የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) በኦሮሚያ ክልል ያለው የእስረኞች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ እንደሚያሳስበው ገለጸ። ኮሚሽኑ ከህዳር 11 ቀን 2013 ዓ.ም.  እስከ ጥር 04 ቀን 2013 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ በክልሉ ያለውን የእስረኞችን አያያዝ ሁኔታ በተመለከተ በተለይም የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በቁጥጥር የዋሉ ተጠርጣሪዎችን ጨምሮ ሌሎችም “በወቅታዊ ሁኔታ” (“haala yeroo”) የተያዙ የሚባሉ ብዛት ያላቸው እስረኞች ከሚገኙባቸውና ተደጋጋሚ ቅሬታዎች ከሚቀርቡባቸው መካከል በ21  የተመረጡ ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ክትትል አድርጓል። በክትትሉም ከእስረኞች እና የፖሊስ ጣቢያዎቹ ኃላፊዎች ጋር ተወያይቷል፣ እንዲሁም የክትትሉን ግኝቶች ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የክልሉ የሕግ አስከባሪ እና የአስተዳደር አካላት በማሳወቅ ምላሽ እንዲሰጥባቸው ጠይቋል። 

ኮሚሽኑ በጎበኛቸው የፖሊስ ጣቢያዎች በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢና በአፋጣኝ ሊሻሻል የሚገባው ነው። በፖሊስ ጣቢያዎቹ ብዙ ሰዎች ያለ ፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ “በወቅታዊ ሁኔታ” የተጠረጠሩ ናቸው በሚል መታሰራቸውን፣ ከነዚህም አብዛኛዎቹ ምርመራ ሳይጀመርባቸው እና ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በሕግ ከተቀመጠው ጊዜ በላይ ታስረው እንደቆዩ የሚያመላክቱ አሳማኝ መረጃዎች ቀርበዋል። በተጨማሪም በብዙ ፖሊስ ጣቢያዎች ዐቃቤ ሕግ በቂ መረጃ ባለመገኘቱ ምክንያት “የአያስከስስም ውሳኔ” የሰጠባቸው ወይም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሠረት መለቀቅ የነበረባቸው ተጠርጣሪዎች ዋና ተሳታፊ ናቸው ወይም በሌላ ወንጀል ይፈለጋሉ በሚል ያለ አግባብ ታስረው እንዲቆዩ የሚደረጉ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል። 

የተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች ኃላፊዎች “በወቅታዊ ሁኔታ” ተጠርጥረው የታሰሩ እስረኞች ጉዳያቸው የሚታየው በዞን እና በወረዳ ደረጃ በተቋቋሙ “የፀጥታ ምክር ቤቶች” (Mana maree  nageenyaa) መሆኑን ይገልጻሉ። ይህ አሰራር ብዛት ያላቸው ተጠርጣሪዎችን በሕግ ከመዳኘት ይልቅ የፖለቲካ (የአስተዳደራዊ) ውሳኔዎች ሰለባ እንዲሆኑ አድርጓል። 

ክትትል በተደረገባቸው የፖሊስ ጣቢያዎች ከሚገኙት እስረኞች መካከል የተወሰኑት በፖሊሶች በሚያዙበት ወቅት እንዲሁም በፖሊስ ጣቢያ ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ድብደባ እንደተፈጸመባቸው የገለጹ ሲሆን የክትትል ቡድኑም በተለያየ የሰውነታቸው ክፍሎች ላይ ጉዳት

የደረሰባቸውን እና ለጊዜያዊ እና ቋሚ የአካል ጉዳት የተዳረጉ እስረኞች መኖራቸውን ተመልክቷል። ኮሚሽኑ በተወሰኑ ቦታዎች “የኦነግ ሸኔ” አባል ወይም ደጋፊ ናቸው በሚል የሚፈለጉ “ልጆቻችሁን አቅርቡ” በማለት አባት ወይም እናትን የማሰር፤ “ባልሽን አቅርቢ” በማለት ሚስትን የማሰር ተግባር እንደሚፈጸም ከተለያዩ ታሳሪዎች አሳማኝ ምስክርነቶችን ተቀብሏል። እንዲሁም በተወሰኑ ቦታዎች ሰዎችን ያለ አግባብ በማሰር “የኦነግ ሸኔ” አባል ናችሁ ብለን አንከሳችኋለን በማለት በማስፈራራት ገንዘብ የመጠየቅ ሁኔታዎች መኖራቸውን የተለያዩ እስረኞች ቅሬታዎችን አቅርበዋል። 

