የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ በትግራይ ክልል ያለውን አጠቃላይ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን በተመለከተ ከተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት (Office of the High Commissioner for Human Rights-OHCHR) ጋር በመተባበር በተለያዩ የመብት ዘርፎች ዙሪያ ከሰኔ 30 እስከ ሐምሌ 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ያከናወነውን የክትትል ሥራዎችን በተመለከተ ባለ 40 ገጽ ሪፖርት የካቲት 12 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። በዚህ ክትትል በክልሉ አራት ዞኖች ማለትም በማእከላዊ ዞን፣ በሰሜን ምዕራብ ዞን፣ በደቡብ ዞን፣ በደቡብ ምሥራቅ ዞን እና በመቀሌ ከተማ የሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ላይ ተጨማሪ የክትትል ሥራ ማከናወኑን እና ይህንንም በተመለከተ ዝርዝር ሪፖርት ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቆም ነበር።

በዚህም መሠረት ዝርዝር ሪፖርቱን እና ተጨማሪ የክልሉ አካባቢዎች የሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ለመረዳት እና በተለይም በዘላቂ መፍትሔዎች አተገባበር ዙሪያ አዎንታዊ ተግባራትን እና ክፍተቶችን በመለየት በሚመለከታቸው አካላት ተገቢው የእርምት እርምጃዎች እንዲወሰዱ ለማስቻል፣ ኮሚሽኑ ከጥቅምት 29 እስከ ኅዳር 10 ቀን 2016 ዓ.ም. በክልሉ በምሥራቅ ዞን፣ በማእከላዊ ዞን እና በመቀሌ ዞን በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በተመለከተ ከዚህ በታች የቀረበውን ተጨማሪ ሪፖርት ይፋ አድርጓል።

ተፈናቃዮች በቂ የሰብአዊ ድጋፍ እየቀረበላቸው አለመሆኑ፣ ለከፍተኛ የመጠለያ ችግር ተዳርገው የሚገኙ መሆኑ፣ በተለይም አብዛኛዎቹ ተፈናቃዮች በትምህርት ቤቶች ውስጥ ጊዜያዊ መጠለያ በተፋፈገ ሁኔታ እንዲኖሩ መደረጉ፣ የሕክምና እና የትምህርት አገልግሎቶችን በተሟላ ሁኔታ የማያገኙ መሆኑ፣ ልዩ ድጋፍ ለሚሹ ተፈናቃዮች የሚደረግ የተለየ ጥበቃና ድጋፍ አለመኖሩ እንዲሁም ለተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ በመፈለግ ሂደት ክፍተቶች መኖራቸው በሪፖሪቱ ከተለዩ አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል ናቸው፡፡

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ “ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃ እና ድጋፍ ስምምነት (የካምፓላ ስምምነት) ተቀብላ ያጸደቀች እንደመሆኗ፤ የሚመለከታቸው የፌዴራል እና የክልሉ መንግሥታት እንደአስፈላጊነቱ ለጋሽ ድርጅቶችን በማስተባበር የተፈናቃዮችን ደኅንነትና ሰብአዊ ክብር በጠበቀ ሁኔታ እንዲሁም በፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የዘላቂ መፍትሔ አማራጮችን ተግባራዊ ለማድረግ በቁርጠኝነት እና በቅንጅት መሥራት ይኖርባቸዋል” ብለዋል። አክለውምዘላቂ መፍትሔ እስኪመቻች ድረስም ተፈናቃዮች በቂ፣ ወቅቱን የጠበቀ እና ተደራሽ የሆነ የሰብአዊ ድጋፍ ሊቀርብላቸው እንዲሁም በቂ መጠለያ ሊመቻችላቸው ይገባል” በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

ዝርዝር መረጃዎች

መግቢያ

1. ከሐምሌ 3 እስከ 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በተከናወነው የክትትል ሥራ ወቅት የተሸፈኑ ሥፍራዎች፦

ሀ. በማእከላዊ ዞን ስር፦ በአክሱም፣ ዓደዋ፣ እንጥጮ፣ ራማ፣ ቆላ ተምቤን ወረዳ ጉያ ቀበሌ እና በዓብይ ዓዲ ከተማ ዓብይ ዓዲ ቴክኒክ እና ሞያ ማሰልጠኛ፤
ለ. በሰሜን ምዕራብ ዞን፦ በሽረ ከተማ፣ በዓዲ ዳእሮ፣ ዓዲ ሀገራይ (መማእከላይ አዲያቦ)፤ በሽራሮ ከተማ፣ በእንዳጋቡና ወረዳ፤
ሐ. በደቡባዊ ዞን ስር፦ በማይጨው፣ እንዳመኾኒ፣ ቦራ ሰላዋ፣ መኾኒ (ራያ ዘቦ)፣ ዓዲ ሽሁ እና ኣምባላጀ  ወረዳዎች፤
መ. በደቡብ ምሥራቃዊ ዞን በሕንጣሎ፣ ዓዲ ጉዶም እና ሰሓርቲ ወረዳዎች፤
ሠ. በመቀሌ ዞን መቀሌ ከተማ፦ ሰባ ካሬ መጠለያ፣ ዓዲ ሐውሲ እና ዓዲ ሐቂ መጠለያ ጣቢያዎች ሲሆኑ፤

