የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በትግራይ ክልል በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች፣ ፖሊስ ጣቢያዎች እና ጤና ተቋማት ከሐምሌ 1 እስከ 23 ቀን 2015 ዓ.ም. አከናውኖት በነበረው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ሥራ የተለዩ ግኝቶችን ለማሳወቅና የመፍትሔ ሐሳቦች ላይ ለመወያየት ከኅዳር 8 እስከ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. በውቕሮ ከተማ ሦስት ዙር የውይይት መድረኮችን አካሂዷል። በውይይቶቹ የክልሉ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽንና የማረሚያ ቤቶች ኃላፊዎች፣ የፖሊስ ኮሚሽን፣ የከተማ እና የዞን ኃላፊዎች፣ የጤና ቢሮ ኃላፊዎች፣ የትግራይ ሴቶችና ሕፃናት ቢሮና የሴቶች ማኅበር ኃላፊዎች፣ የአንድ መስኮት አገልግሎት ማእከል እና የተሐድሶ ማእከላት (One-Stop Center and Safe House) አስተባባሪዎች እንዲሁም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ተወካዮች ተገኝተዋል።

ስምንት ማረሚያ ቤቶች ወደ ሥራ መመለሳቸው፣ መሠረታዊ የሕክምና አገልግሎት መጀመሩ፣ የክልሉ መንግሥት ለአንድ ታራሚ የቀን የምግብ ወጪ 53.45 ብር መመደቡ፣ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ያለምንም ገደብ በማረሚያ ቤቶቹ ተገኝተው መጎብኘት መቻላቸው እንደ መልካም ተሞክሮ በክትትሉ የተለዩ መሆናቸው ተገልጿል። በተመሳሳይ በፖሊስ ጣቢያዎች በተደረገ ክትትል የፖሊስ መዋቅሩ ሥራ መጀመሩ፣ በተወሰኑ ፖሊስ ጣቢያዎች የምግብ አቅርቦት መጀመሩ፣ የተጠርጣዎች ምዝገባ መኖሩ፣ የቤተሰብ ጉብኝት ያለገደብ መፈቀዱ፣ በጤና ተቋማት የሕክምና አገልግሎት መሻሻሉ፣ የጾታዊ ጥቃት ተጎጂዎች የሕክምና አገልግሎት በሰባት የአንድ መስኮት ማእከላት እና በሁለት የተሐድሶ ማእከላት መሰጠቱ እንደ መልካም ጅማሮ የተጠቀሱ ናቸው፡፡

የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ሰላማዊት ግርማይ (በግራ በኩል)

በሌላ በኩል በጦርነቱ ምክንያት የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ በደረሰው ጉዳት የተሟላ የፍትሕና ሕክምና አገልግሎት መሰጠት አለመቻሉ እና በጦርነቱ ወቅት የ18 ወር ደመወዝ አለመከፈሉ በሠራተኞች አጠቃላይ የሥራ ተነሳሽነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ መፍጠሩ ተገልጿል። ባለሙያዎች የመልሶ መቋቋሚያ መንገዶች ላይ ስልጠናዎች አለመሰጠታቸው የፍትሕ አገልግሎትን ወደነበረበት ደረጃ የመመለስ ሂደቱ ላይ ተጸዕኖ ማሳደሩ ተብራርቷል፡፡ በማረሚያ ቤቶች በተደረገ ክትትል የውሃ አቅርቦት፣ የቢሮ እና ፍራሽን ጨምሮ የታራሚዎች መገልገያ ቁሳቁሶች እጥረት መኖሩ እንዲሁም የማደሪያ ክፍሎች ጠባብና ንጽሕና የሌላቸው መሆናቸው ተጠቅሷል። በተጨማሪም በማረሚያ ቤቶቹ የነበሩ የስልጠና እና የገቢ ማስገኛ ማእከላት በጦርነቱ በመጎዳታቸው የማረምና የማነጽ ተግባራትን መሥራት አለመቻሉ በክትትሉ የተለዩ ተግዳሮቶች ናቸው። 

ከፖሊስ ጣቢያዎች ጋር በተያያዘ ከጦርነቱ በኋላ በቂ ክህሎት ባይኖራቸውም በአጭር ግዜ የሙያ ስልጠና የወሰዱ ባለሙያዎች መመደባቸው በመልካም እመርታነት የተለየ ነው። በአንጻሩ በጦርነቱ የተጎዱ የተጠርጣሪ መኝታ ክፍሎች ጥገና አለመደረጉ፣ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ማደሪያ ክፍሎችም ከተጠርጣሪዎች ቁጥር ጋር የተጣጣሙ አለመሆናቸው፣ ከፍተኛ የውሃ አቅርቦት እጥረት መኖር፣ ንጽሕናቸውን ያልጠበቁ የመጸዳጃ ቤቶችና የአጠቃቀም ችግር መኖር እንዲሁም በትራንስፖርት ችግር ምክንያት ተጠርጣሪዎችን በ48 ሰዓት ፍርድ ቤት ማቅረብ አለመቻሉ እንደተግዳሮት ተለይተዋል፡፡

የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ

ከጤና መብት አንጻር የመድኃኒት አቅርቦት የተሻሻለ ቢሆንም በክልሉ ጤና ተቋማት ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ጥቂት መሆናቸው፣ የአምቡላንስ እና የሕክምና መሣሪያዎች እጥረት፣ የሠራተኞች ከሥራ መልቀቅ እና የበጀት እጥረት ፈታኝ ሁኔታዎች መሆናቸው ተገልጿል። ከጾታዊ እና ወሲባዊ ጥቃት ጋር በተያያዘ እየተሰጠ ያለው አገልግሎት ከተፈጸመው ጥቃት አኳያ የማይመጣጠን ከመሆኑ በላይ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች የሚሰጥ ማኅበራዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና ኢኮኖሚያዊ እገዛ ዝቅተኛ መሆኑ እና የለጋሽ ድርጅቶች ያልተቀናጀ ድጋፍ መስጠት በግኝቱ በአሳሳቢነት ተለይተዋል።

ተሳታፊዎች በበኩላቸው አብዛኛዎቹን ግኝቶች እንደሚቀበሏቸው እና ከክትትሉ በኋላ የተሻሻሉ አሠራሮች መኖራቸውን ገልጸዋል። ከነዚህም መካከል የክልሉ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽነር ተወልደብሃን ተስፋዓለም ማረሚያ ቤት ከጤና ቢሮ ጋር በመቀናጀት በስምንቱም ማረሚያ ቤቶች ነጻ የሕክምና አገልግሎት መጀመሩን የገለጹ ሲሆን በጦርነቱ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መጠገን ከክልሉ ዐቅም በላይ መሆኑን ጠቁመዋል። አያይዘውም ለሚስተዋሉት ችግሮች ተገቢ መፍትሔ በመስጠት የሰብአዊ መብቶች አያያዝን ለማሻሻል የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ የክልሉ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ መሰረት በፖሊስ ኮሚሽን ሥር በ7 ዞኖችና እና በ93 ወረዳዎች አዛዥ አመራሮች እና ባለሙያዎች በመመደባቸው የተጠርጣሪዎች ከሕግ ውጭ እሥራት፣ በ48 ሰዓት ፍርድ ቤት ያለመቅረብ እና ከፖሊስ መዋቅር መዘርጋት በኋላ በተጠርጣሪዎች ላይ ሲፈጸም የነበረ ያልተገባ ኃይል አጠቃቀም ችግሮች በሂደት መሻሻሉን ጠቅሰዋል። የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ፀጋይ ብርሀነ (ዶ/ር) በበኩላቸው ለተነሱት ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት የፍትሕ ተቋማት ተቀናጅተው የሚሠሩበት መድረክ እንደሚቀጥል ገልጸው ኮሚሽኑ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡

የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ

የጾታዊ ጥቃት ተጎጂዎች አገልግሎትን አስመልክቶ በጤና ቢሮ አስተባባሪነት የባለድረሻ አካላት ሚና እና ኃላፊነት የሚያሳይ ዝርዝር መመሪያ (Standard Operational Guideline) መዘጋጀቱን፣ ከለጋሽ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለሰባት የአንድ መስኮት አገልግሎት መስጫ ማእከላት እና ለሁለት የተሐድሶ ማእከላት አልትራሳውንድ መሰጠቱ እና የምርመራ አገልግሎት መጀመር መቻሉን ተገልጿል። የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ አመራር የሆኑት ዶ/ር ስምዖን ገ/ጻድቕ ጾታዊ እና ወሲባዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች የሚሰጠው አገልግሎት በጤና ተቋማት ላይ በደረሰ ጉዳት የተነሳ ውስን መሆኑን አስረድተዋል።

በውይይቱ የተገኙት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሓዱሽ ተስፋ የፍትሕ አካላት የመንግሥትን ከባዱን ኃላፊነት የተሸከሙ ተቋማት እንደመሆናቸው ተገቢውን ድጋፍ ያላገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል። ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የፍትሕ ሥርዓቱ ከተቋማዊ ዐቅም፣ ከሰው ኃይል ዐቅም እና ከቁሳዊ አቅርቦት ጋር በተያያዘ መሠረታዊ ተግዳሮቶች እንዳሉበት አብራርተዋል። ችግሮቹን ለመፍታትም የሚመለከታቸው አካላት ባለው ዐቅም በጋራ በመተባበር አገልግሎቶቹን ለማሻሻል ኃላፊነታቸው መወጣት አለባቸው ብለዋል፡፡

የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ሰላማዊት ግርማይ ውይይቱ ከክልሉ ተቋማት በተለይም ከማረሚያ ቤት እና ፖሊስ ጋር በቅርበት ለመሥራት እንዲሁም በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ ዕቅድ ሊፈጸሙ የሚገባቸው ተግባራትን በመለየት ኮሚሽኑ ድጋፍ የሚያደርገበትን መንገድ ለማጠናከር ያለመ እንደሆን ገልጸዋል። አክለውም የታራሚዎችን፣ የተጠርጣሪዎችን እና የጾታዊ ጥቃት ተጎጂዎችን መብት ለመጠበቅ የባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስታዋጽዖ ማበርከትና በትብብር መሥራት አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል።