የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባሕር ዳር ጽሕፈት ቤት በአማራ ክልል በተመረጡ 24 ማረሚያ ቤቶች የታራሚዎችን አያያዝ እና ሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ በሚመለከት በተደረገ ክትትል የተለዩ ግኝቶች እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ላይ በባሕር ዳር ከተማ ግንቦት 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ከሚመለከታቸው የፍትሕ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።

በውይይት መድረኩ አዲስ የተከፈተውን የገንዳ ውሃ ማረሚያ ቤት ኀላፊን ጨምሮ በአማራ ክልል የሚገኙ የ31 ማረሚያ ቤት ኀላፊዎች፤ የክልሉ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ከፍተኛ አመራሮች፤ የክልሉ ፍትሕ ቢሮ እና የጠቅላይ ፍ/ቤት የበላይ ኀላፊዎች፤ የአማራ ክልል ም/ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከፍተኛ ኀላፊዎች እና በኢሰመኮ የባሕር ዳር ጽ/ቤት ኀላፊና ባለሙያዎች እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፍትሕ አካላት ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

በውይይት መድረኩ በክትትሉ የተለዩ የታራሚዎችን አያያዝ አስመልክቶ የታዩ መሻሻሎች፣ አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች እና ምክረ ሐሳቦች ለተሳታፊዎች ቀርበዋል። የታራሚዎች ምዝገባና አቀባበል፣ የምክር አገልግሎት የማግኘት፣ ከኢሰብአዊ አያያዝ የመጠበቅ፣ በቤተሰብ የመጠየቅ መብቶች፣ የሙያ ስልጠና እና የቀለም ትምህርት፣ በገቢ ማስገኛ ሥራዎች የመሰማራት፣ የእምነት ነጻነት፣ አመክሮ እና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በሚፈጽሙ የፖሊስ አባላት ተጠያቂነት ጋር በተያያዘ የተስተዋሉ መሻሻሎች በጥንካሬ ተጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል በክትትሉ ከተለዩ አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል ክትትል ከተደረገባቸው ማረሚያ ቤቶች መካከል በአንዳንድ ማረሚያ ቤቶች ታራሚዎች መደብደባቸው፤ በጎንደር ማረሚያ ቤት የተከለከሉ ነግሮችን ወደ ማረሚያ ቤት አስገብተዋል የተባሉ ታራሚዎች በካቴና መታሰራቸው፤ ከሕግ ውጭ ያለፍላጎት የሚደረግ የታራሚዎች ዝውውር፤ በማረሚያ ቤቶች በሚሰጡ የሙያ ስልጠና እና የቀለም ትምህርት የሴቶች ተሳትፎ አነስተኛ መሆን፤ የሚመደብ የምግብ በጀት አነስተኛ መሆን፤ እና በአንዳንድ ማረሚያ ቤቶች የሚስተዋል የውሃ አቅርቦት ችግር መኖር ይጠቀሳሉ።  እንዲሁም አብዛኞቹ ማረሚያ ቤቶች የተጣበቡ እና የተጨናነቁ መሆናቸው፤ በቂ የጤና አገልግሎት አለመኖር፤ በጊዜ ቀጠሮ ታስረው የጊዜ ቀጠሯቸው ተዘግቶ በእስር ላይ የሚገኙ 303 ታራሚዎች መኖራቸው፤ የፌደራል ፍ/ቤቶች ውሳኔ ያሳለፉባቸው ታራሚዎች በወቅቱ የይቅርታ ተጠቃሚ አለመሆናቸው፤ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ታራሚዎች ፍርዳቸው ሳይፈጸም ወይም ሳይሻሻል ለረጅም ጊዜ በእስር ላይ መሆናቸው፤ በአብዛኞቹ ማረሚያ ቤቶች ወጣት ጥፋተኞችን ከአዋቂዎች ጋር ቀላቅሎ ማሰር እና ልዩ ትኩረት ለሚሹ ታራሚዎች የተለየ ድጋፍ አለማድረግ አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች መሆናቸው በውይይት መነሻ ገለጻ ላይ ተብራርቷል፡፡

ተሳታፊዎችም በክትትል የተለዩት ችግሮች የታወቁ መሆናቸውንና የቀረቡትን ምክረ ሐሳቦች እንደግብዓት እንደሚጠቀሙባቸው ገልጸው፤ የታራሚዎችን ሰብአዊ መብቶች ለማስከበር የበጀት፣ የቁሳቁስ እና የአሠራር ችግሮች ማነቆ ስለሆነባቸው የክልሉ መንግሥት ለማረሚያ ቤቶች ልዩ ትኩረትና ድጋፍ ሊያደርግላቸው እንደሚገባ አሳስበዋል። የኢሰመኮ የክትትል እና ምርመራ የሥራ ክፍል ከፍተኛ ዳይሬክተር ዶ/ር ሚዛኔ አባተ በመክፈቻ ንግግራቸው፤ በክልሉ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች በመታረም ላይ የሚገኙ ታራሚዎች ሰብአዊ መብቶቻቸውን ጠብቆ በማረም እና በማነጽ ወደኅብረተሰቡ ለመቀላቀል የሚደረገው ጥረት እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር አካላት መሻሻሎችን አጠናክረው መቀጠልና የሚታዩ የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ጉድለቶችን ለማረም ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