የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የጥቃት ተጎጂ የሆኑ ሴቶች እና ሕፃናት በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሂደት ውስጥ ያሏቸውን መብቶች አተገባበር አስመልክቶ ባከናወነው ክትትል የተለዩ ግኝቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ጥቅምት 14 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ተወያይቷል።

ውይይቱ በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ የጥቃት ተጎጂ የሆኑ ሴቶች እና ሕፃናት መብቶች አያያዝን በተመለከተ የተለዩ የሕግ፣ የፖሊሲ፣ የተቋም እና የአፈጻጸም ክፍተቶችን ለባለድርሻ አካላት ለማጋራት እንዲሁም ኮሚሽኑ በቀጣይ ሊሠራቸው በሚገቡ ጉዳዩች ላይ ግብአት ለመሰብሰብ ያለመ ነው። በውይይቱ ክትትል የተደረገባቸው አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ሐረሪ እና ኦሮሚያን ጨምሮ ከሌሎች ክልሎች የተውጣጡ ዳኞች፣ ዐቃቢያነ ሕግ፣ ፖሊሶች እና የተቀናጀ የአንድ ማእከል አገልግሎት ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

በውይይቱ የመብት ባለግዴታዎች ያላቸው ምላሽ አሰጣጥ ከተጣለባቸው የሕግ ግዴታ እና ከሰብአዊ መብቶች መለኪያዎች አኳያ በኮሚሽኑ የተለዩ የክትትል ግኝቶች በዝርዝር ቀርበዋል። ይህም የጥቃት ተጎጂ የሆኑ ሴቶች እና ሕፃናት በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ከአቤቱታ አቀራረብ ጀምሮ በምርመራ ሂደት፣ በክስ አቀራረብ እንዲሁም በፍርድ ወቅት ያሉ የመብት አያያዞችን ከዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ ሰብአዊ መብቶች ሕጎች መመዘኛዎች ጋር በማነጻጸር ተብራርተዋል። በተጨማሪም የጥቃት ተጎጂ የሆኑ ሴቶችና ሕፃናትን በፖሊስ፣ በዐቃቢ ሕግ፣ በፍ/ቤቶች እና በድጋፍ ሰጪ ተቋማት በሚቀርቡበት ጊዜ የሚደርስባቸው የመብት ጥሰቶች በዝርዝር ተዳስሰዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች

የውይይቱ ተሳታፊዎች በወንጀል የፍትሕ ሥርዓቱ የጥቃት ተጎጂ በሆኑ ሴቶችና ሕፃናት መብቶች አጠባበቅ ሂደት ውስጥ ያሉ የሕግና ፖሊሲ አተገባበር ተግዳሮቶች፣ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ የጥቃት ተጎጂ ለሆኑ ሴቶችና ሕፃናት ያለውን ውስን ተደራሽነት፣ የጥቃት ተጎጂዎች የደኅንነት ጥበቃ አለማግኘትና ለዳግም ጥቃት የተጋለጡ መሆናቸውን አንስተዋል። በተመሳሳይ ክብርንና ሚስጥራዊነትን በጠበቀ የፍትሕ ሥርዓት በመስተናገድ ውጤታማ መፍትሔ በማግኘት ረገድ እንዲሁም የመደመጥና የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብቶች ላይ ያሉ ክፍተቶችን አስመልክቶ አስተያየታቸውን ገልጸዋል። በተጨማሪም ለወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ አጋዥ ሆነው በተቋቋሙት የአንድ ማእከል አገልግሎት መስጫ አደረጃጀቶች እና በተጎጂዎች መጠለያ ተቋማት የሚስተዋሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን አስመልከቶ ተሳታፊዎቹ ከመጡባቸው ተቋማት ተግባርና ኃላፊነት እንዲሁም ግዴታ አንጻር አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በክትትሉ ባልተካተቱ ክልሎች ያሉ ተሞክሮዎችንም አጋርተዋል። የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ የጥቃት ተጎጂ የሆኑ ሴቶች እና ሕፃናት ጉዳይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ እንደሆነ በመግለጽ የሚመለከታቸው አካላት በሕግ ከተጣለባቸው ግዴታዎች አንጻር በግኝቶቹ እና በተለዩ ክፍተቶች ላይ በትብብር ሊሠሩ እንደሚገባ ተናግረዋል። ኮሚሽነሯ አክለውም የጥቃት ተጎጂ የሆኑ ሴቶችና ሕፃናት መብቶች እንዲከበሩ ባለድርሻ አካላት ከመቼውም ጊዜ በላይ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