የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ለተውጣጡ 35 የማኅበራቱ የሥራ ኃላፊዎች እና አባላት በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ ያላቸውን ዕውቀት ለማጎልበት ያለመ ስልጠና ከጥር 22 እስከ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. በአሶሳ ከተማ ሰጥቷል፡፡

ስልጠናው በተለይም ሰብአዊ ክብር፣ እኩልነት፣ አድሎ አለመፈጸም፣ ፍትሐዊነት እና አካታችነትን የመሳሰሉ መሠረታዊ የሆኑ የሰብአዊ መብቶች እሴቶች፤ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ለአባሎቻቸው እና ለተጠቃሚዎቻቸው በሚሰጡት አገልግሎት ሊጠብቋቸው የሚገቡ እሴቶች መሆናቸውን በተመለከተ የተሳታፊዎችን ዕውቀት እና አመለካከት ለማዳበር የሚያስችሉ ክንውኖችን ያካተተ ነበር፡፡

ተሳታፊዎች በዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና ብሔራዊ የሕግ ማዕቀፎች ውስጥ የተደነገጉ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ዝርዝር ይዘቶችን እንዲሁም ለማኅበራቸው አባላት እና ተጠቃሚዎች የሚሰጡት አገልግሎት የሰብአዊ መብቶች መርሆች እና እሴቶችን ያከበረ እንዲሆን ለማድረግ የሚያግዟቸው ቁልፍ መርሆችን በተመለከተ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ ስልጠናው ምቹ አጋጣሚን ፈጥሯል።

አካል ጉዳተኝነትን እንደ አንድ የብዝሀነት መገለጫ ከመቀበል፣ ከእኩል ዕድል፣ ከማካተት፣ ከተደራሽነት፣ ከተመጣጣኝ ማመቻቸት እንዲሁም ሰብአዊ መብቶችን መሠረት ያደረገ አገልግሎት አሰጣጥን ተግባራዊ ከማድረግ ጋር በተገናኘ የሚታዩ አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችን ለመለየት እና ተግባራዊ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችላቸውን ስልት የመንደፍ ክህሎት በስልጠናው በተግባር እንዲለማመዱ ለማድረግ ተችሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተሳታፊዎች ስልጠናውን መልሰው ለሌሎች የማኅበራቸው አባላት የሚያካፍሉበትን ክህሎት ማስጨበጥ ተችሏል፡፡

የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ከአካል ጉዳተኞች ሰብአዊ መብቶች አፈጻጸም ጋር በተገናኘ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመለየት እና የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ለመወትወት እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች የክትትል ሥራ መሥራት የሚያስችላቸውን ክህሎት በተግባር እንዲለማመዱ ስልጠናው የተለያዩ ተግባራትን ያካተተ ነበር።

በመጨረሻም የማኅበራቱ የሥራ ኃላፊዎችና አባላት አካል ጉዳተኞች የአካል ጉዳት ከሌለባቸው ሰዎች እኩል በመብቶቻቸው መጠቀም እንዲችሉ እና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጎጂ እንዳይሆኑ በስልጠናው ያገኙትን የሰብአዊ መብቶች ዕውቀት፣ አመለካከት እና ክህሎት በመጠቀም ተግባራዊ እርምጃ ለመውሰድ ተነሳሽነት እንዳደረባቸው ገልጸዋል፡፡