2. ከጥቅምት 29 እስከ ኅዳር 10 ቀን 2016 ዓ.ም. በተከናወነው የክትትል ሥራ የተሸፈኑት ተጨማሪ አካባቢዎች፥

ሀ. በማእከላዊ ዞን አክሱም ከተማ፦ ቀዳማዊ ሚኒልክ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት እና አክሱም 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያዎች፤
ለ. በማእከላዊ ዞን ዓድዋ ከተማ:- ንግስተ ሳባ መሰናዶ ት/ቤት የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ፤
ሐ. በምሥራቅ ዞን ዓዲግራት ከተማ፦ ፍኖተ ብርሃን 2ኛ ደረጃ ት/ቤት እና የድሮ አየር መንገድ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያዎች፤
መ. በምሥራቅ ዞን ውቕሮ ከተማ:- ውቕሮ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያ፤
ሠ. በመቀሌ ዞን መቀሌ ከተማ:- በኲሓ ክፍለ ከተማ፣ በመቀሌ ጤና ጣቢያ እና ማይ ወይኒ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የሚገኙ የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች ናቸው፡፡

3. ኮሚሽኑ በሁለቱም ዙር የተከናወኑ የክትትል ሥራዎችን ያካሄደው አግባብነት ያላቸውን የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሰነዶች እና ሕጎች በተለይም አህጉራዊ የሆነው እና ኢትዮጵያ ያጸደቀችውን የአፍሪካ ኅብረት የሀገር ውስጥ የተፈናቃዮች ጥበቃ እና ድጋፍ ስምምነት (የካምፓላ ስምምነት)፣ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትን እና ብሔራዊ ሕግጋትን መሠረት በማድረግ ነው፡፡

4. በእነዚህ የክትትል ሂደቶች ኮሚሽኑ በአጠቃላይ ጾታን፣ ዕድሜን እና የአካል ጉዳትን መሠረት ያደረጉ በድምሩ 26 የቡድን ውይይቶችን ከተፈናቃዮች እና የተቀባይ ማኅበረሰብ አባላት ጋር ያደረገ ሲሆን፤ ከሚመለከታቸው 32 የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የጤና ተቋማት ኃላፊዎች፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ዓለም አቀፍ የተራድዖ ድርጅቶች የሥራ መሪዎች፣ እና የሲቪል ማኅበራት ተወካዮች ጋር ቃለ መጠይቆች እና የተናጠል ውይይቶች በማድረግ እንዲሁም የሰነድ ማስረጃዎችን በማሰባሰብና በመጠለያ ጣቢያዎቹም ምልከታ በማድረግ መረጃና ማስረጃዎችን ሰብስቧል።

5. ኢሰመኮ ይህንን ክትትል ሲያካሂድ የተጠቀመው የማስረጃ ምዘና ደረጃ በተመሳሳይ የክትትል ሥራዎች የሚጠቀመውን ‘ምክንያታዊ ጥርጣሬ’ ተብሎ የሚታወቀውን የማስረጃ ምዘና መስፈርትን ሲሆን ይኸውም ድርጊቱ መፈጸሙን ወይም መድረሱን የሚያጠራጥሩ ሁኔታዎች መኖራቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ማቅረብ ሲቻል ነው። በዚህም መሠረት በአንድ ቀጥተኛ ከሆነ ምንጭ ተፈጸመ ወይም ደረሰ የተባለ ድርጊት ወይም የሰብአዊ መብት ጥሰት ቢያንስ በሌላ በአንድ ነጻ ወይም ገለልተኛ እና ተዓማኒ የሆነ ምንጭ ሲረጋገጥ ነው።

6. ይህ ሪፖርት ኢሰመኮ ከተ.መ.ድ. የሰብአዊ መብቶች ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ከሐምሌ 12 እስከ 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በትግራይ ክልል ሰሜን ምዕራብ፣ ደቡብ፣ ደቡብ ምሥራቅ ዞኖች እና መቀሌ ከተማ የሰብአዊነት ሁኔታን በተመለከተ ያደረገውን ክትትል ተከትሎ ታኅሣሥ ወር 2016 ዓ.ም. ያወጣው ሪፖርት ላይ በተጨማሪነት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ላይ ትኩረት አድርጎ የተዘጋጀ ነው።

7. ከትግራይ ክልል አደጋና ሥጋት ሥራ አመራር ቢሮ በተገኘው መረጃ መሠረት ይህ ክትትል እስከተከናወነበት ጊዜ ድረስ (ጥቅምት 29 እስከ ኅዳር 10 ቀን 2016 ዓ.ም. ባለው ጊዜ) በትግራይ ክልል 950 ሺህ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ የሚገመት ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል 78,956 ተፈናቃዮች በማእከላዊ ዞን፣ 61,492 ተፈናቃዮች በምሥራቅ ዞን፣ 20,548 ተፈናቃዮች በመቀሌ ከተማ፣ በአጠቃላይ በ5 ከተሞች ወደ 161 ሺህ የሚጠጉ ተፈናቃዮች በክትትሉ ተሸፍነዋል።

በክትትሉ የተካተቱ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የመጡባቸው አካባቢዎች

8. ተፈናቃዮች ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በሕወሓት እና በፌዴራል መንግሥት መካከል በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት ከቃፍታ ሑመራ፣ ወልቃይት፣ ፀገዴ፣ ሰቲት እና ማይ ካድራ፣ ታሕታይ ኣድያቦ፣ ሽራሮ፣ ጸለምቲ፣ ሓውዜን፣ ጋንታ ኣፈሹም፣ ግሎመከዳ፣ ኢሮብ፣ አላማጣ፣ ኮረም፣ ኦፍላ፣ ራያ አላማጣ እንዲሁም ከማእከላዊ ትግራይ አካባቢዎች እና ከአፋር ክልል የተፈናቀሉ መሆኑን ለኮሚሽኑ አስረድተዋል፡፡

