የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጥር 5 ቀን 2014 ዓ.ም. በድሬደዋ ከተማ ከሶማሌ ክልል ከፋፈን፣ ጀረር እና ሲቲ ዞን የፖሊሰ ጣቢያ አመራሮች፣ ከክልሉ ምክር ቤት፣ ከክልሉ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት (ጽ/ቤት) ፣ ከክልሉ የሰላምና ፀጥታ ቢሮ እና ከሌሎች ቢሮዎች ከተወጣጡ 25 ኃላፊዎች ጋር በእስረኞች አያያዝ ጉዳይ ላይ ያካሄደው ውይይት በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ። ኮሚሽኑ ከኅዳር 26 እስከ ታኅሣሥ 06 ቀን 2014 ዓ.ም. በሦስቱ ዞኖች በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ባደረገው ክትትል ግኝቶች ላይ የተመሰረተው ይህ ውይይት፣ በተጠርጣሪዎች አያያዝ ላይ የታዩ ጥንካሬዎችንና ክፍተቶችን አንስቷል።

የክትትሉን ግኝቶች ለተሳታፊዎች ያቀረቡት የኢሰመኮ ጅግጅጋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ባልደረባ አቶ አብዱልናስር በረከት “ውይይቱ በተለይም ከባለድርሻ አካላቶች ጋር በክትትሉ የተለዩ ክፍተቶችን ለማረም መግባባት ላይ ለመድረስ ያስቻለ ነው” ብለዋል። ተሳታፊዎቹ በበኩላቸው በክትትሉ የተለዩ ጥሩ ተሞክሮዎችን ለማስቀጠል እና ክፍተቶችን በማረም በክልሉ የእስረኞች ሰብአዊ መብቶች ጥበቃ እንዲሻሻል ከኢሰመኮ ጋር በቅርበት ተባብረው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ መድረክ ከሲዳማ ክልል እና ከደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ከመጡ ተሳታፊዎች ጋር በሃዋሳ ከተማ የተካሄደ ሲሆን፣ በቀጣይ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ከተማ እንደዚህ አይነት ስብሰባ የሚዘጋጅ ይሆናል፡፡