ክትትሉ በተደረገባቸው በሁሉም ፖሊስ ጣቢያዎች ሴት እስረኞች የነበሩ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የተወሰኑት እድሜያቸው ከ 5 ወር አስከ 10 ዓመት የሚሆናቸው ሕጻናት ልጆቻቸውን ይዘው የታሰሩ ናቸው። በሌላ በኩል በወንጀል ነክ ጉዳዮች ተሳታፊ ናቸው በሚል ተጠርጥረው የሚታሰሩ ሕጻናት በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀፅ 172 መሠረት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በዋስ እንዲለቀቁ ቢጠበቅም፤ በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች ከ 9 እስከ 18 ዓመት የሚሆናቸው ሕጻናት አካለ መጠን ከደረሱ ሰዎች ጋር ተቀላቅለው በእስር ላይ እንደሚገኙ ኮሚሽኑ ተመልክቷል።  

የኢሰመኮ የክትትል ቡድን በተመለከታቸው በአብዛኛዎቹ ፖሊስ ጣቢያዎች ተጠርጣሪዎች ንፅህናቸው ባልተጠበቀ እና በጣም በተጨናነቁ ክፍሎች ለጤና ጎጂ በሆነ መልኩ እንደሚያዙ፣ የምግብ አቅርቦት አለመኖሩን እንዲሁም የውሃ፣ የመጸዳጃ እና የሕክምና አገልግሎት አቅርቦት ችግር መኖሩን ለመረዳት ተችሏል። 

ይህ ክትትል ከተደረገ በኃላ የተሻሻሉ ነገሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ቢገመትም በተለይም ሰዎችን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከማስርና የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ ከማክበር ጋር የተያየዙ ችግሮች አሁንም ድረስ የቀጠሉ መሆናቸው ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ 

የኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተጠቀሱትን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በተመለከተ ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር የምርመራ ቡድን በማዋቀር የማጣራት ሥራ መሥራቱን ጠቅሶ ግኝቶቹን በማስተባበል ዝርዝር ምላሽ ሰጥቷል። 

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በክልሉ ያለው የእስረኞች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ አፋጣኝ መፍትሄ የሚያሻው መሆኑን በመግለጽ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለረጅም ጊዜ በእስር ላይ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች ምርመራቸው እንዲፋጠን እና ፍርድ ቤት ቀርበው ፍትሐዊ ውሳኔ እንዲያገኙ እንዲደረግ፣ በእስረኞች ላይ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን የፈጸሙ የፖሊስ አባላት ተጠያቂ እንዲሆኑ እንዲደረግ እንዲሁም ለሕጻናት እና ሴቶች ተጠርጣሪዎች ቅድሚያ በመስጠት በተለይ በወንጀል ነክ ጉዳዮች ተሳታፊ ናቸው በሚል ተጠርጥረው የታሰሩ ሕጻናት በሕጉ መሠረት በአፋጣኝ በዋስ እንዲለቀቁ አሳስበዋል። ዶ/ር ዳንኤል በቀለ አክለውም “በወንጀል የተጠረጠሩ

ሰዎች የዳኝነት ጉዳይ በሕግ የዳኝነት ስልጣን በተሰጣቸው ፍርድ ቤቶች ብቻ እንዲታዩ ማድረግና የፍርድ ቤቶችን ትዕዛዝ ማክበር ልዩ ትኩረት ያስፈልገዋል” ብለዋል። 

ለተጨማሪ መረጃ:
አሮን ማሾ (አማርኛ እና እንግሊዝኛ)
የኮምዩኒኬሽንስ ዳይሬክተር እና ቃል አቀባይ
+251 911364027
aaron.maasho@ehrc.org

ኢማድ አብዱልፈታህ (አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ እንግሊዝኛ)
ዳይሬክተር
+251 912302392
imad.abdulfetah@ehrc.org

ምስጋናው ሙሉጌታ (አማርኛ እና እንግሊዝኛ)
ዳይሬክተር
+251 911105771
mesganaw.mulugeta@ehrc.org