የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከኢትዮጵያ ሴንተር ፎር ዲሴቢሊቲ ኤንድ ዴቬሎፕመንት (ኢሲዲዲ) ጋር በመተባበር በመረቀቅ ላይ ባለው የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች አካቶ ስልት (disability inclusion strategy) ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ኅዳር 12 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ውይይት አካሂዷል፡፡ በውይይቱ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና ልዩ ልዩ የመንግሥት ተቋማት ተወካዮች እንዲሁም የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

በመረቀቅ ላይ ያለው ስልት ወደ ሥራ ሲገባ በኢሰመኮ አካል ጉዳተኞችን በተሟላ ሁኔታ ለማካተት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን ደረጃ በደረጃ እያሻሻለ እንደሚሄድ የታመነበት ሲሆን በሁሉም የኮሚሽኑ መርኃ ግብሮች፣ ፖሊሲዎች፣ ዕቅዶች እና ትግበራዎች ላይ ተፈጻሚነት ይኖረዋል። በተጨማሪም ኢሰመኮ በሚያከናውናቸው ሥራዎች ላይ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራትን ሙሉ ተሳትፎ ያረጋግጣል።

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ

በምክክሩ ስልቱን ለማርቀቅ በተካሄደው ጥናት ላይ በኢሰመኮ በተለይም በሚሰጡ አመራሮች፣ በትግበራ ወቅት፣ የኮሚሽኑ ሠራቶኞች የዕውቀትና የአመለካከት ደረጃ፣ ተደራሽነትን ከማረጋገጥ አኳያ በተሠሩ ሥራዎች እንዲሁም በበጀት እና ሀብት ማሰባሰብ ሂደት የተለዩ ጥንካሬዎች እና ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች በዝርዝር ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ባስተላለፉት መልእክት ይህ ስልት ኢሰመኮ የሚያከናውናቸውን ሥራዎች ለአካል ጉዳተኞች የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ እና አካታች ለመሆን እንዲሁም ለሌሎች ተቋማት ምሳሌ ሆኖ ለመቅረብ እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡ አክለውም ከተቋማዊ ለውጡ ወዲህ ኮሚሽኑን ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ ለማድረግ እና አካታች ለመሆን የተሠሩ ሥራዎችን በማስታወስ፤ ይህ ስልት ወደ ሥራ ሲገባ በጅምር ላይ ያሉ ሥራዎችን የበለጠ አጠናክሮ ለመቀጠል፤ አዳዲስ የአካታችነት ስልቶችን ቀይሶ ወደ ተግባር ለመግባት እንዲሁም ሥራዎች አመራሮች ላይ የተንጠለጠሉ እንዳይሆኑ ጠንካራ ሥርዓትን ለመዘርጋት እንደሚረዳ ገልጸዋል።