የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአፋር ክልል በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎችና ማረሚያ ቤቶች የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅን በተመለከተ ባካሄደው ክትትል በለያቸው ግኝቶች ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ሰኔ 7 እና 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰመራ ከተማ ሁለት የውይይት መድረኮችን አካሄደ፡፡

በውይይት መድረኮቹ ኮሚሽኑ በ17 ፖሊስ ጣቢያዎች እና በሃሪ ረሱ ማረሚያ ቤት ከታኅሣሥ 27 እስከ ጥር 11 ቀን 2015 ዓ.ም. የመጀመሪያ ዙር እንዲሁም በ2014 ዓ.ም. መደበኛ ክትትል ከተደረገባቸውና የምክረ ሐሳብ ማስፈጸሚያ የድርጊት መርኃ ግብር ከተቀረጸላቸው መካከል በሦስት ፖሊስ ጣቢያዎች እና በሁለት ማረሚያ ቤቶች ላይ ያካሄደውን ሁለተኛ ዙር ክትትል ሪፖርት አቅርቧል፡፡

በእነዚህ የውይይት መድረኮች ላይ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት፣ የክልሉ ርእሰ መሰተዳደር ጽ/ቤት ተወካይ፣ የምክር ቤት የሕግ እና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የፖሊስ እና የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽነሮችና ኃላፊዎች፣ የ17ቱም ፖሊስ ጣቢዎች የወንጀል ምርመራ ክፍል ኅላፊዎች፣ የፍትሕና ጤና ቢሮ ኅላፊዎች ተሳትፈዋል።

በፖሊስ ጣቢያዎች በተደረገው ክትትል ከተለዩ ግኝቶች መካከል ተጠርጣሪዎች ሲያዙ መረጃቸው በተገቢው መንገድ መሰነዱ፣ በሕግ ከተደነገገው ቅጣት ውጪ ተጠርጣሪዎችን በካቴና የማሰር ተግባር አለመኖሩ፣ የአካል ፍተሻ በተመሳሳይ ጾታ መፈጸሙ፣ ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ የሚደረግ የቤትና የንብረት ብርበራ አለመኖሩ፣ ተጠርጣሪዎች በቤተሰቦቻቸው፣ በሃይማኖት አባቶች፣ በሐኪሞቻቸውና በሕግ አማካሪዎቸው በፈለጉት ቀናት ጉብኝት መፈቀዱ በአወንታዊነት ተለይተዋል፡፡ በተጨማሪም በከባድ ወንጀል የተጠረጠሩ ካልሆነ በስተቀር ነፍሰጡር እና የሚያጠቡ እናቶች በታዋቂ የሀገር ሽማግሌዎች ዋስትና ምሽት ወደ ቤታቸው ሄደው እንዲያድሩ መደረጉ በጠንካራ ጎን የታየ ጉዳይ ነው።

በተመሳሳይ በማረሚያ ቤቶች በተካሄደ ክትትል የጨለማ ቅጣት ቤቶች አለመኖራቸው፣ ታራሚዎች ወደ ማረሚያ ቤቶች ሲገቡ መብትና ግዴታቸው የሚነገራቸው መሆኑ፣ ለማረሚያ ቤት ፖሊሶች በታራሚዎች አያያዝ ዙሪያ ስልጠና መሰጠቱ እንዲሁም የመድኃኒት ግዥ መፈጸሙ በአዎንታዊ ጎኑ ቀርቧል።

