የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ያላቸውን የተደራሽነት እና አካታችነት ሁኔታ በተመለከተ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሕክምና ትምህርት ተማሪ የሆነው ቢኒያም ኢሳያስ ያቀረበውን አቤቱታ መነሻ በማድረግ ያከናወነውን የሰብአዊ መብቶች ክትትል ባለ 36 ገጽ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል። ክትትሉ ከነሐሴ 10 እስከ 13 ቀን 2014 ዓ.ም. በጎንደር፣ ሐረማያ፣ ሃዋሳ እና ጅማ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ከነሐሴ 17 እስከ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተከናውኗል።

ክትትሉ ከተቋማቱ ሕግጋት፣ ፖሊሲዎችና አሠራሮች የሚመነጩና አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የሚያጋጥሟቸው ተቋማዊ፣ ከባቢያዊ፣ የመረጃና ተግባቦት ተደራሽነት ጉድለቶችን እንዲሁም የአመለካከት ተግዳሮቶችን ለመለየት ያለመ ነው፡፡ በዚህም መሠረት አስፈላጊ መረጃዎችን ለማሰባሰብ ኮሚሽኑ አግባብነት ያላቸው ሰነዶች ላይ ያደረገውን ግምገማ ጨምሮ የመስክ ምልከታ፣ የቡድን ውይይት እና ልዩ ልዩ ቃለ መጠይቆችን አከናውኗል፡፡ ኢሰመኮ በአጠቃላይ ክትትሉ በተከናወነባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ከ74 መረጃ ሰጪዎች ጋር ቃለ መጠይቆችን ያከናወነ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል 34ቱ አካል ጉዳተኞች ናቸው፡፡

በክትትል ሪፖርቱ የትምህርት ተቋማቱ ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ያላቸውን ተቋማዊ፣ ከባቢያዊ እና የመረጃና ተግባቦት ተደራሽነት መጠን፣ በተደራሽነት ጉድለት ምክንያት የተከሰቱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዲሁም ከአመለካከት ጋር የሚገናኙ ተግዳሮቶች ተለይተው ቀርበዋል፡፡ በክትትሉ የተሸፈኑ ዩኒቨርሲቲዎች ተቋማዊ ተደራሽነትን በተመለከተ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ጉዳይ የሚመራበት የጽሑፍ ፖሊሲ አለመኖሩ፣ የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ በዋና ዕቅድ ውስጥ ተካቶ አለመሠራቱ እንዲሁም የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች በተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆኑ በሪፖርቱ ከተካተቱት ግኝቶች መካከል ናቸው። 

በተጨማሪም ከባቢያዊ እና የመረጃና ተግባቦት ተደራሽነትን አስመልክቶ ለልዩ ልዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ሕንጻዎችና መዳረሻ መንገዶች ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ምቹና ተደራሽ አለመሆን፣ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ በቂ መጸዳጃ ቤቶች አለመኖር፣ መስማት ለተሳናቸው ተማሪዎች በምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ እጥረት ምክንያት በቋንቋው የሚሰጥ የትምህርት አቅርቦት ውስንነት፣ እንዲሁም ለሴት አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የሚደረገው ተመጣጣኝ/ምክንያታዊ ማመቻቸት (reasonable accommodation) ዝቅተኛ መሆኑን የሚያመላክቱ ግኝቶች በሪፖርቱ ተካተዋል፡፡ ኢሰመኮ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች ያላቸውን ተደራሽነት እና አካታችነት የተሻለ ለማድረግ የሚያስችሉ እና ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ያስችላሉ ያላቸውን ምክረ ሐሳቦች በሪፖርቱ በዝርዝር አቅርቧል። የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ ‘‘ክትትሉ በአምስት ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የተከናወነ ቢሆንም የግኝቶቹን ምክረ ሐሳቦች አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን የሚያስተናግዱ የትምህርት ተቋማት ሁሉ ሊተገብሯቸው እና የአካል ጉዳተኞችን ትምህርት የማግኘት መብት ሊያረጋግጡ ይገባል’’ ብለዋል፡፡