የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የትምህርት ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽነት እና አካታችነት ላይ ያተኮረ የሰብአዊ መብቶች ክትትል በአዲስ አበባ፣ በጅማ፣ በጎንደር፣ በሃዋሳ እና በሐረማያ ዩኒቨርሲቲዎች አካሂዷል። ክትትሉን ተከትሎ በተዘጋጀው ረቂቅ ሪፖርት የተለዩ ዋና ዋና አሳሳቢ ጉዳዮች እና የቀረቡ ምክረ ሃሳቦች ዙሪያ ጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ክትትሉ የተደረገባቸውና ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚደንቶች፣ የመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎች፣ የልዩ ፍላጎት ማእከላት ተወካዮች፣ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች እና ሌሎች ባለድርሻዎች በተገኙበት ውይይት ተካሂዷል።

በዩኒቨርሲቲዎቹ ለተካሄደው የሰብአዊ መብቶች ክትትል መነሻ የሆነው በተማሪ ቢኒያም ኢሳያስ የቀረበው አቤቱታ ሲሆን፤ ተማሪ ቢኒያም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የአራተኛ ዓመት የሕክምና ትምህርቱን እየተከታተለ ባለበት ወቅት የአካል ጉዳት ስላለበት የትምህርት መስኩን እንዲቀይር ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ አማራጮችን መስጠቱ፤ በኋላም ቢኒያም ባቀረበው አቤቱታ እና የተለያዩ የውትወታ ሥራዎች ትምህርቱን እንዲቀጥል መወሰኑ የሚታወስ ነው።

ክትትሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ተካታችነት ለማረጋገጥ የሚረዳ የፖሊሲ፣ የሕግ እና የአሠራር ማሻሻያ እንዲደረግ ተግዳሮቶችን በመለየት መፍትሔ ለማመላከት ያለመ ነው። በክትትል ሥራው ላይ ኢሰመኮን ጨምሮ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ አካል ጉዳተኞች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበር፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ማእከል እና የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን ያቀፈ የሥራ ቡድን በማቋቋም የተከናወነ ነው፡፡

የውይይት መድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረ ሐዋርያ “የክትትሉ እና የምክክሩ ዓላማ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ሰብአዊ መብቶች ማክበር እና ማስከበር ነው” ብለዋል። አክለውም “በክትትል ግኝቱ ላይ ለተለዩ ስልታዊ የመብቶች ጥሰት የሕግና ፖሊሲ ማሻሻያዎችን ለማድረግ እንዲሁም የተግባር ምላሽ ለመስጠት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ጽሕፈት ቤት አማካሪ ኢንጂነር ውብአየሁ ማሞ በዝግጅቱ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት፤ ዩኒቨርሲቲዎች ምንም እንኳን የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ተካታችነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ሥራዎችን የሠሩ ቢሆንም፤ አሁንም ክፍተቶች በስፋት የሚስተዋሉ በመሆኑ ይህንኑ ለመቀየር በጋራ ለመሥራት ያላቸውን አቋም ገልጸዋል፡፡

ለውይይት በቀረበው ረቂቅ ሪፖርት አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ለማካተት እና ተቋማቱን ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም በአጠቃላይ ክትትሉ የተካሄደባቸው ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ አለመሆናቸውን፣ ከፍተኛ የከባቢያዊ፣ የአመለካከት፣ የተግባቦት እና ተቋማዊ መሰናክሎች መኖራቸው ተመላክቷል፡፡ በተጨማሪም የፖሊሲ፣ የአሠራር፣ የአመለካከት እና በልዩ ሁኔታም ሴት አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን የተመለከቱ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ሊሠሩ የሚገባቸውን ሥራዎች አካቷል ፡፡

የምክክር መድረኩ በየተቋማቱ ያሉ በጎ ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ ምቹ ዕድልን ፈጥሯል። ተሳታፊዎችም የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ተካታችነት ለማረጋገጥ አሁንም በርካታ ሊሠሩ የሚገባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ ኢሰመኮ በምክክሩ የተነሱ ጉዳዮችን በማዳበር የክትትል ሪፖርቱን ይፋ የሚያደርግ እና ግኝቱን መሠረት በማድረግ የተለያዩ የጉትጎታ ሥራዎችን የሚሠራ ይሆናል፡፡