የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በ2014 ዓ.ም. በ3ኛ እና 4ኛ ሩብ ዓመት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች የታራሚዎች አያያዝና ሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ላይ ባደረጋቸው የክትትል ሥራዎች በተለዩ ግኝቶች እና በተሰጡ ምክረ ሃሳቦች ላይ ከማረሚያ ቤቶች ከተዉጣጡ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ላይ ከሚገኙ አመራሮች ጋር በባምባሲ ከተማ ነሐሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ውይይት አድርጓል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ በክልሉ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ላሉ ታራሚዎች በተለያዩ ሙያ ዘርፍ እንዲሰማሩ መደረጉ፣ በሴቶች መኝታ ክፍሎች ምቹ አልጋና ፍራሽ መሟላቱ፣ ጭካኔ የተሞላበት፣ ኢ-ሰብአዊ የሆነና አዋራጅ አያያዝ መቀነሱ እንዲሁም የትምህርት ቤቶች ግንባታዎች መኖራቸው በማረሚያ ቤቶች ውስጥ የታዩ መሻሻሎች መሆናቸው ተገልጿል። 

በሌላ በኩል በሪፖርቱ ከተካተቱ ትኩረት ከሚሹ ክፍተቶች መካከል አልፎ አልፎ የተወሰኑ የፖሊስ አባላት በታራሚዎች ላይ የሚፈጽሙት የስድብ፣ ማስፈራራት፣ ዛቻ እና የድብደባ ድርጊቶች መኖራቸው፣ ከመብራት መጥፋትና ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች አለመኖር ጋር ተያይዞ  የውሃ አገልግሎት መስተጓጎል፣ የሚቀርበው ምግብ በዓይነት፣ በጥራትና መጠን አነስተኛ መሆን፣ የመኖሪያ ክፍሎቹ የተጨናነቁና ምቹ አለመሆን፣ ለታራሚዎች አልጋና ፍራሽ አለመኖር ተጠቅሰዋል፡፡

እንዲሁም ወጣት አጥፊዎች፣ ታራሚዎች እና ተጠርጣሪዎች በየፈርጅ ተለይተው አለመያዛቸው፣ መድኃኒትና የላብራቶሪ አገልግሎት በበቂ ሁኔታ አለመቅረብ፣ የባለሙያዎች አቅም ማነስ እና አልፎ አልፎ የሥነ ምግባር ችግር መስተዋሉ፣ ማረምና ማነፅ ተግባራትን በሚመለከት በቂ መጽሐፎችና ባለሙያዎች አለመኖር፣  እስረኞች ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚገናኙበት ቦታ ወንበሮቹ ተራርቀው የተሰሩ በመሆኑ አመቺ አለመሆናቸውና በስልክ ለመገናኘት ሁኔታዎችን አለማመቻቸት በሪፖርቱ ተለይተው በውይይቱ ተዳሰዋል። 

በተጨማሪም ለአካል ጉዳተኛ ታራሚዎች፣ ሕፃናት እና ታማሚዎች በልዩ ሁኔታ የሚደረግላቸው ድጋፍም ሆነ እንክብካቤ አነስተኛ መሆን፣ ወጥነትና ግልጽነትን የተከተለ የአመክሮና ይቅርታ አሰጣጥ ሥርዐት አለመኖር፣ ከማረሚያ ቤት ወደ ሌላ ማረሚያ ቤት ተዘዋውሮ ለመሄድ ችግሮች መኖራቸው እና በማረሚያ ቤቶች የክስ ማመልከቻ ሳይደርሳቸው በቀጠሮ ታስረው የሚገኙ ታራሚዎች መበራከት ካሉት አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል መሆናቸው በሪፖርቱ ተለይተው በመድረኩ ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በዝግጅቱ ወቅት የመክፈቻ ንግግር ያሰሙት የኢሰመኮ አሶሳ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጉርሜሳ በፉጣ “ በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች መብቶቻቸውን፣ ነጻነቶቻቸውንና ሰብአዊ ክብራቸውን ለመጠበቅ የማረሚያ ቤቶች አመራሮች በየማረሚያ ቤቶቹ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር የእስረኞችን ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ለማሻሻል ሊሠሩ ይገባል” በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የእስረኞችን የመኖሪያ ክፍሎች እና መሰረታዊ ፍላጎቶች ለማሟላት ከፍተኛ የሆነ የበጀት ችግር፣  በሰብአዊ መብቶች አያያዝ ዙሪያ የግንዛቤ እጥረት፣  በተወሰኑ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ፖሊሶች ላይ የሚስተዋሉ የሥነ ምግባር ችግሮች መኖራቸው፣ እንዲሁም ከወቅታዊው የኑሮ ውድነት ጋር በተያያዘ በቀን ለእስረኞች የተመደበው በጀት ዝቅተኛ መሆኑ፣ በመንግሥት በኩል ለክልሉ ማረሚያ ቤቶች የሚደረገው ክትትልና ድጋፍ አናሳ መሆን እና የግብአቶች አለመሟላት ማረሚያ ቤቶችን እያጋጠሙ ካሉ ተግዳሮቶች መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በኮሚሽኑ ክትትል ከተደረገ በኋላ በማረሚያ ቤቶች የ44 ታራሚዎች ዝውዉር መደረጉ፣ ተቋርጦ የነበረው የታረሚዎች ክፍል ግንባታ መቀጠሉ፣ የማረሚያ ቤት አዋጅ መሻሻሉ፣ በቀን ለአንድ ታራሚ ወጪ 26.50 ብር የነበረው ወደ 40.00 ብር መሻሻሉ፣ የሥነ-ምግባር ጉድለት ያለባቸዉ የማረሚያ ቤቱ የሰራዊት አባላትና ኮሚቴዎች በሕግ ተጠያቂ እንደሚደረጉ እና የውሃ ችግርን በዘላቂነት ለመቅረፍ ከዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ድርጅት ጋር መፈራረማቸውን በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙ በየደረጃው ያሉ የማረሚያ ቤት ኃላፊዎችና የክልሉ ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር ገልጸዋል።

በመጨረሻም ተሳታፊዎቹ የውይይት መድረኩ በማረሚያ ቤቶች አመራሮች ቀድመው ያልተለዩ ክፍተቶችን ያሳየና ቀጣይ መሠራት ያለባቸውን አቅጣጫዎች ያስቀመጠ በመሆኑ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ አክለውም ያልተፈጸሙ ምክረ ሃሳቦችን በ2015 ዓ.ም. ዕቅድ ውስጥ አካትተው እንደሚተገብሩ ገልጸው የውይይት መድረኩ ተጠናቋል፡፡