የሕግ ማዕቀፍ

9. በካምፓላ ስምምነት በተሰጠው ትርጓሜ መሠረት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ማለት በትጥቅ ግጭት፣ በመጠነ ሰፊ ብጥብጦች፣ በሰብአዊ መብት ጥሰቶች ወይም በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ወይም እነዚህ ክስተቶች በሚያስከትሏቸው ውጤቶች የተነሳ ከሚኖሩበት ቤት ወይም ከመደበኛ የመኖሪያ ቦታቸው እንዲሸሹ ወይም ለቀው እንዲወጡ የተገደዱ ነገር ግን የኢትዮጵያን የግዛት ወሰን ተሻግረው ያልተሰደዱ ሰዎች ወይም ቡድኖች ናቸው።

10. በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢ.ፌ.ዴ.ሪ.) ሕገ መንግሥት አንቀጽ 89(3) በተደነገገው መሠረት መንግሥት የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች እንዳይደርሱ የመከላከል እና አደጋዎች በሚደርሱበት ጊዜም ለተጎጂዎች የሰብአዊ ድጋፍ በወቅቱ እንዲደርስ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሀገሪቱ ዜጎች እንደመሆናቸው ያለ አድልዎ ለዜጎች ተፈጻሚ የሚሆኑ መብቶቻቸው ይከበርላቸዋል፤ እንዲሁም በመፈናቀላቸው ከደረሰበቻው ሁኔታ አንጻር ድጋፍና ጥበቃ ይደረግላቸዋል፡፡

11. የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕግ እና በትጥቅ ግጭት ወቅት ደግሞ በዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ ጥበቃ ይደረግላቸዋል። በአህጉር ደረጃ የአፍሪካ ኅብረት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃ እና ድጋፍ ስምምነት (የካምፓላ ስምምነት ተብሎ የሚታወቀው) (African Union Convention for the Protection and Assistance of Internally Displaced Persons in Africa) አስገዳጅ ሕግ ሲሆን፤ በግጭት፣ በተፈጥሮ አደጋ እና ሰው ሰራሽ በሆኑ ምክንያቶች ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች በመንግሥት ጥበቃ እንዲደረግላቸው ያስገድዳል፡፡ የዚህ ስምምነት ግዴታ መንግሥትን ብቻ ሳይሆን የታጠቁ ሌሎች አካላት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጭምር ይህን ግዴታ እንዲያከብሩ ያስገድዳል (አንቀጽ 7)።

12. ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ተገቢውን ጥበቃ ለማድረግ እንዲያስችል በ2012 ዓ.ም. በወጣው የካምፓላ ስምምነት ማጽደቂያ አዋጅ ቁጥር 1187/2012 መሰረት ኢትዮጵያ የካምፓላ ስምምነትን አጽድቃለች፡፡ ይህ በአፍሪካ የሀገር ውስጥ መፈናቀልን ለመከላከል እና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ለመጠበቅና ለመደገፍ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት አንቀጽ 9(4) መሠረት የሀገሪቱ ሕግ አካል ነው፡፡

13. በካምፓላ ስምምነት መሠረት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ምንም ዓይነት መድልዎ ሳይደረግባቸው ያላቸውን መብቶች ለማክበር፣ ለማስከበር፣ እና ለማሟላት መንግሥት ቀዳሚ ኃላፊነት ተጥሎበታል (አንቀጽ 3 (1))፡፡

የክትትሉ ዋና ዋና ግኝቶች

የመመዝገብ እና ሰነድ የማግኘት መብቶች

14. መንግሥት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በሙሉ የሚመለከት መዝገብ ማደራጀትና ወቅታዊ መረጃዎችን መያዝ እንዳለበት፤ እንዲሁም የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መብቶቻቸውን መጠቀም እና መተግበር እንዲችሉ የሚያስፈልጓቸውን እንደ ፓስፖርት፣ የግል መታወቂያ፣ የሲቪል ምስክር ወረቀት፣ የልደት የምስክር ወረቀት እና የጋብቻ የምስክር ወረቀት የመሳሰሉ ሰነዶችን እንዲያገኙ ሊያደርግ እንደሚገባ በካምፓላ ስምምነት አንቀጽ 13 ተደንግጓል፡፡

15. ክትትል በተደረገባቸው ቦታዎች ከተወሰኑት መጠለያ ጣቢያዎች/ጊዜያዊ ማቆያዎች በስተቀር በአብዛኛዎቹ መጠለያዎች ሁሉንም ተፈናቃዮች ባካተተ መልኩ በጾታ፣ በዕድሜ፣ በአካል ጉዳት፣ ልዩ ድጋፍ የሚያሻቸውን ተፈናቃዮች እንዲሁም ተጓዳኝ ሕመም ያለባቸውን የሚገልጽ የተሰባጠረ መረጃ የያዘ መዝገብ የተደራጀ ሲሆን፤ መረጃዎች በየጊዜው ወቅታዊ የሚደረጉ መሆኑንና በዚህም አዲስ የተወለዱ፣ የሞቱ፣ ወደ ሌላ ቦታ የተዛወሩ/በራሳቸው የሄዱ፣ የተመለሱ ተፈናቃዮች መረጃ በየጊዜው ወቅታዊ የሚደረግ መሆኑን ኮሚሽኑ የተፈናቃዮች የመረጃ መዝገቦችን እና ቅጾችን ጭምር በመመልከት ለማረጋገጥ ችሏል።

