የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በ2015 ዓ.ም. የበጀት ዓመት የተያዙ፣ የተከሰሱ እና የሕግ ታራሚዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝን በተመለከተ በፖሊስ ጣቢያዎች፣ በኢመደበኛ ማቆያ ቦታዎች እና በማረሚያ ቤቶች ባከናወነው ክትትል የተለዩ ግኝቶች እና የሕግ ማዕቀፍ የዳሰሳ ጥናት አንኳር ግኝቶች ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ሀገር አቀፍ ውይይት ሐምሌ 7 እና 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አካሂዷል።

በውይይት መድረኮቹ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የፌዴራል እና የክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነሮች፣ የፌዴራል እና የክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነሮች፣ የፍትሕ ሚኒስቴርና የክልል ፍትሕ ቢሮ ኃላፊዎች፣ የፌዴራል እና የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ፕሬዝዳንቶች፣ የመከላከያ እና የክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊዎች እንዲሁም የሌሎች ባለድርሻ አካላት ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ኢሰመኮ በፌዴራል እና በክልል መንግሥታት በሚተዳደሩ ማረሚያ ቤቶች ባደረጋቸው ክትትሎች መሠረት የታራሚዎች የተደራጀ መረጃ አያያዝ ሥርዓት እና ዳታ ቤዝ አለመኖር፣ የምግብ፣ የሕክምና አገልግሎት እና የመድኃኒት አቅርቦት እጥረቶች የሚስተዋሉ መሆኑ ተነግሯል፡፡ በፌዴራል እና በክልሎች የተለያዩ የይቅርታ አሰጣጥ መስፈርቶች መኖራቸውና የአፈጻጸም ክፍተቶች ያሉት መሆኑም ተጠቅሷል፡፡ የታራሚዎች ማቆያ ክፍሎች የንጽሕና ጉድለት እና ከፍተኛ የሆነ መጨናነቅ እንደሚታይባቸው፤ እንዲሁም ልዩ ድጋፍና ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው ታራሚዎችን ያገናዘበ አደረጃጀት እና አሠራር የሌላቸው መሆኑ በግኝቱ ተዘርዝሯል፡፡

ከግራ ወደ ቀኝ (የኢሰመኮ የክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል ከፍተኛ ዳይሬክተር ይበቃል ግዛው፣ የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ሰላማዊት ግርማይ፣  የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ዶ/ር አለሙ ምህረቱ)
ከግራ ወደ ቀኝ (የኢሰመኮ የክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል ከፍተኛ ዳይሬክተር ይበቃል ግዛው፣ የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ሰላማዊት ግርማይ፣ የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ዶ/ር አለሙ ምህረቱ)

የታራሚዎች የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ የሕግ ማዕቀፍን በተመለከተም የተለያዩ አዋጆች፣ ደንቦች እና መመሪያዎች ጸድቀው ሥራ ላይ ውለው የሚገኙ ሲሆን ከዓለም አቀፍ ሕጎች አንጻር ጥናቱ በተካሄደባቸው የፌዴራል፣ አማራ፣ ጋምቤላ እና ኦሮሚያ ክልሎች የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ሕጎች ላይ ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ የሕግ ዳሰሳ ጥናቱ አመልክቷል፡፡ ከእነዚህ መካከል በአራቱም ማረሚያ ቤቶች ሕጎች የሕክምና አገልግሎት የማግኘት መብት በመንግሥት ሕክምና ማዕከላት ብቻ የተገደበ መሆኑ፣ በፌዴራል እና በክልሎች የማረሚያ ቤት አስተዳደር ሕጎች የአመክሮ እና የይቅርታ አሰጣጥ መስፈርቶች እና ሂደቶች ልዩነቶች የሚስተዋልባቸው መሆኑ እንዲሁም በአንድ ክልል ሥር በየደረጃው ባሉ ሕጎች መካከል አልፎ አልፎ የመፃረር ሁኔታ የሚስተዋል መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በተመሳሳይ የተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች ጥበቃን የሚገዛው የኢትዮጵያ ሕግ ማዕቀፍ ከዓለም አቀፍ ደረጃዎች አንጻር የሚሰጠውን ጥበቃ በተመለከተ የሕግ ዳሰሳ በማድረግ የተለዩ የሕግ ክፍተቶች ለውይይት ቀርበዋል፡፡ ጥናቱ ከለያቸው ዋና ዋና የሕግ ክፍተቶች መካከልም ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ቆይታ ስር እያሉ የሕግ አገልግሎት የሚያገኙበት የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩ፣ ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ማሳወቂያ ጊዜ በግልጽ አለመመልከቱ፣ የፖሊስ ማቆያ ጣቢያዎች አያያዝን በተመለከተ ለገለልተኛ አካል ቅሬታ የሚያቀርብበት ሥርዓት አለመካተቱ እንዲሁም ለተጋላጭ እና ልዩ ፍላጎት ላላቸው ሰዎች የተለየ ጥበቃ የሚሰጥ እና በፖሊስ ለተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ካሳ የሚያገኙበት የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩ የሚሉት ይገኙበታል።

