የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጣምራ ጋዜጣዊ መግለጫ

ጥር 26 ቀን 2015 ዓ.ም.

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋር የሰብአዊ መብቶች ትምህርትን በመደበኛ እና መደበኛ ባልሆኑ የትምህርት ሥርዓቶች ውስጥ ለማካተት እና ለማጠናከር የመግባቢያ ስምምነት (MoU) ጥር 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ተፈራርሟል፡፡

ስምምነቱ የሰብአዊ መብቶች እሴቶችን ወደ ማኅበረሰቡ ከማስረጽ አኳያ ተደራሽነትን በመጨመር በኢትዮጵያ ዘላቂና ውጤታማ በሆነ መንገድ የሰብአዊ መብቶች ባህልን ለማስፈን ከፍተኛ አስተዋፅዖ አለው፡፡ በተጨማሪም ተማሪዎች ስለ እኩልነት፣ ሰብአዊ ክብር፣ ፍትሐዊነት፣ ሰላም፣ መከባበርና ኃላፊነት እውቀት በማዳበር የሰብአዊ መብቶች እሴቶች መገለጫ የሆኑ የባህሪና የአመለካከት ለውጦችን እንዲያመጡ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ይታመናል፡፡ 

የሰብአዊ መብቶች ትምህርትን በመደበኛ እና መደበኛ ባልሆኑ የትምህርት ሥርዓቶች ውስጥ በአግባቡ እንዲካተት፣ እንዲጠናከር እና እንዲስፋፋ በጋራ መሥራትን፤ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት በተጓዳኝ የትምህርት መንገዶች በተለይም በክለቦችና በሌሎች የማስተማሪያ ማእቀፎች ለተማሪዎች የሚደርስበትን ሁኔታ ማመቻቸት እና ከሌሎች መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር መተባበር የሚሉ ዝርዝር ዓላማዎችን ስምምነቱ አካቷል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ትምህርትና ስልጠና መግለጫ እንዳስቀመጠው የሰብአዊ መብቶች ትምህርትና ስልጠና በሁሉም የዕድሜ ክልል ያሉ ሰዎችን የሚመለከት የዕድሜ ልክ ሂደት መሆኑንና ይህም ከመዋዕለ ሕፃናት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ ባሉ የትምህርት ደረጃዎች ለሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች መዳረስ ያለበት የሰብአዊ መብት ጥያቄ ነው፡፡ በሁለቱ ተቋማት የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ይህንን ሂደት ተግባራዊ በማድረግ ረገድ አስተዋፅዖ የሚኖረው ሲሆን ከዚህ ጋር ተያይዞ ሁለቱ ተቋማት ያለባቸውን ኃላፊነቶች በጋራ እና በመተባበር እንዲወጡ የሚያግዝ ነው።  

በመግባቢያ ስምምነቱ መሠረት የትምህርት ሚኒስቴር የሰብአዊ መብቶች ትምህርትን አመቺ በሆኑ የትምህርት ዓይነቶች በተለይም በግብረ-ገብና በዜግነት ትምህርቶች በግልፅና ትርጉም ባለው ደረጃ መካተታቸውን ለማረጋግጥ እና በተጓዳኝ የትምህርት ዘርፎችም እንዲሰጥ ይሠራል። በተጨማሪም በመምህራን ማሰልጠኛ ተቋማት ሥራ ላይ ያሉ ሥርዓተ-ትምህርቶች እና የስልጠና መጻሕፍት ይዘት በተሟላ መንገድ የሰብአዊ መብቶችን ፅንሰ-ሃሳብና መርሆች እውቀት የሚያስጨብጥ መሆኑን ለማረጋገጥ እና በየዓመቱ ኮሚሽኑ የሚያካሂደውን ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ምስለ ፍርድ ቤት (Moot Court) ውድድር በተመለከተ አስፈላጊውን ትብብር ለማድረግ እንደሚሠራ በስምምነቱ ተካቷል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ በዋናነት የሙያ ድጋፍ ለመስጠት፣ ለሰብአዊ መብቶች ትምህርት ማስተማሪያ የሚሆኑ ለመምህራንም ሆነ ለተማሪዎች የሚያገለግሉ የተለያዩ ደጋፊ ጽሑፎች የሚገኙበት የመረጃ ቋት (ዳታ ቤዝ) ለማዘጋጀት፣ ትምህርት ቤቶች በመደበኛው እና በተጓዳኝ ሥርዓተ-ትምህርቶች ሰብአዊ መብቶችን ለማስረጽ የዕለት ተዕለት የትምህርት ሂደቱ አካል አድርገው የሚሠሩ እንዲሆኑ ለመደገፍ እና በየዓመቱ የሚያካሂደውን ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ምስለ ፍርድ ቤት ውድድር አጠናክሮ ለመቀጠል ተስማምቷል፡፡

በስምምነቱ መፈራረሚያ ሥነ-ሥርዓት ላይ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “የሰብአዊ መብቶች እሴቶችንና መርሆችን ተገንዝቦ በዕለት ተዕለት ግንኙነቱና በባህሪው የሚያንፀባርቅ ትውልድ መፍጠር፤ በመከባበር፣ በመቻቻልና በመግባባት በሰላም አብሮ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ማኅበረሰብን ለመገንባት የሚያስችል እርምጃ ነው” ብለዋል። አክለውም ዘላቂ የልማት ግብ 4.7ን (ትምህርት ለዘላቂ ልማትና ለዓለም አቀፋዊ ዜግነት/Education for sustainable development and global citizenship) ለማሳካት ከፍያለ አስተዋፅዖ ይኖረዋል ሲሉ አብራርተዋል።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ትምህርት ሚኒስትር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ እና የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ሲሆኑ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለን ጨምሮ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌና ዶ/ር ፋንታ ማንደፍሮ እንዲሁም የሁለቱም ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።