16. ኮሚሽኑ ባደረገው ክትትል አብዛኛዎቹ ተፈናቃዮች ጊዜያዊ የመታወቂያ ካርድ የተሰጣቸው ሲሆን፤ የወሳኝ ኹነት አገልግሎቶችን ግን የማያገኙ መሆኑን ለኮሚሽኑ አስረድተዋል፡፡

የጸጥታ፣ በደኅንነት የመጠበቅ እና ፍትሕ የማግኘት መብት

17. መንግሥት ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ያለምንም ዓይነት መድልዎ ጥበቃ የማድረግ እና አጥጋቢ በሆነ ደኅንነት፣ ሰብአዊ ክብር እና ጸጥታ እንዲኖሩ ለማስቻል አስፈላጊ እርምጃዎችን የመውሰድ ግዴታ አለበት (የካምፓላ ስምምነት አንቀጽ 9(2)(ሀ))፡፡

18. በክትትሉ በተሸፈኑ አካባቢዎች ተፈናቃዮች አሁን በሚገኙበት አካባቢ የደኅንነት ሥጋት የሌለባቸው መሆኑን፣ በተለይም ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ በክትትሉ በተሸፈኑ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የጸጥታ እና ደኅንነት ሥጋቶች አለመኖራቸውን እና ተፈናቃዮች በመጠለያ ጣቢያ ውስጥም ሆነ ከመጠለያ ጣቢያ ውጭ ያለሥጋት በነፃነት የሚንቀሳቀሱ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

19. ተፈናቃዮች በጦርነቱና በመፈናቀል ሂደት የተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የደረሰባቸው መሆኑን፣ የሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት መድረሱን፣ ከእነዚህም መካከል አርሶ አደሮች ‘የትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች ናችሁ’ በሚል እንደተገደሉ፣ በተናጠል እና በቡድን ሆኖ ሴቶች መደፈራቸውን እና በተደፈሩ ሴቶች ላይ ጭካኔ የተሞላባቸው ድርጊቶች መፈጸሙን፣ ተገደው የተሰወሩ ሰዎች መኖራቸውን፣ የግለሰቦች ቤትና ንብረት መዘረፉና መውደሙን፣ እንዲሁም ሌሎች አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸሙን ተፈናቃዮች ለኮሚሽኑ አስረድተዋል። ሆኖም ተፈናቃዮች ለደረሰባቸው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ፍትሕ ያላገኙ መሆኑ ለበለጠ ጉዳትና ለአዕምሮ ጤና መታወክና ጭንቀት የዳረጋቸው መሆኑን ተፈናቃዮች ጨምረው አስረድተዋል፡፡

ሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት

20. ለተፈናቃዮች በመንግሥት እና በተራድዖ ድርጅቶች በኩል ጥበቃ እና ድጋፍ መደረግ እንዳለበት በካምፓላ ስምምነት ተደንግጓል፡፡ የመንግሥት ግዴታዎች በአንቀጽ 5 እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ከሰብአዊ ዕርዳታ ድርጅቶች ጋር የተያያዙ ግዴታዎች በአንቀጽ 6 ተዘርዝረዋል፡፡

21. ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በቂ ምግብ፣ ውሃ፣ መጠለያ፣ የሕክምና እንክብካቤ እና ሌሎች የጤና አገልግሎቶች፣ ንጽሕና፣ ትምህርት እና ሌሎች አስፈላጊ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ያካተተ በቂ የሰብአዊ ድጋፍ ማቅረብ እና ተገቢ ሆኖ ሲገኝ እነዚህን ዓይነት ድጋፎች ለአካባቢውና ለተፈናቃዮች ተቀባይ ማኅበረሰቦች እንዲደርስ ማድረግ የመንግሥት ተቀዳሚ ግዴታ መሆኑ በካምፓላ ስምምነት አንቀጽ 9 (2) (ለ) ተደንግጓል።

22. መንግሥት ለተፈናቃዮች የሚያደርገውን የሰብአዊ ድጋፍ በራሱ አቅም ማቅረብ ባይችል ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና የሰብአዊ እርዳታ ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ሌሎች አግባብነት ያላቸው ተዋንያን ድጋፍ በማሰባሰብ ግዴታውን መወጣት እንዳለበት በስምምነቱ አንቀጽ 9(3) ተደንግጓል፡፡

23. ከሐምሌ 3 እስከ 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በተከናወነው የመጀመሪያ ዙር ክትትል በተሸፈኑት አካባቢዎች የምግብ ድጋፍ አቅርቦት ለተከታታይ ሰባት ወራት ድረስ ተቋርጦ የነበረ ሲሆን በወቅቱም ምንም ዓይነት የምግብ ድጋፍ አልቀረበም ነበር፡፡ ከምግብ አቅርቦት እጥረቱ ጋር በተያያዘም የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ እስከ ሐምሌ 2015 ዓ.ም. በነበሩት ጊዜያት ወደ 1000 የሚሆኑ ሰዎች በአብዛኛው ሕፃናት እና እናቶች ከምግብ እጥረት ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው ማለፉን በወቅቱ የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች የገለጹ ሲሆን ኮሚሽኑ ይህንን ሁኔታና አሃዝ በራሱ ገለልተኛ ምርመራ አላረጋገጠም።

