የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ሄልፕኤጅ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ጋር በመሆን ስለ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ሰብአዊ መብቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና፣ የአረጋውያንን መብቶች ከማክበር እና ከማስጠበቅ አንጻር በሚወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎች ዙሪያ ምክክር እና መረጃዎችን ለማደራጀት እና ፍላጎቶችን የሚያመላክት የመረጃ ቋት/ዳታቤዝ አጠቃቀም ለተለያዩ በዘርፎቹ ለሚሰሩ ባለሞያዎች ስልጠና ሰጠ፡፡ ከመጋቢት 22 እስከ 24 2014 ዓ.ም. በተካሄደው በዚህ ስልጠና በክልል ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮዎችና በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞችና የአረጋውያን ዘርፍ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል። የአፍሪካ የሰብአዊና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር የአረጋውያን መብቶች ፕሮቶኮል (አንቀጽ 21)፣ የተ.መ.ድ የአካል ጉዳተኞች መብት ኮንቬንሽን (አንቀጽ 31) እንዲሁም ሌሎች ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው ስምምነቶች ሀገራት አረጋውያንን እና አካል ጉዳተኞችን አስመልክቶ በሥርዓት የተቀረጸ የመረጃ አሰባሰብና ትንተና መካሄዱን እንዲያረጋግጡ ይደነግጋሉ። 

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን በመወከል የአረጋውያን ጉዳይ ማስተባበሪያና ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዳምጠዉ አለሙ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ፤ ዘላቂነት ያለው የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት በዘርፍ የሚሠሩ ባለሙያዎችን አቅም መገንባት እና የመረጃ ሥርዓትን ማጠናከር ወሳኝ ጉዳዮች መሆናቸዉን እና ሰልጣኞች የተጣለባቸው የሙያ ግዴታ እና ኃላፊነት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

የአረጋውያን ጉዳይ ማስተባበሪያና ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዳምጠዉ አለሙ

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በበኩላቸው “ኮሚሽኑ ካደረጋቸዉ ለውጦች መካካል የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ላይ እራሱን የቻለ በኮሚሽነር ደረጃ የሚመራ የሥራ ክፍል እንዲኖረዉና በሁሉም የተቋሙ ተግባራት ውስጥ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶችን ጉዳይ አካቶ እንዲሠራ ማድረግ አንዱ መሆኑን አንስተዋል፡፡ “ኮሚሽኑ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ማስፋፋት፣ የሕግ ክፍተት ያሉባቸውን ወይም የተረሱ ፖሊሲዎችን እና አንዳንድ አግባብ ያልሆኑ አካሄዶችን እየለየ መብቶቻቸዉ በሕግ ማዕቀፎች ውስጥ እንዲካተቱና በዝርዝር እንዲቀመጡ፣ ሕጎች ተሻሽለዉ እንዲወጡ ጉትጎታዎችንና ውትወታዎችን ያደርጋል” በማለት የኮሚሽኑ በዘርፉ የሚኖረውን ሚና አብራርተዋል፡፡

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ

በስልጠናው ላይ በአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን የተመለከቱ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣ ፕሮቶኮሎች እና የሀገር ውስጥ ሕጎች የተዳሰሱ ሲሆን፣ የአረጋውያንን መብቶች ከማክበር እና ከማስጠበቅ አንጻር የሚወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎች ዙሪያ ውይይት አካሂዷል፡፡ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር እና ሄልፕኤጅ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ በበኩላቸዉ የአረጋውያን መረጃዎችን ለማደራጀት እና ፍላጎቶችን የሚያመላክት የመረጃ ቋት/ዳታቤዝ አጠቃቀም ስልጠና በጋራ ሰጥተዋል፡፡

በሀገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተገቢውን የስታትስቲክስ እና የምርምር መረጃዎችን መሰብሰብ ፖሊሲዎችን ቀርጾ ተግባራዊ ለማድረግ ይረዳል፡፡ የአካል ጉዳተኞችን እና አረጋውያንን ቁጥር እና ሁኔታቸውን መረዳት አካል ጉዳተኞችና አረጋውያን የሚያጋጥማቸዉን እንቅፋት ለመለየት፤ ሊገጥማቸዉ የሚችሉ መሰናክሎች በማስወገድ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተደራጀ መረጃ መኖር ወሳኝ ነዉ፡፡ የመረጃ አስተዳደር ሥርዓቱን መዘርጋት የተፈለገበት ምክንያት እንደ ሀገር ከፌዴራል እስከ ወረዳ ድረስ በአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ዙሪያ የመረጃ እጥረት ወይም ትክክለኛነት ስለሌለ ይህንን ችግር ለመቅረፍ አስፈላጊ በመሆኑ ነዉ፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች

የስልጠናዉ ተሳታፊዎች በአብዛኛው ከክልል ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮዎች እና ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መስራያ ቤት ተወካዮች ሲሆኑ፤ እስካሁን ድረስ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያንን በተመለከተ ካከናወኗቸው ተግባራት መካከል የሚከተሉትን ዋና ዋና ሥራዎች በመልካም ተሞክሮነት ተመዝግበዋል፦ 

 • በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያሉ አካል ጉዳተኞችን ሁኔታ የተመለከተ የዳሰሳ ጥናት መካሄድ፣ 
 • የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ማኅበራት ራሳቸውን ለማጠናከር እንዲረዳቸው ለማስቻል የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ ለመሳተፍ የሚያስችላቸው የንግድ ቦታዎች እንዲመቻችላቸው እና ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉ እና 
 • በማኅበራዊ ጥበቃ ፖሊሲው አማካኝነት በርካታ ቁጥር ያላቸው አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች የሴፍቲኔት ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉ። 

በሌላ በኩል በዋናነት አካል ጉዳተኞችን እና አረጋውያንን 

 • የተመለከቱት ሕጎች ቀጥተኛ እና ተጠያቂነትን ለማስፈን ምቹ አለመሆናቸው፣ 
 • ከፌዴራል እስከ ወረዳ ድረስ በሁሉም ክልሎች ወጥ የሆነ ተቋማዊ አደረጃጀት አለመኖር፣ 
 • አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያንን ታሳቢ ያደረገ የመረጃ ተደራሽነት ችግር፣ 
 • ከመንግሥት አካላት እና አስፈጻሚዎች ጀምሮ፣ በማኅበረሰቡ እንዲሁም በአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ዘንድ ያለው ከፍተኛ የሆነ የግንዛቤ እጥረት፣ 
 • አካል ጉዳተኝነትንና አረጋዊነትን በተመለከተ የተሳሳተ ግንዛቤ መኖር፣ 
 • ወጥ የሆነ የመረጃ አያያዝና ወቅታዊ መረጃዎች እጥረት እና መረጃ አመንጪና ፈላጊ ተቋማት በየጊዜው እየተገናኙ መረጃዎችን አለመለዋወጥ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያንን መብቶች ለማስጠበቅ አዳጋች ሁኔታ መፍጠሩን አንስተዋል፡፡

በማስከተልም ተሳታፊዎቹ ከላይ የተጠቀሱትን ተግዳሮቶች በዓይነት በመለየት የመፍትሔ እርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚገባ በማሳሰብ፤ 

 • ቀጥተኛ የሆነና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችል አካል ጉዳተኞችንም አረጋውያንንም የተመለከተ ሕግ ማውጣት፣ 
 • ለሕግና ለፖሊሲዎች የሚሆን ዝርዝር እና የተብራራ መረጃ ማደራጀት፣
 • አገልግሎት እየሰጡ ያልሆኑ የሰው ሰራሽ ድጋፍ ሰጪ ማዕከላት በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገቡ ማስቻል እና እንዲህ ዓይነቱ ተቋም በሌላቸው ክልሎች ደግሞ እንዲቋቋም ማድረግ፣ 
 • ሁሉም የአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ ማድረግ፣
 • በቀጣዩ ብሔራዊ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ላይ የተደራጀ መረጃ እንዲሰበሰብ እና እንዲደራጅ ማድረግ፣ 
 • ኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራውን የበለጠ እንዲያጠናክር ማድረግ ላይ በዋናነት ትኩረት አድርጎ መሥራት ለመፍትሔዎቹ ይበልጥ ጠቃሚ ነው የሚሉት ምክረ ሃሳቦች ቀርበዋል።