የባለሙያ አስተያየት ከኢሰመኮ 
ሜቲ አቶምሳ
የአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር
@AtomssaMeti

ዓለም አቀፉ የአካል ጉዳተኞች ቀን የአካል ጉዳተኞችን መብቶችና ደኅንነቶች የማስፋፋት ዓላማን አንግቦ በየዓመቱ ኅዳር 23 ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ይከበራል። በተመሳሳይ ቀኑ በአካል ጉዳተኞች መብቶች ዙሪያ እና ማኅበረሰቡ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ አካል ጉዳተኞች ላይ የሚያደርሰውን መድሎ በተመለከት ግንዛቤ ለመፍጠር ዓላማ ይውላል። ቀኑን ለማስታወስ የፓናል ውይይቶች፣ ኤግዚቢሽኖች እንዲሁም የተለያዩ ባህላዊ ዝግጅቶትን ጨምሮ ልዩ ልዩ መርኃ ግብሮች ይሰናዳሉ። ሆኖም ዕለቱን አስመልክቶ የሚሰናዱ መርኃ ግብሮችን ከዕለቱ ዓላማ እና መልእክት ጋር ማጣጣም ወሳኝ ነው።

በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች የትምህርት እድል፣ የጤና እንክብካቤ፣ የሥራ ዕድል፣ ማኅበራዊ ጥበቃ አለማግኘትን እንዲሁም በማኅበረሰቡ ዘንድ ከተንሰራፋው የተዘባ አመለካከት በሚመነጩ እንቅፋቶች ምክንያት የሚደርስ መድልዎን ጨምሮ በርካታ ተግዳሮቶች ይገጥሟቸዋል። መንግሥት ተደራሽነትን እና የአካል ጉዳተኞችን መካተት ለማረጋገጥ ተጨባጭ የሆኑ ውጤቶችን በማስመዝገብ ቁርጠኝነት ማሳየትን ጨምሮ የሰብአዊ መብቶች መስፋፋት እና ጥበቃን በማረጋገጥ ረገድ ተቀዳሚ ኃላፊነት አለበት። ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ለአካል ጉዳተኞች መብቶች በመታገል እና በመወትወት መሪነታቸውን እና ቁርጠኝነታቸውን ማሳየት አለባቸው።

የአካል ጉዳተኞች ማኅበራትን እና ባለድርሻ አካላትን በማማከር የተዘጋጀው የዚህ ዓመት ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን መሪ ቃል ለአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ስኬት ትርጉም ያለው ትብብር – ለአካል ጉዳተኞች፣ ከአካል ጉዳተኞች ጋር እና በአካል ጉዳተኞች!” የሚል ነው። ዓለም አቀፉ ዘመቻ ድኽነትን ለማስቀረት እና ሁሉም ሰዎች በእኩል ሰብአዊ መብቶቻቸውን እንዲጠቀሙ ለማስቻል የተቀመጡትን ዘላቂ የልማት ግቦች ስኬት ለሚያደናቅፉ እንቅፋቶች ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል መንገድ የመጥረግ ዓላማ አለው።

በዓሉን የሚያስቡ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን መርሖች በመከተል ክንውኖቻቸው ቀኑ ከሚከበርበት ዋና ዓላማ ጋር መጣጣማቸውን ሊያረጋግጡ ይችላሉ።

  • የአካል ጉዳተኛ ማኅበረሰብንና ማኅበራትን ማማከርና ማሳተፍ:– በአብዛኛው እንዲህ ያሉ ቀናት ከአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ጋር በመተባበር መከበር ያለባቸው ሲሆን ይህም ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ የድርጊት መረኃ ግብሮችን ለመለየት፣ በጥሩ ሁኔታ ምላሽ ለመስጠት እና በፕሮጀክት እና በፕሮግራም ክንውኖች ወቅት ከቀረጻው ጀምሮ እስከ ትግበራው ድረስ የባለመብቶችን ሐሳብ ለማግኘት ጠቀሜታ ይኖረዋል 
  • ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ግቦችን ማስቀመጥ:- በተግባር ሊፈጸሙና ሊለኩ የሚችሉ እንዲሁም ባለግዴታዎች ላልፈጸሟቸው ጉዳዮች ተጠያቂ የሚሆኑባቸው ክንውኖች ላይ ትኩረት ለማድረግ የሚረዱ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ግቦችን ማስቀመጥ፤ 
  • ዘለቄታዊነት:- የአካል ጉዳተኞችን መብቶች ለማስፋፋት እና ለመጠበቅ የሚደረጉ ጥረቶችና እንቅስቃሴዎች ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ፣ ዘለቄታዊ የሆኑ እና ዘለቄታዊ ተጽዕኖ መፍጠር የሚችሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ፤ 
  • የውትወታ ስልት:- ሁሉም ባለድርሻ አካላት የአካል ጉዳተኞችን መብቶችና ደኅንነትን የሚያስፋፉ የፖሊሲ እና የአሠራር ለውጦችን ለማምጣት ውትወታ እንዲያደርጉ ፖለቲካዊ ፍቃዳቸውንና ቁርጠኝነታቸውን ለመጠየቅ እና ቅስቀሳ ለማድረግ ዓለም አቀፉ የአካል ጉዳተኞች ቀን እንደ መልካም አጋጣሚ በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋሉን ማረጋገጥ፤ 
  • የማኅበራዊ ሚዲያን ዐቅም በአግባቡ መጠቀም፦ ባህላዊና አዳዲስ ሚዲያን እንዲሁም ለበርካታ ታዳሚዎች ተደራሽ የሚሆኑ የፈጠራ መንገዶችን በአግባቡ መጠቀማችንን ማረጋገጥ እና ሰዎች ከአካል ጉዳተኞች የሕይወት ልምድ ሊማሩ የሚችሉበት ሁኔታ መፍጠር፤ 
  • ተደራሽነትና አካታችነትን በተግባር ማሳየት:- ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሆኑ፣ አካታች የንግድ ሥራዎች፣ የአካል ድጋፍ አገልግሎቶች እንዲሁም ሌሎች የተደራሽነትንና አካታችነትን አስፈላጊነት የሚያሳዩ ተግባራትን ጨምሮ የተደራሽነት እና የአካታችነት ሥራዎች በአግባቡ ታቅደው የሁሉም የዓለም አቀፍ አካል ጉዳተኞች ቀን ክንውኖች አካል እንደሆኑ ማረጋገጥ።