የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) “የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የመሳተፍ መብት ስላላቸው ድምፃቸው ሊሰማ ይገባል!” በሚል መሪ ቃል ከሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ተወካዮች ጋር ተወያየ፡፡ ነሐሴ 7 እና 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ለሁለት ቀናት የተካሄደው ውይይት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በሚመለከቷቸው ጉዳዮች ላይ ሁሉ እንዲሳተፉ ለማድረግ፣ ስለመብቶቻቸው ግንዛቤን ለማሳደግ እንዲሁም መብታቸውን እንዲጠይቁ ለማብቃት ያለመ ነው። ውይይቱም የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ የፌዴራል መንግሥት ተቋማት፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ ዓለም አቀፍ የልማት ተቋማት፣ የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች እንዲሁም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች እና ባለሙያዎች የተሳተፉበት ነው፡፡

Dialogue with the internally displaced persons and the communities affected by internal displacement
የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች

በውይይቱ ኮሚሽኑ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መብቶች ሁኔታን አስመልክቶ ያካሄዳቸው የክትትል እና ምርመራ ሥራዎች ላይ እንዲሁም የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች በሚባሉት የምዝገባና ሰነድ የማግኘት፣ የጸጥታ እና ደኅንነት ሥጋት፣ የተሳትፎና የመንቀሳቀስ መብት፣ የሰብአዊ ድጋፍ፣ ማኅበራዊ አገልግሎቶች አቅርቦት፣ ልዩ ድጋፍ ለሚሹ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚደረግ የሰብአዊ ድጋፍ እና የዘላቂ መፍትሔዎች ምንነትን የተመለከተ ማብራሪያ ተሰጥቷል። ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚደረገው የሰብአዊ ድጋፍ በዋነኝነት የነፍስ አድን ድጋፍ ላይ ያተኮረ በመሆኑ በተለይም ሴቶች፣ ሕፃናት፣ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን በከባድ እና ፈታኝ ችግር ውስጥ አልፈው እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተጎጂዎች ሆነው የመጡ ቢሆንም የሥነ-ልቦና እና ማኅበራዊ ድጋፍ (Psychosocial Support) አለማግኘታቸው እንደክፍተት ተጠቅሷል።

Dialogue with the internally displaced persons and the communities affected by internal displacement
የቡድን ውይይት

በተጨማሪም በአፋር፣ በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሊ እና በትግራይ ክልሎች የሚገኙ የሀገር ውስጥ የተፈናቃዮች ተወካዮች፤ አሳሳቢ ብለው ከለዩዋቸው የሰብአዊ መብት ጉዳዮች አንጻር እያጋጠሟቸው ያሉ ተግዳሮቶችን ለተሳታፊዎች አጋርተዋል። በዚህም ‘በደኅንነት ሥጋት እና በጸጥታ ችግር ምክንያት ከቀድሞ ቀያችን ሕይወታችንን ለማትረፍ የሸሸን ቢሆንም፤ አሁንም ተጠልለን ባለንባቸው አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ የትጥቅ ግጭቶች እና የጸጥታ ችግሮች ለዳግም መፈናቀል እንዳይዳርጉን ሥጋት አድሮብናል’ ያሉ ሲሆን “የጸጥታው ችግር እየተቆራረጠም ቢሆን የሚደረግልንን ሰብአዊ ድጋፍ እንዲስተጓጎል አድርጎታል” በማለት ገልጸዋል።

Dialogue with the internally displaced persons and the communities affected by internal displacement
የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች

በተመሳሳይ የመንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተወካዮች እና ባለሙያዎች ለተፈናቃዮች የተሟላ ድጋፍ እና ጥበቃን ለማድረግ በዘርፉ የተሰማሩ አካላትን ሥራዎች ለማስተባበር በሕግ ግልጽ ሥልጣን የተሰጠው አካል አለመኖሩ ቅንጅታዊ አሠራር እንዳይኖር በማድረግ፤ ለተፈናቃዮች የሚያደርጉት የጥበቃ እና የድጋፍ ተግባራት ላይ ክፍተት እየፈጠረ መሆኑን ጠቅሰዋል። የሰላም ሚኒስቴር ተወካይ በበኩላቸው በተሳታፊዎች የተለዩትን ክፍተቶች ለመፍታት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መብቶች ጥበቃ ረቂቅ አዋጅ ያስቀመጣቸውን መፍትሔዎች አስመልከቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

Dialogue with the internally displaced
የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እልባት ያላገኙ፣ በተለያየ ጊዜ የሚያገረሹ ወይም በአዲስ መልኩ የሚከሰቱ የታጠቁ ቡድኖች ጥቃቶች እና የትጥቅ ግጭቶች የሰዎች በሕይወት የመኖር፣ የአካላዊ ደኅንነት እና የንብረት መብቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ በመፍጠር፤ ሰዎች የመኖሪያ ቀያቸውን ለቀው እንዲሸሹ፣ በተራዘመ የመፈናቀል ሁኔታ ውስጥ እንዲቆዩ እና በዘላቂነት ተቋቁመው ወደ ቀደመው ሕይወታቸው እንዳይመለሱ እንቅፋት መሆናቸውን ገልጸዋል። ስለሆነም ለግጭቶች አፋጣኝ፣ ሰላማዊ እና ዘላቂ መፍትሔ በመስጥ የአዲስ እና የተራዘመ መፈናቀል መንስኤዎችን መከላከል ላይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል። አክለውም ኮሚሽኑ መፈናቀልን የመከላከል፣ ለተፈናቃዮች ድምፅ ለመሆን እና የተፈናቀሉ ሰዎች ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኙ የሚያከናውነውን የውትወታ ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።