በውይይቱ በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ በ384 ፖሊስ ጣቢያዎች እና ኢመደበኛ የተጠርጣሪ ማቆያ ቦታዎች እና ለኮሚሽኑ በቀረቡ 1986 የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች አቤቱታዎች ላይ በተደረገ ክትትልና ምርመራ የተለዩ ግኝቶች ቀርበዋል። በአወንታዊ መሻሻሎች ከተገለጹት መካከል በአብዛኞቹ ፖሊስ ጣቢያዎች ተጠርጣሪዎች በአግባቡ የሚመዘገቡ መሆኑ፣ ተጠርጣሪዎች ከቤተሰቦቻቸው እና ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር እንዲገናኙ መደረጉ፣ ያላግባብ እስር ላይ የነበሩ በርካታ ተጠርጣሪዎች መፈታታቸው፣ በአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ እና ሌሎች የተወሰኑ ፖሊስ ጣቢያዎች የደኅንነት ካሜራዎች አገልግሎት ላይ መዋላቸው፣ በአሶሳ ሕፃናትን የያዙ እና ነፍሰጡር እናቶች በቁጥጥር ሥር ሲውሉ  በልዩ ሁኔታ ጉዳያቸው ታይቶ በዋስ እንዲፈቱ የሚደረግበት አሠራር መኖሩ እንዲሁም ኢሰብአዊ አያያዝ የፈጸሙ የተወሰኑ የፖሊስ አባላት ተጠያቂ መደረጋቸው ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

በተመሳሳይ የአዲስ አበባ፣ የአመያ ከተማ ፖሊስ ጽ/ቤት እና የመስቃን ወረዳ ፖሊስ ጣቢያዎች እና ሌሎች የተወሰኑ ፖሊስ መምሪያዎች የራሳቸው የሕክምና መስጫ ክሊኒክ ያላቸው መሆኑ፣ በተወሰኑ ፖለስ ጣቢያዎች ምግብ የሚቀርብ መሆኑ እንዲሁም በአማራ ክልል በየደረጃው የሚገኙ ፍርድ ቤቶች ተጠርጣሪዎችን ወደማረሚያ ቤት ሲልኩ ጊዜ በመወሰን ሊሆን እንደሚገባ በጠቅላይ ፍ/ቤት ሰርኩላር መተላለፉ በአዎንታዊነት ከተጠቀሱ አሠራሮች መካከል ይገኛሉ።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ

በሌላ በኩል የዘፈቀደና ሕገ-ወጥ እስራት በስፋት መቀጠሉ፣ አብዛኛዎቹ ተጠርጣሪዎች ስለተጠርጠሩበት ወንጀል በአግባቡ የማይነገራቸው መሆኑ እና በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸው፣ የፍርድ ቤትን የዋስትና ውሳኔ አለማክበር፣ ለመንግሥት ኃላፊዎች እና ተሿሚዎች በሕግ የተሰጣቸው ልዩ ጥበቃ በሕጋዊ መንገድ ሳይነሳ ማሰር፣ “ወቅታዊ ሁኔታ” በሚል የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን፣ የሚዲያ ባለሙያዎችን እና የማኀበረሰብ አንቂዎች ላይ ከሕግ ውጭ የተራዘመ የቅድመ-ክስ እስራት መፈጸም፣ የተያዙ ሰዎችን መደበኛ ባልሆኑ ቦታዎች ማቆየት እና ከአስተዳደር አካላት በሚሰጡ ትእዛዞች ሰዎችን የማሰር ድርጊቶች በአሉታዊ ከተጠቀሱ ግኝቶች መካከል ይጠቀሳሉ። በተጨማሪም ሰዎችን አስገድዶ መሰወር፣ በአንዳንድ ጣቢያዎች በተጠርጣሪዎች ላይ ድብደባ፣ ግርፋት እና ሌሎች ኢሰብአዊ ድርጊቶች የሚፈጸሙ መሆናቸው አሳሳቢ ሆነው ከቀጠሉ ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል። በአብዛኞቹ የፖሊስ ጣቢያዎች የማቆያ ክፍሎች የመሠረታዊ አቅርቦትና አገልግሎት በቂ አለመሆኑ፣ በአንዳንድ ጣቢያዎች በራስ ወጪ ለመታከም ፈቃድ መከልከሉ እንዲሁም ተጠርጣሪዎችን በዕድሜ እና በጾታ ለይቶ ያለመያዝ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውም ተገልጿል፡፡

የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች ለወንጀል ምርመራ ፍርድ ቤቶች የሚሰጡትን የጊዜ ቀጠሮ ታሳቢ በማድረግ የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት ለተጠርጣሪዎች ማቆያ ተገቢውን በጀት እንዲበጅቱ ኢሰመኮ ግፊት እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ አክለውም የማረሚያ ቤቶች የሕግ ዳሰሳው የጠቆማቸው ምክረ ሐሳቦች በፌዴራል እና በክልሎች በረቂቅ ደረጃ ላይ በሚገኙ ሕጎች ውስጥ ተካተው በአስቸኳይ ቢወጡ እና ሥራ ላይ ቢውሉ የታራሚዎችን ሰብአዊ መብቶች ከማረጋገጥ አንጻር ጉልህ አስተዋጽዖ ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በበኩላቸው ከበጀት ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው የታራሚዎች የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶችን ለማክበር ቀና ፍላጎት እና የሕግ ተገዢነት ብቻ የሚፈልጉ መሆናቸውን አንስተው፤ ከበጀት ጋር ተያይዘው የሚስተዋሉ ጉድለቶችን በሚመለከት ከመንግሥት አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት፣ አማራጭ የቅጣት አሰጣጥ ውሳኔዎች በፍርድ ቤቶች የሚሰጡበትን እና በሰፊው ሥራ ላይ የሚውሉበትን መንገድ መፈለግ እንደሚገባ ገልጸዋል። አክለውም  በረቂቅ ደረጃ ያሉትን ሕጎች በፍጥነት በማጽደቅ ወደሥራ የሚገቡበትን ሁኔታ መፍጠር ይገባል ያሉት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ ተቋማት የኮሚሽኑን ምክረ ሐሳቦች ዓመታዊ ዕቅዳቸው ውስጥ በማካተት እንዲተገብሩ አሳስበዋል።