24. በተመሳሳይ በክልሉ ከምግብ ድጋፍ አቅርቦት መቋረጥ ጋር በተገናኘ የነበረውን ሁኔታ ኮሚሽኑ ጥቅምት 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫም እንደገለጸው በክልሉ መንግሥት የተጠቀሰ አንድ ጥናት ላይ እንደተመለከተው፤ በ5 ከተሞች በሚገኙት 53 የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች እንደ ናሙና ተወስዶ ተደርጓል በተባለው ጥናት፣ ቢያንስ 1,329 ተፈናቃዮች በምግብ እጥረት መሞታቸው ተገልጾ የነበረ ሲሆን፤ ኮሚሽኑ የዚህን ጥናት ግኝት በራሱ ገለልተኛ ምርመራ አላረጋገጠም፡፡ ሆኖም አጠቃላይ ሁኔታው የጉዳዩን በከፍተኛ ሁኔታ አሳሳቢነት የሚያሳይ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።

25. በተጨማሪም ወደ 1 ሺህ የሚጠጉ ዕድሜያቸው ከ1 እስከ 5 ዓመት የሆኑ ተፈናቃይ ሕፃናት ለከፍተኛ የምግብ እጥረት (Malnutrition) መጋለጣቸው እንደተለየ እና በተወሰኑ የጤና ተቋማት እና የረድኤት ድርጅቶች በኩል ተጨማሪ አልሚ ምግቦችን እየወሰዱ በክትትል ላይ እንደሚገኙ፤ አብዛኞቹም አሳሳቢ በሚባል ደረጃ ላይ የሚገኙ መሆኑን ኮሚሽኑ ከተፈናቃዮች፣ ከቤተሰብ አባላት፣ ከካምፕ አስተዳዳሪዎች፣ እንዲሁም ከአካባቢው የጤና ተቋማት ኃላፊዎች እና ከተራድዖ ድርጅቶች ተወካዮች በክትትሉ ወቅቱ ያሰባሰባቸው ማስረጃዎች ያሳያሉ።

26. ኮሚሽኑ ከጥቅምት 29 እስከ ኅዳር ወር 2016 ዓ.ም. ባከናወነው ሁለተኛ ዙር ክትትል በተሸፈኑ አካባቢዎች በመስከረም ወር 2016 ዓ.ም. የምግብ ድጋፍ ከፌዴራል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን መቅረብ የጀመረ መሆኑን ተረድቷል። ነገር ግን አቅርቦቱ ስንዴ እና እጅግ ውስን የምግብ ዘይት ድጋፍ ብቻ መሆኑንና ለሁሉም ተፈናቃዮች እንዳልተዳረሰ ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው ተፈናቃዮች እና የመንግሥት ኃላፊዎች ለኮሚሽኑ ገልጸዋል።

27. በመሆኑም በክልሉ የሚገኙ ተፈናቃዮች የምግብ ድጋፍ ተቋርጦ በቆየባቸው ጊዜያትና ከተጀመረም በኋላም ለሁሉም ተደራሽ ባለመሆኑ ተፈናቃዮች የከተማው ማኅበረሰብ እንዲሁም አልፎ አልፎ የግል ባለሀብቶች እና የተራድዖ ድርጅቶች በሚሰጧቸው የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ ሲረዱ እንደቆዩ ለኮሚሽኑ አስረድተዋል። በረሃብ እንዲሁም ሕክምና ባለማግኘት የተነሳ በሕይወት ላይ ጭምር ጉዳት ደርሶ ሊሆን እንደሚችል፣ በምግብ እጥረት የተጎዱ ሕፃናት፣ የሚያጠቡ እናቶች፣ አረጋዊያንና ተጓዳኝ ሕመም ያለባቸው ተፈናቃዮች መኖራቸውን የሕክምና ባለሙያዎችን በማነጋገር እንዲሁም በመጠለያ ጣቢያዎች በተደረገ ምልከታ ለመረዳት ተችሏል፡፡

28. በተመሳሳይ፤ ተፈናቃዮች ከፍተኛ ለሆነ የመጠለያ ችግር ተዳርገው የሚገኙ መሆኑን ኮሚሽኑ በክትትሉ ለመገንዘብ ችሏል። በክትትሉ በተሸፈኑ አካባቢዎች አብዛኛዎቹ ተፈናቃዮች በት/ቤቶች ተጠልለው የሚገኙ ሲሆን ቀሪዎቹ በጤና ጣቢያ እና በአንድ ግለሰብ የብሎኬት ማምረቻ መጋዘን ውስጥ ይገኛሉ፡፡

29. አብዛኞቹ ተፈናቃዮች በትምህርት ተቋማት መማሪያ ክፍሎች የተጠለሉ ሲሆን በአንድ የመማሪያ ክፍል ውስጥ በአማካይ ከ8 እስከ 10 ቤተሰቦች ወይም ከ60 በላይ ሰዎች በተፋፈገ ሁኔታ የሚኖሩ መሆኑን ኮሚሽኑ ተመልክቷል፡፡ ይህም ተፈናቃዮችን ለልዩ ልዩ ተላላፊ በሽታዎች ያጋለጣቸው ሲሆን፣ በተጨማሪም ሴቶች ከወንዶች ጋር፤ በተለይም ከማያውቋቸው ወንዶች ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ እንዲኖሩ መደረጉ በተለይም ሕፃናት ሴቶች ለፆታዊ ጥቃት ተጋላጭ ያደርጋቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ትምህርት ሊጀመር ስለሆነ ትምህርት ቤቱን ለቀው እንዲወጡ እየተነገራቸው መሆኑንና በአንዳንድ ት/ቤቶች ደግሞ ከፍተኛ በሆነ መጨናነቅ ተሸጋሽገው እንዲኖሩ እንደተደረገና በተፈናቃዮች በተለቀቁ የተወሰኑ ሕንጻዎች ትምህርት በፈረቃ መሰጠት መጀመሩን ኮሚሽኑ ተመልክቷል፡፡ በመቀሌ ከተማ በጤና ጣቢያ ግቢ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮችም ጤና ጣቢያው አገልግሎት መስጠት ሊጀምር ስለሆነ ከጤና ጣቢያው ለቀው እንዲወጡ እንደተነገራቸው ለኮሚሽኑ አስረድተዋል፡፡

