የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በተካሄደው ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ፤ እንዲሁም ምርጫ ማድረግ ባልተቻለባቸው ቦታዎች እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የደቡብ ምዕራብ ሕዝበ ውሳኔ በመስከረም ወር 2014 ዓ.ም. በተደረገው የምርጫ ሂደት ዙሪያ ባከናወነው የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ክትትል ረቂቅ ሪፖርት ላይ ጥቅምት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ውይይት አካሂዷል። 

በውይይቱ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተሳትፈዋል። በሪፖርቱ የተለዩ ዋና ዋና ግኝቶችን መሰረት በማድረግ ከተሳታፊዎች ግብአት የተሰበሰበ ሲሆን በክትትል ሥራዎች የተስተዋሉ ቁልፍ እመርታዎች፣ አሳሳቢ ጉዳዮች እና ምክረ ሃሳቦች ላይ ተሳታፊዎች መክረዋል፡፡

የኮሚሽኑ ክትትል በዋነኝነት የአመለካከት እና ሃሳብን በነጻነት የመያዝና የመግለጽ መብት፣ የእኩልነትና ከአድልዎ ነጻ የመሆን መብት፣ የመደራጀት መብት፣ የመዘዋወር ነጻነት፣ የመሰብሰብ እና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት፣ ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች (እኩልነትና ከአድሎ ነጻ መሆን፣ ተደራሽነት እና አካታችነት አንጻር) በቅድመ ምርጫ፣ የድምጽ መስጫ ዕለት እና ድኅረ ምርጫ ሂደቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር፡፡ 

በክትትሉ የተለዩ አዎንታዊ ግኝቶችን በተመለከተ ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ በአብዛኛው በሰላም መከናወኑ፣ ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ እንዲሆን በምርጫ ቦርድ በኩል የተደረጉ ጥረቶች እና በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻም ቢሆን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በምርጫው እንዲሳተፉ ባስቻለው ሕግ (መመሪያ ቁጥር 13/2013) አማካኝነት በምርጫው መሳተፋቸው ተጠቅሰዋል።

ሆኖም በቅድመ ምርጫ፣ በድምጽ መስጫ ዕለትም ሆነ በድኅረ-ምርጫ ወቅት የተለያዩ ክፍተቶችን ኮሚሽኑ የታዘበ ሲሆን፤ በተለያዩ ቦታዎች የፀጥታ ሥጋት ሊሆኑ ይችላሉ በሚል የበርካታ ሰዎች (በተለይ ወጣቶች) መታሰር፤ በፀጥታ ሥጋት ምክንያት አንዳንድ አካባቢዎች ምርጫው ዘግይቶ መጀመር ወይም ሳይከናወን መቅረት፤ ድምፅ ለመስጠት የተገኘው ሕዝብ ረዥም በሆነ ሰልፍ ምክንያት ለከፍተኛ እንግልት፣ ድካምና ምሬት መጋለጥ፣ በድምፅ ቆጠራ ወቅት አንዳንድ የምርጫ አስፈጻሚዎች አቅም ማነስ፣ የቅሬታ አቀራረብ ሥርዓቶች ድክመት፣ እንዲሁም በድምፅ ቆጠራ ጊዜ ምርጫ አስፈጻሚዎች ሥራ ላይ ጣልቃ የመግባት ሁኔታ ለመጪው ምርጫዎች ትኩረት የሚሹ መሆናቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል።

ተሳታፊዎች ካነሷቸው ሃሳቦች እና ግብአቶች መካከል በክትትሉ የተለዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል በርካታ የምርጫ ባለድርሻ አካላት በተለይ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከኮሚሽኑ ጋር በቅርበት ተባብሮ መሥራት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ ምርጫ በመታዘብ የተሳተፉ የሲቪል ማኅበራት በበኩላቸው ከሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን እንዲሁም የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በምርጫው ከነበራቸው ተሳትፎ እና አጠቃላይ የምርጫው ሂደት የነበረው ተደራሽነት እና አካታችነት አንጻር የተስተዋሉ ክፍተቶችን ሪፖርቱ መዳሰሱን አንስተው በቀጣይ በሁሉም ባለድርሻ አካላት ብዙ ሥራዎች በቅንጅት መሠራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ በተጨማሪም በምርጫ ወቅት የተስተዋሉ በመንግሥት እና ገዢው ፓርቲ መካከል ያሉ የተግባር መደበላለቆች፣ በተለይ የሕግ አስፈጻሚው አካል ከገዢው ፓርቲ የፖለቲካ አመራሮች ተጽዕኖ የጸዳ እንዲሆን መሥራት በቀጣይ የሚደረጉ ምርጫዎች ፍትሐዊ እና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆኑ ለማድረግ ቁልፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በመክፈቻ ንግግራቸው፤ በተሻሻለው የኢሰመኮ ማቋቋሚያ አዋጅ ከተካተቱ ዋና የኮሚሽኑ ተግባራት መካከል በምርጫ እንዲሁም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ላይ ክትትል ማድረግ አንዱ እንደሆነ ገልጸዋል። አክለውም በኮሚሽኑ የክትትል ሥራ የተለዩ ክፍተቶችን ለመሙላት ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት በቁርጠኝነት ካልሠሩ በቀጣይ ምርጫዎች ሰብአዊ መብቶች ላይ በተለይም የዜጎች የመምረጥና የመመረጥ መብት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸው እሙን ነው ብለዋል።