በሌላ በኩል በፖሊስ ጣቢያዎች ከፍተኛ የሆነ የቢሮ ጥበት፣ የሴት ተጠርጣሪዎች ማረፊያ አለመኖር፣ እንደ መፀዳጃ እና መታጠቢያ ያሉ መሠረታዊ አገልግሎቶች አለመሟላት፣ ተጠርጣሪዎች በተያዙ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት አለማቅረብ፣ ተጠርጣሪዎች ለፖሊስ የሚሰጡት ቃል በሚገባቸው ቋንቋ ተነቦላቸው እንዲፈርሙ መደረግ ላይ ክፍተት መኖሩ በቀረበው ሪፖርት ላይ ተገልጿል። በተጨማሪም ማደሪያ ክፍሎች ጠባብና ደረጃቸውን የጠበቁ አለመሆናቸው እንዲሁም የንጽህና ጉድለት ያለባቸው መሆኑ፣ በአካባቢው ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል እና ሞቃታማ የአየር ሁኔታን ያላገናዘቡ መሆናቸው በክትትሉ የተለዩ ጉድለቶች ናቸው። በተለይም በአይሳይታ እና አብዓላ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጣቢያዎች ለሴቶች የተለየ መኖሪያ ክፍል አለመኖር እና የመጸዳጃና የመታጠቢያ ክፍሎች አለመሟላታቸው፣ በመንግሥት አማካኝነት የሚቀርብ ምግብ አለመኖር፣ በፖሊስ ጣቢያዎች ለተጠርጣሪዎች የሚቀርብ ምግብ፣ ውሃ፣ አልጋ፣ ፍራሽና አልባሳት እንዲሁም የጤና አገልግሎት አለመኖር በክትትል ግኝቱ ተመላክተዋል፡፡

በማረሚያ ቤቶች በተካሄደ ክትትል በግኝቱ ከተመላከቱ ክፍተቶች መካከል ለአንድ ታራሚ የሚያዘው የምግብ በጀት በወቅቱ ባለው የገበያ ሁኔታ ጥራቱን የጠበቀ ምግብ ለማቅረብ አለማስቻሉ፤ የመዝናኛ አቅርቦት አለመኖር፤ ታራሚዎችን ከማረምና ማነፅ አንጻር በማረሚያ ቤቶቹ ስልጠናና እና ገቢ ማስገኛ ሥራዎች አለመኖር፣ ልዩ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ታራሚዎች በቂ ድጋፍ አለመኖሩ እና የመፀዳጃ እና መታጠቢያ ቤቶች እጥረት መኖር ይገኙበታል፡፡

ተሳታፊዎቹ ኮሚሽኑ ክትትል ሥራውን ማካሄዱን በበጎ ጎን እንደሚቀበሉት ገልጸው አብዛኛውዎቹን ግኝቶች እንደሚቀበሏቸው፤ የተወሰኑት ደግሞ ከክትትሉ በኋላ ማስተካከያ እንደተደረገባቸው እንዲሁም ችግሩን በጋራ ለመፍታት እንዲቻል ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት በውይይቱ እንዲሳተፉ መደረጉ ሊበረታታ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ የክልሉ ፍትሕ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት በኮሚሽኑ የቀረቡ ምክረ ሐሳቦችን ለመተግበር የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡ ከበጀት ጋር የተያያዙ ችግሮችን በተመለከተ ኮሚሽኑ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት በመወትወት እገዛ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ
የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በበኩላቸው የውይይት መድረኩ ኮሚሽኑ ባካሄደው ክትትል በለያቸው የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ጉድለቶች ላይ ተቀራርቦ ለመሥራት እና ለቀጣይ ሥራዎች አጋዥ እንዲሆን የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸው በማረሚያ ቤት የሚገኙ ታራሚዎችም ሆኑ በፖሊስ ጣቢያዎች ያሉ ተጠርጣሪዎች ኢሰብአዊ ከሆነ አያያዝ ሊጠበቁ ይገባል፤ መንግሥትም የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶችን እና ሕገመንግስታዊ ድንጋጌዎችን ማክበር ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ሰላማዊት ግርማይ
የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ሰላማዊት ግርማይ

በመጨረሻም የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ሰላማዊት ግርማይ ማረሚያ ቤቶች እና ፖሊስ ጣቢያዎች በሕግ ጥላ ሥር ያሉ ሰዎችን መብቶች ለማክበር ኮሚሽኑ በሰጠው ምክረ ሐሳብ መነሻነት የፖሊስና ማረሚያ ቤቶች ኀላፊዎችና አባላት የወሰዷቸው ማሻሻያ እርምጃዎች በተለይም ለታራሚዎች ፍራሽና አንሶላ መሟላቱ፣ መጸዳጃ ክፍሎች መሠራታቸው እንዲሁም የታራሚዎች የእርሻ ልማት ሥራ መጀመሩ አበረታች ናቸው ብለዋል፡፡ አክለውም ኮሚሽኑ በቀጣይ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ስልጠናዎችን መስጠትን ጨምሮ የምክረ ሐሳቦች ተፈጻሚ እንዲሆኑ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን በመወትወት ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