30. ኮሚሽኑ ሁለተኛውን ዙር ክትትል ባከናወነበት ወቅት ከክልሉ አደጋና ሥጋት ሥራ አመራር ቢሮ በተገኘው መረጃ መሠረት በትግራይ ክልል 110 ት/ቤቶች የተፈናቃይ መጠለያዎች የተደረጉ ሲሆን፣ ይህም የትምህርት አገልግሎትን እንዳስተጓጎለና በትምህርት ሥርዓቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ኮሚሽኑ ተገንዝቧል፡፡ ተፈናቃይ ተማሪዎች በከፊል ትምህርት በጀመሩ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ቢሆንም በምግብ እና በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ትምህርታቸውን በአግባቡ ለመከታተል መቸገራቸውን የተማሪዎች ወላጆች ለኮሚሽኑ ገልጸዋል፡፡

31. ከትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር በተላለፈው መመሪያ መሠረት ሁሉም ተፈናቃዮች ነፃ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ነፃ የሕክምና ካርድ የተሰጣቸው ቢሆንም መድኃኒት በጤና ጣቢያዎችም ሆነ ሆስፒታሎች የማያገኙ መሆኑንና መድኃኒት ከግል ፋርማሲዎች ለመግዛት አቅም ስለሌላቸው በተለይም የስኳር ሕመም ያለባቸው ሰዎች ጊዜው ያለፈበትን መድኃኒት ጨምሮ ለመጠቀም መገደዳቸውን ለኮሚሽኑ ገልጸዋል፡፡

32. ኮሚሽኑ ካነጋገራቸው ተፈናቃዮች መካከል የመንግሥት ሠራተኞች፣ አስተማሪዎች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ የፌዴራል ተቋማት ሠራተኞች እንዲሁም ጡረተኞች የሚገኙ ሲሆን፣ ከሁለት ዓመታት በላይ ደመወዝ እንዳልተከፈላቸው፤ በዚህም መሠረታዊ የሆኑ ፍላጎታቸውን እንኳን ማሟላት አቅቷቸው ለከፍተኛ ችግር ተዳርገው የሚገኙ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ተፈናቃዮች

33. ልዩ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በተለይም ከቤተሰባቸው ለተለዩ እና ብቻቸውን ላሉ ሕፃናት፣ ለሴት የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች፣ ለነፍሰጡሮች፣ ሕፃናት ልጆች ላሏቸው እናቶች፣ ለአረጋውያን እና ለአካል ጉዳተኞች ወይም ተላላፊ በሽታ ላለባቸው ሰዎች ልዩ ጥበቃ እና ድጋፍ እንዲያደርግ መንግሥት ግዴታ አለበት፡፡ በተጨማሪም መንግሥት ለሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ሴቶች የሥነ-ተዋልዶና የሥርዓተ ጾታ ጤና አገልግሎትን እንዲሁም የጾታ እና ሌሎች ተያያዥ ጥቃቶች ለደረሰባቸው ተገቢውን የሥነ-ልቦና እና ማኅበራዊ ድጋፍ ለመስጠት እና ጥበቃ ለማድረግ ልዩ እርምጃ ይወስዳል በማለት በካምፓላ ስምምነት ተደንግጓል (አንቀጽ 9/2/ሐ/መ)፡፡

34. ክትትል በተደረገባቸው ቦታዎች ልዩ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ተፈናቃዮች ለሕፃናት፣ ሴቶች፣ አረጋዊያን እና አካል ጉዳተኞች በቂ እና ፍላጎታቸውን ያማከለ ድጋፍ አይደረግም።ሆኖም እነዚህ ተፈናቃዮች የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት በሚኖርበት ጊዜ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሲሆን በተለያዩ የተራድዖ ድርጅቶች አማካኝነት ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ድጋፍ እንዲሁም በአንዳንድ መጠለያ ጣቢያዎች ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች የሕክምና እና የሥነ-ልቦና ድጋፍ የሚደረግ መሆኑን ተፈናቃዮች ለኮሚሽኑ አስረድተዋል፡፡

35. ኮሚሽኑ ሁለተኛውን ዙር ክትትል ባከናወነበት ወቅት በአክሱም 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተጠልለው የሚገኙ ሴት ተፈናቃዮች የንጽሕና መጠበቅያ ቁሳቁስ/ሞዴስ ድጋፍ ከተደረገላቸው አንድ ዓመት ያለፈ መሆኑን ገልጸው በተለያዩ የተራድዖ ድርጅቶች አማካኝነት የወሊድ ክትትል፣ የሕፃናት ክትባት፣ የሥነ-ተዋልዶ ጤና እና ጥቃት ለደረሰባቸው የሥነ-ልቦና ድጋፍ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ ቢሆንም በክትትሉ ወቅት ትምህርት ሊጀመር ስለሆነ በሚል ምክንያት ድርጅቶቹ አገልግሎቱን የሚሰጡበትን የመማሪያ ክፍሎች እንዲለቁ የተደረገ መሆኑን፣ በዚህም ምክንያት በትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥ አገልግሎቱ የሚሰጥ ቢሆንም ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች አገልግሎቱ ተገቢውን ግላዊነት ወይም ሚስጥራዊነት (privacy and confidentiality) ሳይጠብቅ የሚሰጥ በመሆኑ ተጎጂዎች ምቹ በሆነ ሁኔታ አገልግሎት ለማግኘት መቸገራቸውን ለኮሚሽኑ አስረድተዋል፡፡

