት ያሉት ኮሚቴ በተሳታፊዎች ተዋቅሯል፡፡

የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ በምክክሩ የተገኙ ባለድርሻ አካላት ተጨባጭ እርምጃዎችን ለመውሰድ ቃል መግባታቸውና ተቀናጅቶ ለመሥራት ኮሚቴ ማዋቀራቸው መልካም ጅማሮ ነው ብለዋል፡፡ አክለውም በክልሉ ከወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት ጋር በተያያዘ በወንጀል ነክ ጉዳዮች ውስጥ ገብተው የሚያዙ ሕፃናት ሰብአዊ መብቶችን ማስከበር የመንግሥት ቀዳሚ ግዴታ ቢሆንም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ከመንግሥት ጋር በመተባበር ዘላቂ በሆኑ መፍትሔዎች ላይ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።