የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአዲስ አበባ በሚገኙ የሕፃናት መንከባከቢያና ማሳደጊያ ማእከላት ላይ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታና አያያዝ ከሕፃናት መብቶች፣ መርሖች እና መስፈርቶች አንጻር ለመገምገም ባከናወነው ክትትል የተለዩ ግኝቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ግንቦት 29 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ውይይት አካሂዷል።

ኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች ክትትሉን በኮልፌ ወንድ ሕፃናት ማቆያና ማቋቋሚያ ተቋም፣ በክበበ ፀሐይ የሕፃናት ማቆያና እንክብካቤ ማዕከል፣ በቀጨኔ ሴት ሕፃናት ማቆያና ማቋቋሚያ፣ በኪዳነ ምሕረት የሕፃናት ማሳደጊያ፣ በሰላምታ ፋሚሊ የሕፃናት ማሳደጊያ፣ በአበበች ጎበና የሕፃናት ማሳደጊያ እና በሚሽነሪ ኦፍ ቻሪቲ የሕፃናት ማሳደጊያ ማእከላት ያካሄደ ሲሆን በውይይቱ ከእነዚሁ ማእከላት የተውጣጡ ተወካዮች እና ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር እና ከአዲስ አበባ ሴቶችና ማኅበራዊ ቢሮ የተወከሉ  የሥራ  ኅላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

Meeting participants

ክትትሉ በሕፃናት መንከባከቢያና ማሳደጊያ ማእከላት ውስጥ ያሉ ሕፃናት ሁኔታ ከአስፈላጊነት፣ ከተስማሚነት እና ከሕፃናት መብቶች መሠረታዊ መርሖች አንፃር የተቃኘ ሲሆን የሕፃናቱ በቂ የኑሮ ደረጃ ማግኘት፣ የጥበቃ፣ የተሳትፎና የግላዊ ሕይወት ሁኔታ እንዲሁም መረጃና ማኅበራዊ መብቶች የክትትሉ መስፈርቶች ተደርገዋል፡፡ በክትትሉ የተለዩ ተግዳሮቶች፣ መወሰድ ያለባቸው የማሻሻያ እርምጃዎችና ምክረ ሐሳቦች ለተሳታፊዎች በዝርዝር ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

Meeting participants

የውይይቱ ተሳታፊዎች የክትትሉ ግኝቶች ነባራዊ ሁኔታን የሚያሳዩ መሆናቸውን ገልጸው የሕፃናት መብቶችንና መርሖችን ለመተግበር የዐቅም ውስንነት እንዳሉባቸው እና እነዚህንም ለማሟላት የመንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ርብርብ እንደሚያስፈልግ በአጽንዖት ገልጸዋል። በመጨረሻም የሕፃናት መንከባከቢያ እና ማሳደጊያ ማእከላት የሕፃናት መብቶች ሁኔታዎችን ለማሻሻል የቀረቡትን ምክረ ሐሳቦች በማስተባበርና በመተግበር ረገድ ኃላፊነት ያለባቸው ተቋማትን በዝርዝር ተለይተዋል።

የኢሰመኮ የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር መብራቱ ገበየሁ በሕፃናት ማሳደጊያ ተቋማት የሚገኙ ሕፃናትን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ መፈተሽና መከታተል መንግሥት ችላ ሊለው የማይገባ ተግባር እንደሆነ ጠቁመው፤ “የሕፃናት መንከባከቢያና ማሳደጊያ ማእከላት በሕፃናት መብቶች የተቃኘ የእንክብካቤ፣ የአገልግሎትና የጥበቃ ሥርዓት ሊኖራቸው ይገባል” ብለዋል፡፡ አክለውም ኮሚሽኑ ይህን መሰል ክትትል በስምንት የክልል ከተሞች ጭምር ያካሄደ መሆኑንና ሀገራዊ ሁኔታውን የሚያሳይ የተጠቃለለ ሪፖርት አጠናቅሮ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ተደራሽ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።