36. ሕፃናት ለልመና ወደ ወታደር ካምፕ እና ወደተለያዩ ሥፍራዎች በሚሄዱበት ጊዜ ጥቃት የሚደርስባቸው መሆኑን የሴት ተፈናቃዮች ተወካዮች ለኮሚሽኑ አስረድተዋል፡፡

ዘላቂ መፍትሔ

37. ተፈናቃዮች ላለፉት ሦስት ዓመታት በመጠለያ ጣቢያዎች ያለበቂ ድጋፍ እና ያለምንም ሥራ ወይም የገቢ ምንጭ መቆየታቸው ከፍ ያለ የሥነ ልቦና ጫና እንደፈጠረባቸው በመግለጽ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እና የፌዴራል መንግሥት ወደቀድሞ ቀያቸው እንዲመልሳቸውና እንዲያቋቁማቸውም ጠይቀዋል፡፡

38. ኮሚሽኑ ሁለተኛውን ዙር ክትትል ባከናወነበት ወቅት ያነጋገራቸው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች እንዳስረዱት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ስር በሚገኙ አካባቢዎች ተፈናቃዮችን የመመለስ ሥራ በተወሰነ ደረጃ እየተከናወነ የሚገኝ ቢሆንም የበጀት ውስንነት በመኖሩ ተፈናቃዮች በሚመለሱበት የቀድሞ መኖሪያ አካባቢዎች መደበኛ ኑሮን ለማስጀመር የሚያስችሉ በጦርነቱ የወደሙ መሠረተ-ልማቶች እና አገልግሎቶች ተመልሰው ሳይገነቡ እንዲሁም የማቋቋምያ ድጋፍ ሳይደረግላቸው እንዲመለሱ የተደረጉ መሆኑን ለኮሚሽኑ ገልጸዋል፡፡ በዚህም አስቀድሞ በክልሉ ከነበሩት ከ2 ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች ወደ 1.3 ሚሊዮን ገደማ ተፈናቃዮች በተለያዩ ጊዜያት የተመለሱ መሆኑንና በመጠለያ ጣቢያ በረሃብ ከምንሞት በሚል በራሳቸው ተነሳሽነት በእግር ጭምር እየተጓዙ በግጭት ወደወደሙ የቀድሞ መኖሪያቸው የተመለሱ መሆኑን የትግራይ ክልል አደጋና ሥጋት ሥራ አመራር ቢሮ ኃላፊዎች ለኮሚሽኑ አስረድተዋል፡፡

39. በሌላ በኩል ከቃፍታ ሑመራ፣ ወልቃይት፣ ፀገዴ እና አቅራቢያ ካሉ አካባቢዎች እንዲሁም ከራያ ኣላማጣና አካባቢው የተፈናቀሉ ሰዎች እንዳስረዱት መሬታቸው፣ ቤታቸውና ንብረታቸው ከሌሎች የአማራ ክልል አካባቢዎች መጥተው እንዲሰፍሩ በተደረጉ የአማራ ብሔር ተወላጆች ተይዘዋል በሚል እና የጸጥታ ሁኔታውም አሁን ድረስ አስተማማኝ የሚባል ባለመሆኑ ጭምር መመለስ እንዳልቻሉ ለኮሚሽኑ አስረድተዋል፡፡

40. በተመሳሳይ ሁኔታ ከሰሜን ምዕራብ ትግራይ ድንበር አካባቢዎች ከሽራሮ፣ ዛላአምበሳና አካባቢው የተፈናቀሉ ሰዎች በእነዚህ አካባቢዎች የኤርትራ መንግሥት ወታደሮች ይገኛሉ በሚል የደኅንነት ዋስትና ባለመኖሩ መመለስ እንዳልቻሉ ለኮሚሽኑ ገልጸዋል፡፡

41. ከአፋር ክልል አብዓላ፣ በረሃሌ እና ኮነባ ወረዳዎችና የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በመቀሌ ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች ለኮሚሽኑ እንዳስረዱት ከተፈናቀሉበት ቦታ የነበራቸው ቤት፣ መሬትና ንብረት በሌሎች ሰዎች አለመያዙን ሆኖም በአካባቢዎቹ ባሉ የጸጥታ አካላት እና አንዳንድ ግለሰቦች ጥቃት ሊደርስ ይችላል የሚል ስጋት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ ተፈናቃዮች አክለውም ከዚህ ቀደም አንዳንድ በራሳቸው ተነሳሽነት ተመልሰው የነበሩ ተፈናቃዮች በሕይወታቸው ላይ ጭምር አደጋ ደርሷል የሚል መረጃ ተሰምቶ የነበረ ስለሆነ፤ ተፈናቃዮች ከመመለሳቸው በፊት የአፋር ክልል እና የፌዴራሉ መንግሥት ለሁሉም ተመላሽ ተፈናቃዮች የደኅንነት ዋስትና እና ጥበቃ ቢያደርጉ ወደቀድሞ መኖሪያቸው ለመመለስ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

