የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ኅዳር 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ተከብሮ የዋለውን ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን ምክንያት በማድረግ ከአሜሪካ ኤምባሲ፣ ላይት ፎር ዘ ዎርልድ እና የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር የፓናል ውይይቶች፣ የማነቃቅያ ንግግሮች እና የኪነጥበብ ሥራዎችን ያካተተ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ኅዳር 27 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አከናውኗል፡፡ 

በዝግጅቱ ላይ ሁለት የፓናል ውይይቶች የተደረጉ ሲሆን የመጀመሪያው የፓናል ውይይት አካታች የሥራ ቦታን መፍጠር በሚል ርእስ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ አካል ጉዳተኞች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ በሆኑት ሙሴ ጥላሁን አወያይነት ተካሂዷል፡፡ በዚህ የፓናል ውይይት ኢሰመኮ፣ የአሜሪካ ኤምባሲ፣ ፍቅር የኢትዮጵያ አእምሮ እድገት ውስንነት ብሔራዊ ማኅበር፣ ሞዛይክ ሆቴል እንዲሁም ኢትዮ-ጆብስ የተወከሉ ሲሆን የአካል ጉዳተኞችን የመሥራት መብት ለማክበርና ለማስከበር መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች፣ መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በተመሳሳይ በጋዜጠኛ የኔአለም ካሳሁን የተመራው ሁለተኛው የፓናል ውይይት የኪነጥበብ ባለሞያ፣ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሞያ እና የፋሽን ባለሞያ የተሳተፉበት ሲሆን የቴአትርና ፊልም ሥራዎች፣ የፋሽን ሥራዎች እና የማኅበራዊ ሚድያ አካታችነት የተዳሰሰበት ነበር፡፡

በቴዴክስ አነቃቂ ንግግሮችን በማድረግ የሚታወቀው አሜሪካዊ የእግር ጉዳተኛ ጆን ሬጂስተር እና በተኪ የወረቀት ማምረቻ የፕሮጀክት አስተባባሪ የሆነችው መስማት የተሳናት ትዕግስት አለማየሁ ያካፈሉት የሕይወት ተሞክሮ አካል ጉዳተኞች በተለይም ከአመለካከት አንጻር የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች ሁሉ አልፈው ስኬታማ መሆን እንደሚችሉ በማሳየት ረገድ በልዩ ሁኔታ ትምህርት የሰጠ መሆኑን ተሳታፊዎች ገልጸዋል። 

ይህንን ዓመታዊ በዓል ምክንያት በማድረግ በአካል ጉዳተኞች ሰብአዊ መብቶች ዙሪያ በኢሰመኮ የሁለት ቀናት ስልጠና ወስደው የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ያካሄዱ የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎች በማኅበራዊ ሚድያ ገጾቻቸው ያጋሯቸው የተለያዩ ቪዲዮዎች እና ጽሑፎች፣ በመሥራት መብት ዙሪያ የሚያጠነጥን በኮሚሽኑ የተዘጋጀ አጭር ቪዲዮ እና በአሜሪካን ኤምባሲ የተዘጋጀ Breaking Barriers የተባለ ቪዲዮ ለተሳታፊዎች ቀርበዋል።  

እንዲሁም የካቲም ዲሴቢሊቲ ዳንስ ኤንድ አርቲስትሪ በአካታችነት ዙርያ ያተኮረ የኪነ ጥበብ ሥራ፣ በአካል ጉዳተኞች የተሠሩ የእደ ጥበብ ሥራዎች፣ አልባሳት፣ የወረቀት ቦርሳዎች እና ልዩ ልዩ ሥዕሎች ለእይታ ቀርበዋል፡፡ 

የኢሰመኮ የአረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረ ሐዋርያ በመክፈቻ ንግግራቸው ባስተላለፉት መልዕክት “የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን አካታች የፈጠራ ሥራና ሽግግራዊ መፍትሔ ለኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተደራሽነት በሚል መሪ ቃል ሲከበር የፈጠራ ሥራዎች አካታች ለሆነ የሥራ እድገት፣ እኩልነትን ለማረጋገጥና መድሏዊ አሠራርን ለማስወገድ በአጠቃላይ አካታች የሆነ እድገትን ለማምጣት የሚኖራቸውን ሚና በማጉላት ነው” ብለዋል፡፡

የኢሰመኮ የሴቶች እና ሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ በሰጡት ማጠቃለያ የኪነ-ጥበብ ሥራዎች የሰብአዊ መብቶች ዕሴቶችን ለማስተማር አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ሚና ያላቸው መሆኑን በመጥቀስ አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አክለውም በኪነጥበብ ሥራዎች ውስጥ አካል ጉዳተኛ ገጸ ባሕርያት የሚወከሉበት መንገድ ትኩረት እንዲሰጠው ጥሪ አቅርበዋል፡፡