ምክረ ሐሳቦች 

42. ለትግራይ ክልል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ቢሮ እንዲሁም ለኢ.ፌ..ሪ. አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን

  • ለተፈናቃዮች በቂ፣ ወቅቱን የጠበቀ እና ተደራሽ የሆነ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲያቀርቡ፣
  • በተለይም ተፈናቃዮች በምግብ እጥረት እና ከፍተኛ በሆነ የመጠለያ ችግር የሚገኙ በመሆኑ የተራድዖ ድርጅቶችን ጭምር በማስተባበር አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጡ፣

43. ለማከላዊ ዞን አስተዳደር፣ ለምሥራቅ ዞን አስተዳደር እና ለመቀሌ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤቶች እንዲሁን ለማከላዊ ዞን ሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት እና ለአክሱም ከተማ ከንቲባ፣ ለምሥራቅ ዞን ሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት

  • በት/ቤቶች እና በመቀሌ ከተማ በጤና ጣቢያ ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኙ ሁኔታዎችን እንዲያመቻቹ፣ እስከዚያ ተፈናቃዮች ለጊዜው የሚቆዩበትን ጊዜያዊ መጠለያ እንዲያዘጋጁ፣
  • ተፈናቃዮች በቂ፣ ወቅቱን የጠበቀ እና ተደራሽ የሆነ የምግብ ድጋፍ እንዲሁም ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን እንዲያገኙ እንዲያደርጉ፣
  • ልዩ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ተፈናቃዮች ትኩረት በመስጠት ሁኔታቸውን ያገናዘበ ልዩ ድጋፍ እና አገልግሎት እንዲያገኙ እንዲያደርጉ፣

44. ለትግራይ ክልል ጤና ቢሮ እና ለኢ.ፌ..ሪ. ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር

  • በትግራይ ክልል በሚገኙ የጤና ተቋማት አስፈላጊውን የሕክምና ግብዓቶችና መድኃኒት በማሟላት ተፈናቃዮች የሕክምና አገልግሎቶቹን እንዲያገኙ እንዲያደርጉ፣

45. ለትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ እና ለኢ.ፌ..ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ለማከላዊ ዞን፣ ለምሥራቅ ዞን እና ለመቀሌ ዞን ትምህርት ጽ/ቤቶች

  • ለተፈናቃይ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሁም ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ የትምህርት ቤት ምገባን ጨምሮ ልዩ ድጋፍ እንዲያደርጉ፣

46. ለትግራይ ክልል ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ እና ለኢ.ፌ..ሪ. ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም ለማከላዊ ዞን፣ ለምሥራቅ ዞን እና ለመቀሌ ዞን ሴቶችና ሕፃናት ጽ/ቤቶች

  • ጾታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴት ተፈናቃዮች የሕክምና እና የሥነ-ልቦና ድጋፍ ለተጎጂዎች ምቹ በሆነ ሁኔታ እንዲያመቻቹ፣ የሚያጠቡ እናቶችን እና ነፍሰጡሮችን ልዩ ፍላጎት ያማከለ ድጋፍ እና የንጽሕና መጠበቂያ በቋሚነት እንዲቀርብ፣
  • ለሕፃናት ዕድሜያቸውን እና ልዩ ፍላጎታቸውን መሠረት ያደረገ የምግብ ድጋፍ እንዲቀርብ፣ እንዲሁም ሕፃናት ለልመናና ሌሎች ጎጂ ተግባራት እንዳይሰማሩ በቂ ድጋፍ እና ጥበቃ እንዲደረግ፣
  • ለአካል ጉዳተኛ ተፈናቃዮች እና አረጋውያን ተፈናቃዮች ልዩ ፍላጎቶቻቸውን ከግምት ውስጥ ያስገባ ድጋፍ እንዲደረግ፣

47. ለትግራይ ክልል ፍት ቢሮ እና ለኢ.ፌ..ሪ. ፍት ሚኒስቴር

  • ጥቃት የደረሰባቸው ተፈናቃዮች ፍትሕ እንዲያገኙ እና የሥነ ልቦና ድጋፍ እንዲደረግላቸው፣

48. ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ለትግራይ ክልል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ቢሮ፣ ለኢ.ፌ..ሪ. አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እንዲሁም ለሚመለከታቸው የፌዴራል መንግሥት አካላት በሙሉ

  • ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞ ቀያቸው እንዲመለሱና በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ሁሉም መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት በትብብር እንዲሠሩና አስቻይ ሁኔታዎች እንዲመቻች፣

49. ፌዴራሉ መንግሥት፣ አፋር እና ለአማራ ብራዊ ክልላዊ መንግሥት የጸጥታ አካላት

  • ተፈናቃዮች ወደቀድሞ መኖሪያቸው ለመመለስ እና ለማቋቋም እንዲቻል የጸጥታ ስጋት ያለባቸውን አካባቢዎች ጥቃት ማድረስ ከሚችሉ አካላት ነጻ የማድረግ እና የተመላሾችን በደኅንነት የመኖር መብት የማረጋገጥ ኃላፊነታቸውን በጋራ እንዲወጡ፣

50. ለተራድዖ ድርጅቶች

  • የተለየ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ተፈናቃዮች ልዩ እና ተደራሽ ድጋፍ እንዲያቀርቡ፣ ለተፈናቃዮቸ ዘላቂ መፍትሔን በማፈለለግ ሂደት ውስጥ መንግሥትን እንዲያግዙ ይገባል፡፡